ርኅራኄያዊ ግድያ
ባለፈው ጊዜ ዱባይ እያለሁ ነው ይህንን ታሪክ አንዲት እኅት የነገረችኝ፡፡ ከአራት ዓመታት በላይ እዚያ ሠርታለች፡፡ ያገኘችውን ወደ ሀገር ቤት ትልካለች፡፡ ልብሱ፣ የቤት ዕቃው፣ ገንዘቡ፣ ጌጡ፣ ሽቱው አይቀራትም፡፡ መላክ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ተባብራ ካርጎ ትጭናለች፡፡
እናቷ ደውለው «ከጎረቤትኮ እገሌ ታምሞ መታከሚያ አጣ» ይሏታል ተልካለች፡፡ ወንድሟ «እንዲህ ላደርግ ነበር ገንዘብ አጣሁ» ይላል ትልካለች፡፡ «እገሌ የተባለ ዘመድሽ ምነው ረሳችኝ ብሎሻል» ትባላለች ትልካለች፡፡ አንዳንዴም «እንዴው ለዚህ ቤተ ክርስቲያን ቃል ገብተን ነበረ» ይሏታል ትልካለች፡፡ ብቻ ከራሷ በስተቀር ሁሉንም ልካለች፡፡
የኤምሬትስ ስደት ሲሞላ ሲጎድል ነው፡፡ ቪዛዋ ይሠረዝባታል፡፡ ያ ሰሞን ደግሞ ፖሊሶቹ ተነሥቶባቸው ከየመንገዱ እያፈሱ ወደ ሀገር ቤት ሰውን መላክ ጀምረው ነበር፡፡ አንዳንዴም አበሻ አለበት በሚባለው ሠፈር ፍተሻ ያደርጉ ነበር፡፡ እየተደበቁ መኖሩ ሰለቻት፡፡ መሰልቸት ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ መደበቁ ሥራ እንዳትሠራም አደረጋት፡፡ እጇም እያጠረ መጣ፡፡
ይኼኔ መረራትና ወደ ሀገሯ ልትገባ ወሰነች፡፡ አስቀድማ ግን እንዲዘጋጁ ለወላጆቿ ለመንገር አሰበችና ደወለች፡፡ «እኔ እዚህ ሀገር ያለ ቪዛ መኖር ሰልችቶኛል፡፡ በየቀኑ መደበቁም አስመርሮኛል፡፡ አሁን ወደ ሀገሬ ልመጣ ነው» አለች፡፡ ይኼኔ አባቷ «ኧረ ልጄ ሲሆን እኅቶችሽንም መውሰድ ነው እንጂ አንቺማ አትምጭ» አሏት፡፡ «እኔ እዚህ ሀገር ከዚህ በኋላ መሰቃየት አልፈልግም፤ ልመጣ ነው፡፡ መሥራትም አልቻልኩም፡፡ ከፖሊሶቹ መደበቅም አልቻልኩም፡፡» ትላቸዋለች፡፡ «አንቺ ከመጣሽኮ የኛ ኑሮ አበቃ ማለት ነው፤ ግዴለም እንደምንም ብለሽ እየተደበቅሽ ሥሪ» ይሏታል፡፡ «እንዴ አባዬ የት እደበቃለሁ፤ መንገድ መሄድኮ አልቻ ልኩም፤ ይይዙኛል» ትላለች፡፡ «አይ እንደው እንደምንም በጫካም ውስጥ እየተደበቅሽ ቢሆን ሥሪ» ይሏታል፡፡
ይኼኔ ዕጢዋ ዱብ ይላል፡፡ «እነዚህ ሰዎች ገንዘቤን እንጂ እኔን አይፈልጉም ማለት ነው?» ትላለች ለራሷ፡፡ ከዚያ በኋላ ቪዛዋን የምታሠራበትን መንገድ ማፈላለግ ትጀምራለች፡፡ አይገቡ ገብታም በጭንቅ ታገኛለች፡፡ ስልኳን ግን ከቤተሰቧ ለመጨረሻ ጊዜ ሠወረች፡፡ መገናኘትም አቆመች፡፡
ይህንን ታሪክ ዛሬ ያስታወሰኝ እዚህ አሜሪካ አንዲት ሌላ እኅት የነገረችኝ ታሪክ ነው፡፡ ከዋሽንገተን ዲሲ ወደ ኦክላንድ ካሊፎርንያ ለመብረር ዳላስ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እያለሁ አገኘኋትና ማውራት ጀመርን፡፡ «እንዴት ነው ኑሮ በአሜሪካ? አገባሽ? ወለድሽ? ለውጥ የለም ወይ?» አልኳት፡፡ እየሳቀች የሚከተለውን ታሪክ አወጋችኝ፡፡
