«ካህናተ ደብተራ»
«እናንተ ደብተራ ከምትባሉት በቀር ይህንን ሁሉ ያደረገ ማነው? ታመሰግኑታላችሁ፣ ታወድሱታላችሁ፣ እንዳንተ ያለ ኀያል ማነው? ትሉታላችሁ፤ እንዳንተ ያለ ድል አድራጊ፣ እንዳንተስ ያለ ለጋሥ በሁሉ ዘንድ ወዴት አለ? እንዳንተ ያለስ ምጽዋት ሰጭ የት አለ? ትሉታላችሁ፡፡ እንዲህ ስታመሰግኑትም በኀጢአት ላይ ኀጢአትን ይጨምራል፡፡»
ይህንን ቃል ከዛሬ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የተናገረው ታላቁ ተጋዳይ አባት አባ በጸሎተ ሚካኤል ዘደብረ ጎል ነው፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን ከክርስትና ሕግ ውጭ የአባቱን ሚስት በማግባቱ እንደ ዮሐንስ መጥምቅና እንደ ዮሐንስ አፈወርቅ ሳይፈራና ሳያፍር ፊት ለፊት በመገሠፁ ብዙ መከራ ደረሰበት፡፡ ተገረፈ፤ ታሠረ፤ ተሰደደም፡፡
አስቀድማ የንጉሡ ሚስት የነበረች በኋላ ደግሞ ንጉሡ ለአንዱ ወታደሩ የሰጣት አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ይህቺ ሴት ይህንን ሕይወት ንቃ ንስሐ ገባችና ሥጋወደሙ ተቀበለች፡፡ ንጉሥ ዓምደ ጽዮን «ሂዳችሁ አምጧት፤ እኔም በመኝታዬ አረክሳታለሁ» ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡ መልክተኛ ወደ ሴቲቱ ሲሄድ እርሷ ወደ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ዘንድ ላከች፡፡
አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ልጆቹን እንዲህ አላቸው «ተነሡ እግዚአብሔር ሥራ እንዲሠራ እንለምነው፡፡ ክውስጣዊ ልብሳችሁ በቀር ሌላውን አውልቁ፡፡ በፊቱም እያለቀስን እንለምነው»፡፡ ሌሊቱን ሙሉ በዕንባና በስግደት፣ በጸሎትና በማዕጠንት እግዚአብሔርን ሲለምኑት አደሩ፡፡ ሲያለቅስ መሬቱ የሚረጥብ አለ፡፡ ሲሰግድ መሬቱ የሚጎደጉድ አለ፡፡ ደረቱን ሲደቃ ውጭ ድረስ የሚሰማ አለ፡፡ ሲያጥን ዕንባው እሳቱን የሚያጠፋው አለ፡፡
ሌሊት ንጉሡ በከባድ ሕመም ታመመ፡፡ ነፍሱም ልትወጣ ደረሰች፡፡ ያን ጊዜ ባለሟሎቹ ቀረቡ፡፡ እርሱም «ይህ ሕመም በምን ምክንያት እንደ መጣ አውቄዋለሁ፤ ያቺን የበጸሎተ ሚካኤልን ልጅ ላረክሳት በመፈለጌ ነው፡፡ አሁንም ሂዱና ይቅር በለኝ በሉት» ብሎ በቤተ መንግሥቱ የሚያገለግሉትን ካህናት ላካቸው፡፡
ካህናቱ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል ሲደርሱ «ልጆቼ ተነሡ እግዚአብሔር ሰምቶናል፡፡ ልብሶቻችሁን ልበሱ፤ መልክተኞችም መጥተዋል» አላቸው፡፡ እነርሱም ተነሥተው ከመቅደስ ሲወጡ የንጉሡን መልክተኞች አገኟቸው፡፡ መልክተኞቹም የንጉሡን መልክት ነገሩት፡፡ አባ በጸሎተ ሚካኤልም «እግዚአ ብሔር ይቅር ይበልህ በሉት» አላቸው፡፡ የንጉሡን አገልጋይ ካህናት ግን እጅግ ወቀሳቸው፡፡
አባ በጸሎተ ሚካኤል የወቀሳቸው ካህናት በዚያ ዘመን «ካህናተ ደብተራ» ይባሉ ነበር፡፡ ስማቸው የተወሰደው በንጉሡ ቤተ መንግሥት የምትገኘውንና በድንኳን ያለቺውን ቤተ ክርስቲያን ስለሚያገለግሉ ነው፡፡ ነገሥታቱ በየሀገሩ ስለሚዘዋወሩ የድንኳን ቤተ ክርስቲያን ነበራቸው፡፡ እዚያ ካህናት ይመደባሉ፡፡
