ስጋት አርግዘን ስጋት ለብሰናል! (ግሩም ተ/ኃይማኖት – የመን)
በየመን ያለ ሀበሻ ቁጥሩ ሲጠራ የሚያምን የለም::ትክክል የማይመስል ነገር ነው። በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ ሁኔታ የመን ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊ ከ 80,000 በላይ ነው። 5000 የምንጠጋው በUNHCR ስር ያለን ስንሆን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማቋረጥ እና የመን ለመኖር ከጅቡቲ..ከሱማሊያ..ተነስተው በባህር በየእለቱ የሚገቡትን መገመት ይከብዳል። ከ4,000,000 በላይ ትውልደ ሀበሻ አለ። ከአረብኛው ቀጥሎ ህዝቡ በሰፊው የሚናገረው አማርኛ ቋንቋ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የሚያሳየው የመናዊያን እና ኢትዮጵያዊያን አብረው የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ነው። ነገር ተገልብጦ ሆኗል። ትላንት ችግራቸውን ለመቅረፍ ወደ ሀገራችን እንዳልተሰደዱ ለሀበሻ ያላቸው ጥላቻ ኢትዮጵያን እጀ ሰባራ ያሰኛታል። ለነገሩ እንኳን የተጠለለባት ከአብራኳ የወጣውስ ነካሽ እንጂ አይዞሽ ባይ መች ሆናት?…ቢሆን ኖሮ ከነቀዞች ማላቀቂያው ሰዓት አሁን ነበር።