«ባለፈው እንዳስተዋወቅኩህ አንድ እጮኛ ነበረኝ፡፡ አንድ አምስት ዓመት አብረን አሳልፈናል፡፡ እኔ ለማግባት ካሰብኩ ቆየት ብያለሁ፡፡ ግን አንድ ሃሳብ ነበረኝ፡፡ መጀመርያ ቤተሰቦቼን ልርዳ የሚል፡፡ ለወላጆቼ ኮንዶሚኒየም ቤት ገዛሁ፡፡ እርሱ ብቻ ነው የተሳካልኝ፡፡ ታናሹ ወንድሜን ኮሌጅ ላስተምር ጀምሬ ነበር፡፡ «አሜሪካ ውሰጅኝ እንጂ አልማርም» አለኝ፡፡ ብለው ብሠራው አይሆንም አለ፡፡ ታናሿ እኅቴ ደግሞ «አንቺ ከዚያ ዕቃ ላኪልኝ እኔ እዚህ ሱቅ ልክፈት» አለች፡፡ መጀመርያ ሳስበው መልካም ሃሳብ ነው ብዬ ጀመርኩት፡፡ ግን ሊዘልቅ አልቻለም፡፡
አንደኛ ሌላ ሥራ ሆነብኝ፡፡ እኔ እዚህ በርካሽ ያለበትን ቦታ ማሠስና ሰው ፈልጎ መላክ ሆነ ሥራዬ፡፡ ከዚያም በላይ ለዕቃው መግዣ ገንዘብ እኔ ነኝ የምከፍለው፡፡ ጥቂት ጊዜ ከረዳኋት በኋላ ከእንግዲህ ራስሽን ችለሽ ሥሪ፡፡ እኔ ይህንን የዘወትር ጉዳዬ ማድረግ አልችልም አልኳት፡፡ አኮረፈችና ሥራውንም ተወችው፡፡
እኔ ሲሰለቸኝ ይህንን ያህል ዘመን ከረዳሁ አሁን ደግሞ ወደራሴ ሕይወት ለዙር ብዬ ትዳር ለመመሥረት አሰብኩ፡፡ ያንን ለቤተሰቦቼ ስነግራቸው አበዱ፡፡ እንዴት እኛ ወንድምሽን አግብተሽ ትወስጅዋለሽ እያልን አንቺ ሌላ ታገቢያለሽ አሉኝ፡፡ ይታይህ እንግዲህ እርሱን አግብቼ ካመጣሁት ከዚህ በኋላ ቢያንስ ሁለት ዓመት መጠበቅ አለብኝ፡ እኔ ደግሞ እድሜዬ እየጨመረ ነው፡፡ እርሱን እንደዚህ ማድረግ አልችልም አልኳቸው፡፡ ካልሆነ አንቺም ሌላ ሰው አግብተሽ ውሰጅ፣ በምትኩም እኅትሽን አግብቶ የሚወስድ ፈልጊ እንጂ አይሆንም አሉኝ፡፡
እስከ መቼ የኔ ሕይወት በሌሎች ፈቃድና ፍላጎት ይመራል ብዬ አሰብኩ፡፡ ለእኔ ሕይወትስ የሚያስብ የለም ወይ? እኔ እኅታቸው ወይንም ልጃቸው ነኝ ወይስ የርዳታ ድርጅታቸው? የኔ የርዳታ መጠንስ እስከየት ድረስ ነው? ብዙ ነገር አሰብኩ፡፡ ሲመረኝም ርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ አሁን በቃ በራሴ ወስኜ ላገባ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ግን ሁሉም አኩርፈውኛል፡፡ ባይሆን እናንተ ትድሩኛላችሁ» አለች እየሳቀች፡፡
ብዙ ወገኖቻችን ወደ ውጭ ሀገር ለኑሮና ለሥራ ከሚሄዱበት ምክንያት አንዱ ቤተ ሰቦቻቸውን ለመረዳት ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ማሳለፍ እንደ ትልቅ ስኬት ያዩታል፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን የመደገፍ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ግዴታ አለና የሚመሰገን ነው፡፡ ነገር ግን ርዳታችን የት ድረስ መሆን አለበት? የምንረዳው እነማንን ነው? የምንረዳበት ዓላማስ ምንድን ነው? ርዳታችንስ በሰዎቹ ላይ ምን መፍጠር አለበት? መርዳት ያለብን መርዳት ስለቻልን ነው ወይስ መረዳት ስላለባቸው? ውለታን መክፈል የሚቻለውስ በመርዳት ብቻ ነው? የሚሉትን በሚገባ ካልመለስናቸው ርኅራኄያችን ከሚያድናቸው ሰዎች ይልቅ የሚገድላቸው ሰዎች ሊበዙ ይችላሉ፡፡
