ከጎላ ወደ ዝቋላ
ዓለማየሁ ደንድር ከጎላ ሚካኤል በፌስ ቡክ እንደ ተረከው
የዝቋላ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም አባታችን አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ብዙ ገድላትን የተጋደሉበት ጥንታዊ ገዳም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሄ ገዳም ዙሪያውን በደን የተሸፈነ ገዳም ነው ፡፡ ሰሞኑን ታዲያ አንድ አስደንጋጭ ዜና ሰማን፡፡ የገዳሙ ደን በእሳት ተያይዞ እየነደደ እንደሆነ እና ይሄንን እሳት ተረባርበን ማስቆም ካልቻልን ብዙ ዘመናት ተጠብቆ የቆየውን ገዳማችንን በጥቂት ሰዓታት ልናጣው እንደምንችል ተነገረን፡፡
እኔ ይሄንን ዜና የሰማሁት ከሚዲያ ሳይሆን ከዲ.ዳንኤል ክብረት ብሎግ «ክተት ወደ ዝቋላ » ብሎ በጻፈልን ጽሑፍ ነው ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የፌስ ቡክ ገጾች በዚህ ዜና ተጥለቀለቁ፡፡
ታዲያ በሕዝበ ክርስቲያኑ ወዲያው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀመረ የተደናገጠው የአዲስ አበባ ወጣት፣ ምዕመናንና የፌዴራል ፖሊስ ጉዟቸውን ወደ ገዳሙ አደረጉ ፡፡ ወደዚያው ያቀኑት ወጣቶችና ምዕመናን እሳቱን ለማጥፋት ደፋ ቀና ማለት ጀመሩ ፡፡ ብዙዎቹ በድንጋጤ ወደ ገዳሙ ይሂዱ እንጂ በቂ መሣሪያና ለራሳቸው የሚሆን ስንቅ እንኳን አልያዙም ፡፡ አሁንም የተለያዩ ብሎጎችና የፌስቡክ ገጾች ይሄንን ዜና ይዘው ወጡ ፡፡ ስንቅና ውሃ አካፋና ዶማ ተይዞ እንዲኬድ ጥሪው ተላለፈ ፡፡
ማክሰኞ መጋቢት 11፡– ወደ 40 የምንጠጋ የጎላ ሚካኤል አካባቢ ወጣቶችና የፍኖተብርሃን ሰ/ት/ቤት አባላት ገዟችን ወደ ዝቋላ ለማድረግ ተነሳን ፡፡ ወደ ገዳሙ መሄድ ብቻ ሳይሆን ቀድመው ለሄዱት ወንድሞች ስንቅ ውሃ እና እነ አካፋና ዶማ የመሣሠሉትን ይዞ መሄድ አስፋላጊ በመሆኑ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጀመረ ፡፡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከጠበቅነው በላይ ገንዘብ አገኘን ለዚህም ዋነኛዎቹ በጎ አድራጊዎች ከጥቁር አንበሳ እስከ ተ/ሃይማኖት ያሉት የመኪና መለዋወጫ ሱቆች፣ ካፌዎች እና ግለሰቦች ነበሩ ፡፡
