ሰላም ነው አዳሩ

ዝቋላ ካለፉት ቀናት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ ገደሉ ሥር ከሚታየው ጭስ በስተቀር ይህ ነው የተባለ የጎላ እሳት አሁን የለም፡፡ ከየአካባቢው የሄዱት ወጣቶች ከገዳማውያኑ እና ከአደጋ መከላከል ባለሞያዎች ጋር በቅንጅት ባደረጉት ተጋድሎ ገዳሙን ከአደጋ ታድገውታል፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢው ያለው ሙቀት ቀትር ላይ ሲጨምር የሚሆነው ባይታወቅም በአሁኑ ደረጃ ግን እሳቱ ከገደሉ በላይ እንዳይወጣ አካባቢውን የማጽዳት እና የእሳት መከላከያ የመሥራቱ ሥራ ተጠናክሯል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ አካባቢው ደርሰው አካፋ እና በመያዝ የመከላከሉን ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ እያገዙ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ወደ ገዳሙ ተጨማሪ ሰዎች እንዳይጓዙ አንዳንድ የአካባቢው ፖሊሶች የጣሉት እገዳ ግን በመነጋገር መፈታት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም በገዳሙ በቂ የሰው ኃይል አለ ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ ሥራው በፈረቃ እንዲሠራ ማድረግ እንጂ ከእሳቱ የባሰ ግርግር መፍጠሩ መልካም አይደለም፡፡