የዴር ሡልጣን ጥሪ
በኢየሩሳሌም የጥንቷ ከተማ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጲላጦስ አደባባይ እስከ ጎልጎታ የተጓዘበት መንገድ አለ፡፡ ፍኖተ መስቀል ይባላል፡፡ ይህ መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበላቸውን አሥራ አራቱን ሕማማት የምናስታውስበት መንገድ ነው፡፡ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት የሚመጡ መንገደኞች ሁሉ በእያንዳንዱ ምእራፍ እየቆሙ ጸሎት በማድረስና በቦታው ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ በማሰብ እስከ ጎልጎታ የትሣኤው ቤተ ክርስቲያን ይደርሳሉ፡፡
በዚህ መንገድ የሚጓዝ ተሳላሚ ዘጠነኛው ምእራፍ ላይ ሲደርስ አንድ አስደናቂ ነገር ያያል፡፡ በጎልጎታ የሚገኙ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች ሁሉ በነጮች የተያዙ ናቸው፡፡ በቦታው የሚታዩት መነኮሳትም ነጮች ብቻ ናቸው፡፡ የኢየሩሳሌም ተሳላሚ ጥቁር አፍሪካውያንን የሚያየው ዘጠነኛው ምእራፍ ላይ ሲደርስ ነው፡፡ በዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ገዳም፡፡
ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም መጓዝ የጀመሩት ገና ክርስትና ሳይሰበክ መሆኑን የሐዋርያት ሥራን የጻፈልን ቅዱስ ሊቃስ በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጉዞ አረጋግጦልናል፡፡ ከዚያም በኋላ በተለይም ክርስትና የሀገሪቱ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በአራተኛው መክዘ ሲታወጅ አያሌ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም ለተሳላሚነት ይሄዱ ነበር፡፡ እነዚህ ክርስቲያኖች በተሳላሚነት መጓዝ ብቻ ሳይሆን በዚያ በሚገኙ ቅዱሳን መካናት ገብተው በምናኔ ይኖሩ እንደነበር በቤተልሔም ለብዙ ዓመታት የኖረውን አባ ሄሮኒመስን (ጄሮም) (347–420) ጨምሮ ብዙ የታሪክ ጸሐፍት መስክረዋል፡፡
የዐፄ ገብረ መስቀል ወንድም (አንዳንዶች ልጅ ይላሉ) ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘው በዚያው ከመነኑት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበር፡፡ ይህ «ሙሴ አል ሐበሽ» ተብሎ የሚጠራው ኢትዮጵያዊ በተለይም በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ውስጥ ታላላቅ ሥራዎች ከሠሩ አበው አንዱ መሆኑን የሶርያ ቤተ ክርስቲያን መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በእርሱ ስም የተቋቋመው የመናንያን ገዳም ከደማስቆ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከናብክ ከተማ አጠገብ ይገኛል፡፡
ከዐፄ ገብረ መስቀል በፊት ነግሠው በሀገረ ናግራን ዘመቻ ዝናቸው በመላው ዓለም የናኘው ዐፄ ካሌብም ከዘመቻው መልስ ዘውዳቸውን ወደ ኢየሩሳሌም የጌታ መቃብር ልከው ነበር፡፡ ይኼው ዘውዳቸው ከጎልጎታ ተሰርቆ ቤተ ልሔም በሩሲያውያን እጅ እንዳለ ይሰማል፡፡
![]() |
| «ሙሴ አል ሐበሽ» ገዳም |