የእነዚህ ካህናት ጠባይ በሌላው ቦታ ከነበሩት ካህናት ጠባይ ይለይ ነበር፡፡ ካህናተ ደብተራ የሚታወቁባቸው ጠባያት ነበሯቸው፡፡ የመጀመርያው ጠባያቸው በገዳም ከሚኖሩት ቅዱሳን አበው ጋር አለመስማማታቸው ነው፡፡ ለእነርሱ ገዳማዊ ሕይወት ጊዜ ማጥፋትና ራስን ማሞኘት ነው፡፡ በገዳም ያሉ አባቶቸንም በትኅትናቸው ምክንያት ይንቋቸው ነበር፡፡ እነርሱን ማሳጣትና መክሰስ ብሎም ከየገዳማቸው ማሳደድ የዘወትር ተግባራቸው ነበር፡፡ ገዳማቱ ሲፈቱና ማኅበረ መነኮሳቱ ሲበተኑ ምንም ዓይነት ቁብ አይሰጣቸውም ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የንጉሡ ወታደሮች የሚያዝኑላቸውን ያህል ካህናተ ደብተራ ለገዳማውያን አባቶች አያዝኑም፡፡ ወደ ንጉሡ ዘንድ ደርሰው ጉዳያቸውን እንዳያስፈጽሙ ከጠባቂዎቹ ይልቅ የሚያስቸግሯቸው ካህናተ ደብተራ ነበሩ፡፡
ሁለተኛው ጠባያቸው ደግሞ ማንኛውንም ነገር ከጥቅም ጋር ማገናኘታቸው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ሕግ፣ የእግዚአብሔር ቁጣና ቅጣት አይታያቸውም፡፡ ከንጉሡ ማዕድ እየበሉና ፍርፋሪ እየለቀሙ፣ በንጉሡም ካባና ላንቃ እየተሸለሙ ስለሚኖሩ የሚሠሩት የሚገባቸውን ሳይሆን የሚያበላቸውን ነው፡፡ በቤተ መንግሥቱ ያገኙትን ክብርና ማዕድ እንዳያጡ ሲሉ ማንኛውንም ኢ ሃይማኖታዊ የሆነ ተግባር ከማድረግ አይመለሱም፡፡
በገድለ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ላይ እንደ ተጻፈው ዓምደ ጽዮንንም ሆነ ልጁን ሰይፈ አርእድን ትክክል ያልሆነ ትምህርት አስተምረው ያሳሳቱት ካህናተ ደብተራ ናቸው፡፡ አቡነ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ ወደ ዓምደ ጽዮን ገብተው ለምን ይህንን ጥፋት እንዳጠፋና የአባቱን ሚስት እንዳገባ ሲጠይቁት « ዐዋቂዎች የሆኑ ካህናት እርሷን ካላገባህ መንግሥትህ አይጸናም ብለውኝ ነው» ነበር ያላቸው፡፡ ከካህናተ ደብተራ አንዱ የነበረው እወደድ ባዩ ዘአማኑኤል የተባለ ሰው ከንጉሥ ዓምደ ጽዮን በኋላ የነገሠውን ሰይፈ አርእድን በተመሳሳይ ስሕተት አሳስቶት ነበር፡፡ «ከጥቂት ጊዜም በኋላ ዘአማኑኤል የሚባል አንድ ሰው ተነሣ፡፡ ይህም በግብር ሳይሆን በስም ነው፤ እርሱ ንጉሡን እንዲህ ሲል አሳስቶታልና፡ አንተ ንጉሥ ነህና በአንዲት ሚስት ልትኖር አይቻልህም፤ ንጉሥማ ሦስት ሚስት እንዲያገባ ታዝዞለታል ብሎም አስተማረው» (ገድለ አቡነ ፊልጶስ፣ ገጽ 225)
ካህናተ ደብተራ ንጉሡን የሚያስደስትና ጥቅማቸውን የሚያስከብር ከመሰላቸው ከንጉሡ በላይም ሄደው ግፍ ከመፈጸም አይመለሱም ነበር፡፡ በሰይፈ አርእድ ዘመነ መንግሥት ተመሳሳይ ስሕተት መሠራቱን አይተው አበው ከየአቅጣጫው መጥተው ሲገሥፁት አቡነ አኖሬዎስ ንጉሡን በኃይል ተናገረው፡፡ ይህንን ያየው የንጉሡ ማዕድ ባራኪ ካህን ወይም ቄስ ሐፄ ከወታደሮቹ ተሽቀዳደመና አቡነ አሮንን በጥፊ መታው፡፡ ለምን እንደ መታው ገድለ አቡነ አኖሬዎስ ሲናገር «በንጉሡ ዘንድ ሊመሰገን ሽቶ» ይለዋል፡፡ ያን ጊዜም አቡነ አኖሬዎስ «ለምን ትመታኛለህ? ለሰው ከማድላት ለእግዚአብሔር ማድላት አይሻልህም ነበር?» አለው ይላል፡፡ ቄስ ሐፄው ግን ያሰበውን ምስጋና አላገኘም፡፡ በአበው ኀዘን ምክንያት ወዲያውኑ ሞተ፡፡
