ትዝብት

click here for pdf

ደንበኛ ንጉሥ ነው፤ የት?
ጎንደር አንድ ሻሂ ቤት ተቀመጥን፡፡ አዘዝን፡፡ አልመጣም፡፡ ደግመን አዘዝን፡፡ አልመጣም፡፡ በኋላ ያዘዝናትን ልጅ ጠራንና «ተውሽንኮ» አልናት፡፡ አንገቷን ሰበቅ አደረገችና «ከቸኮልክ ማትሄድ» አለችን፡፡ ምን ይደረግ የፋሲልን እና የቴዎድሮስን ንግሥና እንጂ የደንበኛን ንግሥና ከማታውቅ ልጅ ብዙም መጠበቅ የለብንም ብለን ተውነው፡፡
አዲስ አበባ መገናኛ ካለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሦስት ጊዜ ሄድኩ፡፡ ከድሬዳዋ የተላከ ገንዘብ ልወስድ፡፡ ሦስቴም አልደረሰም ተባልኩ፡፡ በተላከ በሦስተኛ ቀኑ፡፡ እዚያ ድሬዳዋ ስደውል ደግሞ ተልኳል ይሉኛል፡፡ ታድያ ምን ላድርግ? «በቃ የላከልህ ሰው ባንክ ሄዶ ይደውልልን» አሉኝ፡፡ ምን አደርጋለሁ ብዬ እንዳሉት አደረግኩ፡፡ በእኔው ስልክ ተደዋውለው ሰጡኝ፡፡ ለስልክ ግን የላከልኝ ሰው ከፍሏል፡፡ የባንኩ ደንበኛ መሆኔ ቀርቶ የባንኩ ሠራተኛ ሆኜ በስልኬ እየደወልኩ መረጃ ሳቀባብል ቆየሁ፡፡
እዚህም ደንበኛ ንጉሥ አይደለም፡፡ ንጉሥን ደርሶልሃል ብለው ይጠሩታል፤ ሲመጣም አረፍ በል ብለው ያስተናግዱታል እንጂ በራስህ ስልክ ደውለህ ገንዘብክን አስመጣ አይሉትማ፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ እዚያ የመጻሕፍት መሸጫ መደብር አላቸው፡፡ ሁለት መጽሐፍ እገዛ ዘንድ ፈለግኩ፡፡ አንዱን ገዛሁ፡፡ ሁለተኛውን ግን «ሻጩ የለም» ተባልኩ፡፡  
«የሥራ ሰዓት አይደለም ወይ አልኩ 
 «ሻሂ ሊጠጣ ሄዶ ነውና ጠብቀው» አሉኝ፡፡ 
 ምን ያህል ሰዓት አልኩ፡፡ «አንድ ሃያ ደቂቃ፡፡»
«የሥራ ሰዓታችሁ ከስንት እስከ ስንት ነው አልኩ፡፡  
«እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል» ተባልኩ፡፡  
«ታድያ ምነው ይህቺን ሰዓት እንደማታስተናግዱ ማስታወቂያችሁ ላይ አልጠቀሳችሁም? ወይም ሌላ መንገድ አልፈለጋችሁም» ብዬ ጠየቅኩ፡፡ () መልሱ የለም፡፡ እዚህ ትልቁ የትምህርት ተቋም ውስጥም ደንበኛ ንጉሥ አይደለም፡፡ ንጉሥ ቢሆንማ ለሻሂ የሄደ አገልጋዩን ሃያ ደቂቃ እንዲጠብቅ አይደረግም ነበር፡፡ ያውም ሊከፍል እንጂ ሊከፈለው ያልመጣ ንጉሥ፡፡
እኔ እስካሁን ደንበኛ ንጉሥ ሆኖ በትክክል ያየሁት ቀብር አስፈጻሚዎች ነው፡፡ እዚያ በክብር ይሸከሟችኋል፡፡ ይገንዟችኋል፡፡ መኪና ውስጥ ያስገቧችኋል፡፡ በመኪናቸው ሲወስዷችሁም አያንቀዠ ቅዧችሁም፡፡ በወታደራዊ ተጠንቀቅ ያጅቧችኋል፡፡ በኋላም ተሸክመው መቃብር ያደርሷችኋል፡፡ ከዚህ በላይ ለንጉሥ ምን ይደረግለታል?
እናም እንዲህ አሰብኩ፡፡ እዚህ ሀገር ደንበኛ ሆኖ ንጉሥ ለመሆን የግድ መሞት ያስፈልጋል ማለት ነው?