ርዳታ ሰውን ከችግር ለማውጣትና ሕይወቱ እንዲቀጥል ለማድረግ እንደሚያስችለው ሁሉ ርዳታ ሰውንም ይገድለዋል፡፡ ሰውዬውን ሞራለ ቢስና ጥገኛ አድርጎ ያኖረዋል፡፡ ከነ ሙሉ ክብሩና ግዴታው እንዳይኖርም ያደርገዋል፡፡ ሕልውናውን በሌሎች ላይ ብቻ እንዲመሠርትም ያደርገዋል፡፡ ርዳታ ሰውን ሰነፍና ሃሳብ የለሽ ሊያደርግ ይችላል፡፡
እዚህ አሜሪካ ከሚኖሩ አፍሪካ አሜሪካውያን ከፊሎቹ በሀገሩ የሚሰጠውን የማኅበራዊ ዋስትና ርዳታ ብቻ በመቀበል የሚኖሩ ናቸው፡፡ መሥራትን እንደ ባህል እንዳይቀበሉት፣ ጥሮና ግሮ መኖርንም እንደ ስቃይ እንዲያዩት አድርጓቸዋል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ርዳታ የሚገኝባቸውን መንገዶች በማፈላለግ ኑሯቸውን በርሱ ላይ ይመሠርታሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በአብዛኛው ርዳታ በሚሰጥባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ በርዳታ ተወልደው በርዳታ የሚያድጉ ልጆችን በማፍራታቸውም የርዳታ ተቀባዩ ትውልድ ሠንሠለቱን ማቋረጥ አልተቻለም፡፡ አንዲያውም ርዳታውን በደንብ ለማግኘት ሲባል በልጅነት መውለድንና ብዙ ልጆች ማፍራትን ያዘወትራሉ ይባላል፡፡
የማኅበራዊ ዋስትና ገንዘብ እነዚህን ሰዎች ጠቀማቸው ወይስ ጎዳቸው? የሚል ክርከር እየተነሣ ነው፡፡ ርኅራኄው አድኗቸዋል ወይስ ገድሏቸዋል? ብዙ ልጆችን ከተለያዩ ባሎች እንዲወልዱ፤ ትምህርታቸውን በጊዜ እንዲያቋርጡ፤ ሥራን በአግባቡና በሥርዓቱ እንዳይሠሩ፤ አካባቢያቸው በንጽሕናና በጽዳት የተጠበቀ እንዳይሆን አንዱ አስተዋጽዖ ያደረገው በርዳታ ተደግፈው መኖራቸው ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡
ገንዘቡ እንደልብ የሚገኝና ድካም የማይከፈልበት በመሆኑም በቁጠባ ለዘላቂ ነገር ከማዋል ይልቅ ለአደንዘዥ ዕጽና ለመጠጥ እንዲጠቀሙበት አድርጓቸዋል፤ ወንጀል እንዲበራከትና ግብር መክፈልን ባህሉ የማያደርግ ትውልድ ለማፍራትም አብቅቷቸዋል የሚሉ ተከራካሪዎችም ተነሥተዋል፡፡
በኛም ሀገር ቢሆን ችግረኞችን እንደዚህ ሀገር በተቀናጀ መንገድ እንኳን ባይሆን በየግላችን የመርዳቱ ባህል አለን፡፡ አንዱ ሀብትን ለሌሎች የምናካፍልበት መንገድ ነውና፡፡ በሃይማኖትም ቢሆን ድኾችን መርዳት ግዴታ ነው፡፡ ጥያቄው ግን ድኾች እነማን ናቸው? የሚለውና ድኾችን በትክክለኛው መንገድ መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ነው፡፡