የካህናተ ደብተራ ሌላው ጠባይ ደግሞ ወተቱን ማጥቆር ከሉን ማንጣት ነው፡፡ እውነትን የሚመዝኗት ከጥቅማቸው አንፃር ብቻ ስለነበረ ኃጢአት ሲሠራ እያዩ ጽድቅ ነው፤ ግፍ ሲፈጸም እያዩ ቅድስና ነው ማለት ይወዱ ነበር፡፡ ነገሥታቱና መኳንንቱ በበደል ላይ በደል እንዲጨምሩ ያደርጓቸው የነበሩትም እነርሱ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው አቡነ በጸሎተ ሚካኤል ወደ እርሱ ለማማለድ የመጡትን ካህናተ ደብተራ «እናንተ ደብተራ ከምትባሉት በቀር ይህንን ሁሉ ያደረገ ማነው? ታመሰግኑታላችሁ፣ ታወድሱታላችሁ፣ እንዳንተ ያለ ኀያል ማነው? ትሉታላችሁ፤ እንዳንተ ያለ ድል አድራጊ፣ እንዳንተስ ያለ ለጋሥ በሁሉ ዘንድ ወዴት አለ) እንዳንተ ያለስ ምጽዋት ሰጭ የት አለ? ትሉታላችሁ፡፡ እንዲህ ስታመሰግኑትም በኀጢአት ላይ ኀጢአትን ይጨምራል፡፡» ያላቸው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
አንዳንዶቹ የካህናተ ደብተራ ወገኖች ሹመት እንጂ እምነት አልነበራቸውም፡፡ በገድለ አቡነ አኖሬዎስ ላይ እንደ ግብጦን በተባለ ቦታ ንቡረ እድነት የተሾመ አንድ የካህናተ ደብተራ ወገን ነበረ፡፡ ይህ ሰው ምንም ሳያደርገው በቅድስናው ብቻ አቡነ አኖሬዎስን ይጠላው ነበር፡፡
አንድ ቀን «ምን እንደምትሠራ ለማየት እመጣለሁ» ሲል ላከበት፡፡ ይህ ሰው ሹመት ሽልማት ፈልጎ ንቡረ እድ ሆነ እንጂ እግዚአብሔርን እንኳን የማያመልክ ሰው ነበረ፡፡ ገድለ አቡነ አኖሬዎስ እንዲህ ይላል «ቅዱሱም በዚያ በገዳሙ እያለ ስሙ ጳውሎስ የሚባል አንድ ሰው በትዕቢት «መጥቼ ሥራህን አያለሁ» ብሎ ወደ እርሱ ላከበት፡፡ ያም በስም መነኩሴና ንቡረ እድ የሆነ፣ ከንጉሡም ዘንድ የተሾመ ነበረ፡፡ እርሱም ቤተ ክርስቲያንን አጠፋት፡፡ ምእመናንንም አሳዘናቸው፡፡ የተላከውም መልክተኛ ለአባታችን ይህንን ነገረው፡፡ አባታችንም ይህንን ሰምቶ «ኃጥእን እንደ አርዘ ሊባኖስ ከፍ ከፍ ብሎ አየሁት፤» ብሎ ተናገረ፡፡ ወደ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ ጮኸ፡፡ ያም በትዕቢቱ ሞትን አገኘ፡፡ ለቅዱሱም እንደ ሞተ ነገሩት፡፡ እርሱም «በተመለስኩ ጊዜ ግን አጣሁት» አለ፡፡ እርሱም «በምን ሞተ?» አላቸው፡፡ እነርሱም «ሌሎች አማልክትን ያመልክ ነበር» አሉት፡፡ ቅዱስ አባታችንም መራር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ «ፈለግኩ ቦታውንም አላገኘሁትም» አለ፡፡
አንዳንዶቹ ካህናተ ደብተራ ክህነትን ለእንጀራ ማግኛና ለክብር መሸመቻ እንጂ አምነውበት የሚያገለግሉበት አልነበረም፡፡ ርስት ጉልት ስላለ፣ በንጉሡ ማዕድ ለመቅረብ ስለሚያስችል፣ ልብስና መዓርግም ስለሚያሰጥ ነበር ወደ ክህነቱ የገቡት፡፡