በመስቀል ጦርነት ጊዜ ብዙ ዓረቦች እየተሰደዱ ወደ ኢትዮጵያ በመግባታቸው ንጉሥ ላሊበላ እና ቅድስት መስቀል ክብራ እየተቀበሉ አስተናግደዋቸው ነበር፡፡ ሳላሕ ዲን የተባለው የዓረቦች ጦር መሪ ሮማውያን ድል አድርጎ ኢየሩሳሌምን በያዘ ጊዜ ለዚህ ውለታቸው ብሎ የጎልጎታን የጌታ መቃብር፣ የቤተ ልሔምን ቤተ ክርስቲያን እና እሌኒ መስቀል ያወጣችበትን የመስቀሉን ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያውያን ሰጥቷቸው ነበር፡፡
እነ ቅዱስ ላሊበላ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ፣ አቡነ እዝራ፣ እና ሌሎችም ቅዱሳን ኢየሩሳሌም መጓዛቸውን ገድሎቻቸው ይተርኩልናል፡፡ በገድለ ዜና ማርቆስ ደግሞ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዙ የኢትዮጵያ መነኮሳት እና በመለካውያን መካከል ተደርጎ የነበረውን የሃይማኖት ክርክር በዝርዝር ይተርከዋል፡፡ በገድለ አቡነ እዝራም የኢየሩሳሌም መንገደኞች ይደርስባቸው የነበረውን መከራ እና እንግልት እናነባለን፡፡
በ1614 እኤአ ኢየሩሳሌምን ተሳልሞ የጻፈው ጣልያናዊ ተሳላሚ «በጎልጎታ ያለው የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በደብረ ጽዮን የሚገኘው የዳዊት ዋሻ፣ በቤተ ልሔም የሚገኘውም መቅደስ በኢትዮጵያውያን እጅ ነው» ብሎ ጽፎ ነበር፡፡
ሌላው ፈረንሳዊ ተሳላሚ ቻርለስ ፊሊፕ እንደሚለው «በጎልጎታ የሚገኙት የማርያም መግደላዊት፣ የቅዱስ ሚካኤል፣ የቅድስት ድንግል ማርያም፣ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እና የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ መቅደሶች የኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡»
የኢትዮጵያውያን ኃይል በኢየሩሳሌም እየተዳከመ የሄደው ቱርኮች ኢየሩሳሌምን ከያዙ በኋላ ነው፡፡ በአንድ በኩል የቱርክ ሁለተኛ ዜጎች ሆነው የመጡት ግሪኮች እና አር መኖች የኢትዮጵያውያንን ርስት ወሰዱ፡፡ በሌላ በኩል በቱርኮች እና በኢትዮጵያ መካከል ተደጋጋሚ ጦርነቶች በመደረጋቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ለመግባት አዳጋች ሆነባቸው፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ የዘመነ መሳፍንት የርስ በርስ ጦርነት ነገሥታቱ ለቅዱሳን ከማናት ይሰጡት የነበረውን ድጋፍ አስቆመው፡፡
![]() |
| የዴር ሡልጣን ገዳም |
እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ እና የኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች እና መነኮሳት ቁጥር ሲቀንስ ቦታዎቻችንን ሌሎች እየወሰዱት ሄዱ፡፡ የመጨረሻውን የዴር ሡልጣን ርስት ደግሞ ግብጾች አብዛኛውን ሥፍራ ነጠቁን፡፡ በተለይም በ1838 እኤአ በኢየሩሳሌም ገብቶ በነበረው ወረርሽኝ ብዙ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት አለቁ፡፡ በዚህ ወቅት የኢየሩሳሌምን ከተማ በቱርኮች ሥር ሆነው የሚያስተዳድት ግብጾች ነበሩ፡፡ ይህንን አጋጣሚ ያገኙት ግብጻውያን መነኮሳትም እኛ የኢትዮያ ቤተ ክርስቲያን ጠባቂ ነን ብለው ቦታውን ተረከቡት፡፡ በገዳሙ የነበሩ መዛግብትንም አቃጠሏቸው፡፡
ከወረርሽኙ በኋላ የመጡት አበው ዋናው የዴር ሡልጣን ቦታቸው በግብጾች ተነጥቆ፣ ሌላውንም ሌሎች ተቀራምተውት ደረሱ፡፡ መጠጊያ ሲያጡም በእሌኒ የመስቀል ቤተ ክርስቲያን ጣራ ላይ ከጭቃ መጠለያ እየሠሩ ተቀመጡ፡፡ ኢትዮጵያውያን አበው ሰሚ እያጡ፣ እየተደበደቡ እና እየተባረሩ፤ እየታሠሩ እና እየተገደሉ አብዛኛውን ርስታቸውን ቢነጠቁም የቀረችውን ለማትረፍ ግን ባለ በሌለ ኃይላቸው ተጋድለዋል፡፡