በየቤተ ክርስቲያኑና መስጊዱ አያሌ ነዳያን ተኮልኩለው ይገኛሉ፡፡ እዚያ የሚኖሩበት ምክንያትም አላቸው፡፡ ለእነርሱ የመስጠት ሃይማኖታዊ ግዴታ አለብን የሚሉትን ምእመናን የሚያገኟቸው እዚያ ስለሆነ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የተደረገ ጥናት እንዳሳየው በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዙርያ ያሉ ነዳያን እዚያው በመኖር ብቻ እስከ አራት ትውልድ አፍርተዋል፡፡ ቅድመ አያቷ ወይም ቅድመ አያቱ እዚያ ትለምን የነበረች ወይም ይለምን የነበረ ትውልድ ዛሬም ሳይቀየር እዚያው ቦታ ላይ አለ፡፡ ነዳያን ነዳያንን እየወለዱ ማለት ነው፡፡
የኛ ርዳታ ነዳያኑን ከነዳይነት የሚያወጣ አልሆነም፤ እንዲያውም የነዳያን ትውልድ እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ እዚህ ላይ ነው ከርዳታችን ባሻገር ስለ ርዳታ አሰጣጣችን እንድናስብበት የሚያስገድደን፡፡ ርዳታችን ነዳያኑን ሳይኖሩም ሳይሞቱም እንዲቀጥሉ እያደረጋቸው ብቻ ነው፡፡ ርዳታችን ነዳይነት እንዳይቋረጥ እያደረገ ብቻ ነው፡፡ ርዳታችን ችግረኛን እያኖረ እንጂ ችግርን እየፈታ አይደለም ማለት ነው፡፡ ነዳያኑ የልመና ግጥማቸውን እንጂ ሕይወታቸውን መቀየር አላስቻላቸውም፡፡
በአንድ ወቅት ከአዋሳ ከመጣ ወዳጄ ጋር አራት ኪሎ ቅድስት ማርያም በር አጠገብ ቆመን ስናወራ አንድ በአካባቢው በልመና የተሠማራ ጎልማሳ ወዳጄን በስሙ ጠራው፡፡ እርሱም ደንግጦ ዘወር አለ፡፡ አንዴ ላናግርህ እችላለሁ? አለው፡፡ ያን ጊዜ እኔ ፈቀቅ አልኩላቸው፡፡ ከአንድ ከሃያ ደቂቃ በኋላ ራሱን እየነቀነቀ መጣ፡፡ እኔም ምን ሆንክ? አልኩት፡፡
ልጁ እነርሱ መሥሪያ ቤት በአትክልተኛነት ይሠራ የነበረ ነው፡፡ አንድ ቀን አዲስ አበባ ለጉዳይ ይመጣል፡፡ ሲዘዋወር ቆይቶ ይደክመውና ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዐረፍ ለማለት ይገባል፡፡ በጣም ደክሞት ስለነበር አንዱ ዛፍ ሥር ጥቅልል ብሎ ይተኛል፡፡ ሲነሣ የሆነው ነገር የሕይወቱን መሥመር አስቀየረው፡፡
ከዕንቅልፉ ሲነሣ በዙርያው ብዙ ብሮችና ሳንቲሞች ተዘርግተዋል፡፡ እየገረመው ዘወር ዘወር ብሎም እያየ ቆጠራቸው፡፡ አሥራ ስምንት ብሮች ተሰባስበዋል፡፡ እርሱ በወር የሚያገኘው ሦስት መቶ ብር ነው፡፡ አሁን ምንም ሳይለፋ አሥራ ስምንት ብር አገኘ፡፡ ታድያ ለምን ጥቂት ጊዜ አልሠራም አለና ጀመረው፡፡ «ይኼው ዓመት ሆነኝ፡፡ አሁን አዋሳ ቤት እየሠራሁ ነው» አለና ነገረው፡፡ እንደዚህ ልጅ ልመናን ቀላል የገንዘብ ማግኛ መንገድ እድርገውት የተሠማሩ «ፕሮፌሽናል ለማኞች» ሞልተዋል፡፡