ካህናተ ደብተራ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ለእንጀራና ክብር ማግኛ ብቻ እንጂ ለድኅነት ስለማይ ጠቀሙበት አንዳንድ ጊዜ ነገሥታቱን ከአምልኮ እግዚአብሔር ወደ ጥንቆላ ይከቷቸው የነበሩት እነርሱ ነበሩ፡፡ በዐፄ ዳዊት ዘመን አባ ጊዮርጊስ ሲከራከራቸው የነበሩትና በኋላም በንጽሕናው ምክንያት ተመቅ ኝተው ወደ ዳሞት እንዲጋዝ ያደረጉት በጥንቆላ ሥራ ተሠማርተው የነበሩት ካህናተ ደብተራ ነበሩ፡፡
ካህናተ ደብተራ በዕውቀትና በቅድስና የሚበልጧቸውን አባቶችና ሊቃውንት አይወዷቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለማበልጸግ፤ ለማደራጀትና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት የሚጥር ሁሉ ጠላታቸው ነው፡፡ ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ያዕቆብ አቡነ ፊልጶስን ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾመው ሲነሣ በዋናነት የተቃወሙት ካህናተ ደብተራ እንደነበሩ ገድለ አቡነ ፊልጶስ ይነግረናል «እንደዚህ አታድርግ፤ በአንድ ሀገር ሁለት ኤጲስ ቆጶስ ይሆናልን? ሕዝቡ ይከፋፈላል፤ የአንተም ክብርህ ይጠፋል፤ ምድረ ሼዋኮ ከፊል መንግሥት ናት፤ እንዴት እንደዚህ ትላለህ? ከኛ በኋላ የሚመጣ ትውልድም ይህንን አይፈቅድም፤ ከኛም አስቀድሞ እንዲሁ ነበረ፡፡ እኛስ ከኛ በፊት የነበሩ አበው ጳጳሳት ያላደረጉትምን አናደርግም፣ አንናገርምም» (ገድለ አቡነ ፊልጶስ፣ ገጽ 197)
በወቅቱ የነበረውን የደቡቡን ክፍል ከአሥራ ሁለት ከፍሎ አሥራ ሁለት ወንጌላውያንን የሾመውን በሰሜኑ ክፍልም ሐዋርያትን ያሠማራውን ግብፃዊውን አቡነ ያዕቆብን ካህናተ ደብተራ አልወደዱትም፡፡ የስብከተ ወንጌል መስፋፋትና የሕዝቡ ማወቅ ለእነርሱ የግብዝነትና የኃጢአት ሥራ ዕንቅፋት ይሆናል ብለው አሰቡ፡፡ በዚህም የተነሣ ይህንን የስብከተ ወንጌል አደረጃጀትና ሥምሪት ማጥፋት እንዳለባቸው ወሰኑ፡፡ በዚህም ምክንያት ዘአማኑኤል ንጉሡ አቡነ ያዕቆብን ወደ ግብጽ እንዲመልሰው መከረው፡፡ አቡነ ያዕቆብ ስላወገዘውም በለምጽ ተመትቶ ሞተ፡፡ አቡነ ያዕቆብም ወደ ግብጽ ተመለሰ፡፡
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የእውነተኞቹ አባው፣ ሊቃውንትና ካህናት አገልግሎትና ትሩፋት ለቤተ ክርስቲያን ብልጽግና እንዳይሰጥ ሲያሰናክሉና ለእውነት ዕንቅፋት ሲሆኑ የኖሩት ካህናተ ደብተራ ናቸው፡፡ እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር አብሮ እስከ መከር ይኖራልና የካህናተ ደብተራ ጠባይና አሠራር ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን ሲያውካት ይኖራል፡፡ እንደ አቡነ አሮን፣ እንደ አቡነ በጸሎተ ሚካኤል እንደ አቡነ ፊልጶስና እንደ አቡነ አኖሬዎስ ያሉ ጀግኖችን እስክታገኝ ድረስ፡፡click here for pdf