በተገኘው ገንዘብ ምግብ ውሃና አስፈላጊ መሣሪያዎች ተይዞ ፣ከቀኑ 8፡00 ላይ የመኪና ጉዞ ተጀመረ ፡፡ በመኪና ጉዟችን የአዲስ አበባን ከተማ ጥለን በደብረ ዘይት በኩል ታጥፈን የአካባቢው ሰዎች ድሬ ብለው በሚጠሯት መንደር መኪናችን ሳናስበው ቆመች፡፡ ከፊት ለፊታችን እንደኛው 5 ሚኪናዎች ቆመዋል ፡፡ ከመኪናችን ወርደን ስናጣራ የኦሮሚያ ፖሊስ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ማለፍ እንደማንችል ነገረን፡፡ ከየመኪናችን ሁለት ሁለት ተወካይ ልከን ከኮማንደሩ ጋር እንዲያወሩ ቢደረግም ምንም ለውጥ ሊመጣ አልቻለም ፡፡ ማለፍ የተከለከለው የ6 መኪና ወጣት ግብግብ ከመፍጠር ቀድሞ ፈጣሪን መጠየቅ ይሻላል በሚል አርቆ አሳቢነት አካባቢው ላይ በሚገኝ ሜዳ ላይ ጸሎት ተጸለየ ፡፡ ከጸሎት በኋላ አንድ ወሬ ተሰማ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቦታውን ለመቅረጽ ከመጡ ጋዜጠኞች ጋር ጋር እሳቱ ሳይጠፋ ጠፋ ብላችሁ በሚዲያ አስነግራችኋል በማለት በተፈጠረው ውዝግብ ላይ አንድ የ4ኛ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ በሚሊሻ ታጣቂዎች በጥይት መመታቱ ተሰማ ፡፡
በዚህን ጊዜ ወጣቱ ከፍርሃት ይልቅ ምናልባት አቡዬ የጠሩን ለሰማዕትነት ሊሆን ስለሚችል ጉዟችንን በእግር ማድረግ አለብን በማለት ማታ 12፡00 ላይ የእግር ጉዞውን ተያያዝነው 3 የድሬ አካባቢ ሕጻናት እንመራችኋለን ብለው ፊት ፊት በመሄድ ተባበሩን ፡፡በእርግጥ ጉዞው በጣም አድካሚና ውጣ ውረድ የበዛበት ቢሆንም የነበረው ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ አንድነት የጉዞውን ድካማ አስረስቶናል ፡፡ 12፡00 ሰዓት የጀመርነው የእግር መንገድ ከሌሊቱ 8፡30 /ለ8፡30 ተጉዘን / ወደ ገዳሙ ለመድረስ ችለናል ፡፡ በዚህ አድካሚ ጉዞ ውስጥ አስገራሚው ነገር የእኛ የወጣቶች መሄድ ሳይሆን በሌላ መኪና የነበሩት ሴቶች፣ እናቶችና፣ ማየት የተሳናቸው ጭምር የዚህ ጉዞ ተካፋይ መሆናቸው ነው ፡፡
ምንም እንኳን ሌሊት 8፡30 ወደ ገዳሙ ብንደርስም ለ8 ሰዓታት በመጓዛችን የተነሳ እሳቱ ወዳለበት ቦታ ለመሄድ አቅም አጠረን ፡፡ ከኛ ቀድሞ የሄደው ሕዝብ ግን እዛው አድሮ እሳቱን በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ተነገረን ፡፡ ለ3 ሰዓታት ያክል በገዳሙ ጊቢ በየጥጋጥጉ ተደራርበን ተኛን ፡፡
ሌሊት 12፡00 ሰዓት ከእንቅልፍ በመነሳት እሳቱ ወዳለበት ቦታ አመራን፡፡ እሳቱ በደኑ ላይ ብዙ ሊባል የሚችል ጉዳት አድርሷል ፡፡ ምናልባት የሕዝቡ ርብርብና የእግዚአብሔር ረዳትነት ባይኖር ኖሮ ወደ ገዳሙም ሊሻገር ይችል ነበር ፡፡ በቦታው ስንደርስ በጣም ብዙ ወጣቶችና የፌዴራል ፖሊሶች እሳቱን በማጥፋት እና ድጋሚ ቢነሳ እንዳይዛመት የቀድሞ መከላከል ሥራውን ተያይዘውት አገኘናቸው ፡፡ እኛም በአፋጣኝ ወደ ሥራው ተቀላቀልን እሳት ወዳለበት ቦታ በመሯሯጥ አጥፍተን ቆርጠን ወደ ሌላ ቦታ ማምራት፤ አንድ ቦታ ላይ እሳት ሲታይ በፉጨት እየተጠራራን ያ ሁሉ ወጣት ይዘምትበታል / ለካ ለእሳትም እሳት አለው / በዚህ ረገድ የፌዴራል ፖሊስ አስተዋዕጾ ከመጠን በላይ ሊያስመሰግናቸው ይገባል ፡፡
