ለዝቋላ ነገ

በዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አሁን እሳት ሲነሣ እኔ እስከማውቀው ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ በሁለተኛው እሳት ጊዜ በምእመኑ እና በሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ታሪክ ከፍ አድረጎ ሲናገርለት የሚኖር ሥራ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ይህ እሳት ቢቻል ለሦስተኛ ጊዜ እንዳይነሣ፤ ከተነሣም ሥጋት በማይፈጥርበት መጠን እነዲሆን ለማድረግ ምን ይደረግ? የሚለው ወሳኙ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
አሁን የዝቋላ ገዳምን በተመለከተ ለዘለቄታው መሠራት ያለባቸው ዐሥር ጉዳዮች አሉ፡፡
1/ መልሶ መተካት
በእሳቱ የወደመውን ደን ተረባርበን ችግኝ በመትከል እና በማጽደቅ መመለስ አለብን፡፡ በተለይም መጭው ክረምት ከመድረሱ በፊት ይህንን ሥራ ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡

የመከላከያ ጉድጓዶች [Buffer trenches] በተጠኑ ስፍራዎች የመከላከያ ጉድጓዶች የሰደድ እሳት በሚነሣ ወቅት ከእንድ አቅጣጫ የተነሣው እሳት ወደሌላው በቀላሉ እንዳይዛመት እያነቀፉ ያስቀሩታል። ስለሆነም እነዚህ ጉድጓዶች ሁልጊዜ በላያቸው ላይ የሚበቅሉ ነገሮች እንዳይኖሩ መጠበቅ አለባቸው። የበቀሉ ካሉም በቀላሉ ማስወገድ ይገባል። ምክንያቱም እሳት በሚነሳ ጊዜ የበቀሉትን እንደመሸጋገሪያ እየበላ ከአንዱ ወደሌላው እንዲተላለፍ ስለሚረዳው ነው። ስለዚህ ከሥር ከሥር እየተከታተሉ ማረም ይገባል።

3/ ተንቀሳቃሽ የእሳት ማጥፊያ መሣሪያ [Fire Extinguisher] በበቂ ሁኔታ ሊኖራቸው ይገባል ይህም በካርቦን ዳይኦክሳይድ ወይም በእሳት ማጥፊያ ኬሚካል ዱቄቶች የተሞላ ሊሆን ይችላል። በየገዳማቱ እንደ ስፋታቸው መጠን እሳት ሲነሣ ወዲያውኑ ለማጥፋት እንዲቻል እነዚህን የመከላከያ መሣሪያዎች ማሠራጨት ያስፈልጋል።
4/ በቂ የጥበቃ ኃይል ማሠማራት ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የደኖቹ የጥበቃ ጉዳይ ነው። የተጠናከረ ጥበቃ የሚደረግ ከሆነ እሳት የሚያስነሱ አካላትን በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡

5/ የውኃ ማጠራቀሚያ
በገዳሙ ላይ እና ታች በቂ ውኃ ሊያጠራቅሙ የሚችሉ ቢያንስ ሁለት የውኃ ማጠራቀሚያዎች ያስፈልጉናል፡፡ በተለይ በክረምት ወቅት ዝናብ ከመጣ ውኃው ሊጠራቀም በሚችል መልኩ ማጠራቀሚያውን መገንባት ይገባል፡፡
6/ የውኃ ቱቦ እና ፓምፐር
በቅርቡ የተነሣውን አሳት ለማጥፋት ሥራውን ከባድ ካደረጉት ነገሮች አንዱ የውኃ እጥረት እና የተገኘውንም ውኃ ወደ ተራራው ለማውጣት ያለመቻል ነው፡፡ በመሆኑም ለወደፊቱ ከታች የተጠራቀመውን ውኃ ወደ ላይ ለመውሰድ የሚያስችሉ የውኃ ቱቦዎች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ የውኃ ቱቦዎችም ውኃው ከታች ወደ ላይ ለመውጣት እንዲችል የውኃ መግፊያ መሣርያ ያስፈልገናል፡፡ እነዚህን መሣርያዎች በባለሞያ ተረድተን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
7/ የማጥፊያ መሣርያዎች
በአሁኑ የእሳት ማጥፊታ ተጋድሎ ወቅት አንዱ ችግር ለእሳት ማጥፊያ የሚሆኑ መሣርያዎች በአካባቢው ያለመገኘታቸው ነው፡፡ ለወደፊቱ ይህ እንዳይደገም በገዳሙ የዕቃ ግምጃ ቤት ተሠርቶ እንደ አካፋ፣ዶማ፣ በአደጋ ጊዜ ሊለበሱ የሚችሉ የመከላከያ ልብሶች፣የውኃ ማማላለሻ ዕቃዎች፣ ወዘተ እንዲቀመጡ ቢደረግ፡፡
8/ መንገድ
እኔ ያነጋገርኳቸው የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሀብቶች ሁሉ የእሳት አደጋ መካከያ መኪኖችን እና የውኃ ማመላለሻ ቦቴዎችን ለመስጠት ፈቃደኞች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መንገዱ ለዚህ አመቺ አይደለም፡፡ በመሆኑም በገዳሙ የአደጋ ጊዜ መግቢያ አመቺ መንገድ መሠራት ይገባዋል፡፡ ምናልባት ወደ ገዳሙ በመኪና መግባት የማያስፈልግ ከሆነ እንኳን በአደጋ ጊዜ ብቻ ለመጠቀም በሚሆን መልኩ ተዘግቶ ቢቀመጥ መልካም ነው፡፡
9/ ሥልጠና
ለገዳሙ ለሚገኙ ገዳማውያን የአደጋ ጊዜ ሁኔታዎች ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እሳት ሊነሣ ሲል እንዴት ማወቅ እንደሚቻል፡፡ እንዴት መከላከል እንደሚገባ፤ እንዴት እና ለማን መረጃ መስጠት እንዳለባቸው፡፡ በአደጋው ሰው ቢጎዳ ምን ማድረግ እነደሚገባ፤ ሥልጠና መሰጠት አለበት፡፡
10/ ተቆጣጣሪ ግብረ ኃይል  በየጊዜው የቃጠሎ ስጋት ያለባቸውን ገዳማት የሚቃኝ እና የቅድመ መከላከል ሥራውን የሚመራ አንድ አካል ማቋቋም። በሚከሰቱት አደጋዎች የሚያልቀው እልቂት በዘመናት የማይተኩ ውድ የሀገር ሀብቶች ከመሆናቸው አንጻር ቋሚ አካል መኖሩ ያስፈልጋል። ይህ አካል ገዳማቱን እያስተባበረ ሥልጠና እየሰጠ የሥራ መርሐ ግብር አያወጣ በማዕከላዊነት ገዳማቱን የሚረዳ ሊሆን ይገባዋል። የእስቸኳይ ጊዜ ሥራ እና መደበኛ የመከላከል ሥራ መለየት አለበት፡፡