አዎ! ይቻላል!!!

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ “ቱኒዚያዊያን፣ ግብጾች፣ የመኖች፣ ሊቢያዊያን እና ሌሎች  የአካባቢው አገር ዜጎች ማድረግ የቻሉትን እናንተ ማድረግ አትችሉም፤ ፈጽሞ አታስቡት” እያለን ነው። ውሸት ማውራት ሥራቸው የሆነው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን “በመለስ ዜናዊ  ሥልጣን ላይ አንዳች ተቃውሞ ከተቃጣ አገሪቱ ትታመሳለች” በማለት ያስፈራራሉ። የመለስና ቤተዘመዶቹ ደካማና ዘረኛ ድርጅትን ግዙፍና የማይደፈር አድርገው ያቀርባሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን ወላጆች ለልጆታቸው ባርነትና ፈሪነትን እንዲያስተምሩ ያበረታታሉ፤ “ልጆቻችሁን ጠብቁ” እያሉም ይሰብካሉ፤ ያሰብካሉ።

እኛ ግን “የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች ማድረግ የቻሉትን እኛ ኢትዮጵያዊያን ማድረግ የማንችልበት ምክንያት የለም” እንላለን። እራሳችንን ከሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች ጋር ባወዳደርን መጠን ደግሞ ልበ ሙሉነት ይሰማናል።

  1. የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች ለአስርት ዓመታት በአምባገነን አገዛዝ ተገዝተዋል። እኛ ደግሞ ለአስርት ዓመታት አምባገነን ብቻ ሳይሆን ዘረኛም ጭምር በሆነ  አገዛዝ እየተገዛን ነው። እኛ እየደረሰብን ያለውን ዓይነት አዋራጅ ዘረኝነት እነሱ ላይ አልደረሰባቸውም። አምባነንነት እነሱን አስመርሮ በገዚዎቻቸው ላይ በአንድነት እንዲነሱ አድርጓቸዋል። እኛ ዘንድ ደግሞ አምባገነንነትና ዘረኝነት ተዳብለውብናልና ከእነሱ በላይ አምርረን በህብረት እንነሳለን።
  2. እነሱ አገር ውስጥ ኑሮ  በመወደዱና  ሥራ በመጥፋቱ ድህነት አስመርሯቸዋል። እኛ አገር ደግሞ የዛሬ ኑሮዓችን ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋችን ጭምር ጠፍቶብናል። ለም መሬታችን ለባዕዳን ተሽጦብናል። እነሱ ያጡት ሥራ ነው፤ እኛ ግን አገርም የለንም። እኛ ከነሱ በላይ አምርረን ለመነሳት በቂ ምክንያቶች አሉን።
  3. የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሹሞች በሙስና ያካበቱት ሃብት በቢሊዮን ዶላሮች ይገመታል። የእኛ የመጨረሻይቱ ድሃ አገር ሹሞችም በሙስና ያካበቱት ሃብት በቢሊዮን ዶላሮች ይገመታል። እርግጥ ነው በከተሞቻችን ህንፃዎች በርክተዋል ሆኖም ግን የሙሰኞቹ እንጂ የለፍቶ አዳሪዎቹ አይደሉም። በሃብት መበላለጥ የተቆጩት እና በሙስና መብዛት የተናደዱ የአህጉራችን ዜጎች  በገዢዎቻቸው ላይ ተነስተዋል። እኛ ደግሞ  ከእነሱ በላይ ተጎድተናልና ከእነሱ በላይ አምርረን እንነሳለን።
  4. የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች በያገራቸው ፍትህ በመጓደሉ ተማረዋል። እኛ አገር ደግሞ ፍትህ ራስዋ ተዋርዳለች። ፍርድ ቤቶች ማጥቂያዎች ሆነዋል። አገራችን እስር ቤት ሆናለች። አብዮት ከቀሰቀሱት ጎረቤቶቻችን በባሰ እኛ ተበድለናልና  ከእነሱ በባሰ አምርረን እንነሳለን።
  5. የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች ለዘመናት መብቶቻቸው ተገፎ “የታዘዛችሁትን አድርጉ፤ አንዳችም ነገር አትጠይቁ” ሲባሉ ኖረዋል። እኛም ለሃያ ዓመታት “እኛ ስንናገር እናንተ አጨብጭቡ፤ ከዚያ ባፈለ ግን አትጠይቁ” እየተባልን ነው። እነሱ “በቃን” ብለዋል፤ እኛም “በቃ – ጋዮ” ብለናል።

“ኢትዮጵያ ቱኒዝያ ወይም ግብጽ አይደለችም” የሚለውን ፕሮፖጋንዳ ሰልችቶናል። በቱኒዝያና ግብጽ ብቻ ሳይሆን በየመንና ሊቢያ ህዝብም ጥንካሬ እንኮራለን። ለአርባ ሁለት ዓመታት የተደራጀን ኃይል በሳምንታት ውስጥ በተፈጠረ የአማጽያን ኃይል እያርበደበደ ያለው የሊቢያ ህዝብ ጥንካሬ የልብ ልብ ሰጥቶናል።

በአምባገነን አገዛዝ መረገጥ በቃን!!!! የሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ዜጎች ማድረግ የቻሉትን እኛ ኢትዮጵያዊያን ማድረግ እንችላለን። አዎ! እኛም እንችላለን! ይቻላል!!

በቃ- ጋዮ!!!!