4 ቀን ሙሉ ምግብ ሳይመገቡ /በዛ ላይ ብዙዎቹ ጿሚዎች ናቸው / ከወጣቱ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ ሲሰሩ ተስተውሏ፡፡ እንደውም ከተማ ላይ ለነሱ የነበረንን የተሳሳተ አመለካከት አስቀይረውናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን እሳቱ ጠፍቷል የሚባልበት ደረጃ ላይ ደረስን ፡፡ ጠፍቷል ስንል አይነሳም ማለታችን ግን አልነበረም ሰው ላይደርስበት የሚችሉ ገደሎች ነበሩ ምናልባት ድጋሚ እንዳያስነሳ ስጋት አሳድሯል ፡፡ ምናልባት አንድ ጊዜ በሄሊኮፕተር ርምጃ ቢወሰድበት ስጋቱን ሊቀንሰው ይችላል፡፡ የእሳቱን መጥፋት ካረጋገጥን በኋላ ከፌዴራል ፖሊሶች ጋር በመሆን ወደ ገዳሙ አመራን ፡፡ በገዳሙ አዳራሽ የሚቀመሰውን ቀማምሰን ከፖሊሶቹ ጋር አዲስ አበባ ላይ ለመገናኘት ተቃጥረን የመልስ ጉዟችንን ጀመርን ፡፡
እኛ ስንመለስ እኛን የሚተኩ ብዙ መኪኖች በመምጣት ላይ ነበሩ ፡፡ መኪናችን በባዶው እንዲመጣ ስለተፈቀደለት ሐሙሲት ጋር ጠብቆን ወደ አዲስ አበባ ገሰገስን ስንሄድ በድንጋጤና በጭንቀት የነበረው ወጣት አሁን ፊቱ ፈክቶ መቀላለድ ጀምሯል ፡፡ ቀልድ ሲባል ደግሞ ቀልድ እንዳይመስላችሁ /ድሮስ የጎላ ልጅ አይደልን/ ፡፡ ለኔና ለአንድ ጓደኛችን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚል ስም ወጣልን /ስልካችን እንዴት እንደወደቀ ሳናውቀው ስለጠፋብን በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ፡– እሳቱንም ስልካችንንም አጥፍተን መምጣታችን መሆኑ ነው/፡፡
ለኛ ግን ደስታው ወደር አልነበረውም ፡፡ አንድ አካባቢ ሆነን የማንግባባ፣ የማንነጋገር ሁሉ የሚገርም ፍቅር ሸምተን መጣን ፡፡ እንደውም አንድ ጓደኛችን ሲናገር « አቡዬ በዚህ እሳት አመካኝተው እኛን ሰብስበውናል ፤ የሌለ የሚመስለውን ፍቅር፣ የተከፋፈለ የሚመስለውን አንድነት እና ሕዝበ ክርስትያኑ ምን ያህል ለሃይማኖት እንደሚቆም ለማሳየት ፈልገው ነው » ያለውን ንግግር አልረሳውም ፡፡፣
እግዚአብሔር አምላክ ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን ፡፡ አሜን ፡፡
የአክብሮት ምስጋና ፡– ለዲ.ዳንኤል ክብረት / ከሰባኪነት ወደ ጋዜጠኝነት /፣ የአካባቢያችንን ወጣቶች እንድንነሳሳ ትልቁን ማስተባበር በብቃት ለተዋጣው ለዳዊት ፣ ለአካባቢያችን ስፔርፓርቶች፣ ለፌዴራል ፖሊሶች፣ ምንም እንኳን ክርስቲያናዊ ግዴታቸው ቢሆንም ከነሱ አልፎ ሌላውን በማነሳሳታቸው ሊበረታቱ ይገባል ፡፡