አንዳንዱ ርዳታ የኛን ርኅሩኅነት እንጂ የችግሩን መልክ የሚያሳይ አልሆነም፡፡ የምንሰጠው ርዳታ የሰውዬውን ችግር ይፍታ አይፍታ? ለሰውዬው የሚያስፈልገው ያ ይሁን አይሁን አናመዛዝንም፡፡ ብቻ መስጠት ግባችን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ርኅራኄያችን ከመጥቀም ይልቅ የሚጎዳበት ጊዜ አለ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በውጭ ያሉ ወገኖች ለቤተ ሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ወደ ሀገሪቱ ከሚገቡ ገንዘቦች ትልቁን ቦታ እየያዘ መምጣቱ ይሰማል፡፡ ይህ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ላሳደገች ሀገር ውለታ መክፈልም ነው፡፡ ነገር ግን የምንልከው ገንዘብ የሚያድን እንጂ የሚገድል እንዳይሆን መጠንቀቅም ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በአሜሪካና በዱባይ ገንዘብ የሚዘንጡ ወገኖችን ማፍራት፤ የሽቱና የጫማ፣ የአይፎንና የአይፖድ ዓይነት እያጠኑ ላኩ የሚሉ ወንድሞችና እኅቶችን ማፍራት በርኅራኄ መግደል ነው፡፡
አንድ በዲግሪ የተመረቀ ወጣት በወር ተጣርቶ ከአንድ ሺ አምስት መቶ ብር በላይ አያገኝም፤ አንድ ወንድሙ ወይም እኅቱ መቶ ዶላር በየወሩ የምትልክለት ተመጽዋች ግን በየወሩ አንድ ሺ ስምንት መቶ ብር የተጣራ ያገኛል፡፡ ይህንን እያየ ማን ይማራል ታድያ? አንዳንዶቹም «እዚህ ኢትዮጵያ የሚሰጠው ትምህርት አሜሪካ ዋጋ ስለሌለው ለምን እደክማለሁ» ይላሉ አሉ፡፡ ኧረ ሌሎቹ ደግሞ «ነገ አሜሪካ ስሄድ ለማቋርጠው ለምን እማራለሁ» የሚሉም አሉ አሉ፡፡ አካላቸው ኢትዮጵያ ልባቸው አሜሪካ የሆኑት፡፡
አንድ ሰው እንዲያውም «እኔ ሀገር ቤት ስደውል ሁሉም ነገር ተወድዷል፤ መኖር አለተቻለም፤ መቅመስም መላስም አልቻልንም የሚሉኝ ርዳታዬን እንዳላቋርጥ ሳይሆን አይቀርም» ብሎኛል፡፡ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮ እየተወደደ ቢሆንም ውጭ ሀገር ያለ ሰው ሲሰማው ግን ቫት 15%ና የአገልግሎት ክፍያ 10% ተጨምሮበት ነው፡፡ ያ ደግሞ ልጁ እንዳለው የርዳታውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ይመስላል፡፡
ርኅራኄ ከደግ ሰዎች እሴቶች አንዱ ነው፡፡ነገር ግን ርኅራኄ የሚያድን እንጂ የሚገድል መሆን የለበትም፡፡ የኛ ግዴታ የመስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ወገኖቻችንንም ከችግር የማላቀቅ ጭምር እንጂ፡፡ አጠቃቀሙን ለማያወቅ ሰው የጋዝ ምድጃ መስጠት መግደል እንጂ መርዳት አይሆንም፡፡ ለአንድ ሰው የት ድረስ እንደሚሄድ ሳይነግሩ መንገድ ማሳየት ማጥፋት እንጂ ማገዝ አይሆንም፡፡
እናም እንርዳ፤ ግን ርዳታችን ሕይወት ለዋጭ እንጂ፤ ልብስ ለዋጭ፣ አይሁን፡፡ አመለካከት ለዋጭ እንጂ ጫማ ለዋጭ አይሁን፡፡ ደረጃ ለዋጭ እንጂ ስልክ ለዋጭ አይሁን፡፡ ራርተን እናድን እንጂ ራርተን አንግደል፡፡
ሳክራሜንቶ፣ ካሊፎርንያ