በዚህ ዘመን ቅዱሳን ቦታዎችን ይዘው የነበሩት ግብጾች እና አርመኖች በኢትዮጵያውያን ላይ ያደርሱት የነበረውን ግፍ እና መከራ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚሲዮናዊነት ያገለገለው እንግሊዛዊው ሳሙኤል ጎባት ሲገልጠው «ኢትዮጵያውያን አስተዋዮች እና የተከበሩ ናቸው፤ ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም እንደ ባሮች ነበር የሚታዩት፡፡ በተለይም አርመናውያን እና ግብጾች እንደ አራዊት ይቆጥሯቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን አርመኖች ደስ ካላላቸው በቀር ወደ ራሳቸው መቅደስ እንኳን ለመገባት መብት አልነበራቸውም፡፡ አንድ ጊዜ እንዲያውም ላረፈ ለአንድ አባላቸው ፍትሐት እንዳያደርጉ መቅደሳቸው በአርመኖች ተዘግቶባቸው ነበር፡፡ የበሮቻቸው ቁልፎች በጨቋኞቻቸው እጆች ነበሩ፡፡ ሲመሽ ይዘጉባቸውና አንዱ ደስ ያለው ግብጻዊ መጥቶ ጠዋት እስኪ ከፍትላቸው ይጠበቁ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ አንዳች የጤና እክል ቢደርስባቸው እንኳን ከመኖርያቸው ወጥተው ወደ ሕክምና ለመሄድ እድል አልነበራቸውም»
በ1850 አካባቢ በኢየሩሳሌም የእንግሊዝ ቆንስላ የነበረው ጄምስ ፊን ስለ ኢትዮጵያውያን አባቶች መከራ ሲገልጥ «የአርመኑ ሊቀ ጳጳስ ድኾቹን ኢትዮጵያውያን ያሰቃያቸው ነበር፡፡ ይገርፋቸዋል፤ በሠንሠለት ያሥራቸዋል፤አልፎ አልፎ ካልሆነም በቀር ወደ ቤተ መቅደሳቸው መግባትን ይከለክላቸዋል» ብሎ ነበር፡፡
ይህንን የመሰለው የመነኮሳቱ መከራ ነበር ዐፄ ቴዎድሮስን ኢየሩሳሌም ተጉዘው የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበር እንዲመኙ ያደረጋቸው፡፡
ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሣ ብሎ ስም
ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም ያስባሉትም ለዚህ ነበር፡፡ ራሳቸውም ሲፎክሩ «የኢትዮጵያ ባል የኢየሩሳሌም እጮኛ» ይሉ ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ያሰቡት ሳይሳካ መቅደላ ላይ ዐረፉ፡፡ ዐፄ ዮሐንስ ከቱርክ በማረኩት አራት ሺ ብር የደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረትን ሥራ አስጀመሩ፡፡ ንጉሥ ምኒሊክም አስፈጸሙ፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ እና እቴጌ ጣይቱ ሕንፃ ገዙ፡፡ እቴጌ መነን የቅድስት ሥላሴን ቤተ ክርስቲያን አሠሩ፡፡ እነ አፈ ንጉሥ ነሲቡ፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ፣ እነ ወይዘሮ አማረች ዋለሉ እነ ወይዘሮ በየነች ገብሩ፣ እነ ወይዘሮ አታየ ወርቅ የየራሳቸውን ሕንፃ እና ቦታ እየገዙ ገዳማቱን አጠናከሩ፡፡
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል መንገድ ተጉዘው ዘጠነኛው ምእራፍ ሲደርሱ እነዚህን ሁሉ እንዲያስታውስዎት የሚያድርግ አንዳች አሳዛኝ ነገር ያያሉ፡፡ ያሉበት ሀገር እሥራኤል መሆኑንም ይጠራጠራሉ፡፡ የቀሞሙበት ዘመን ሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን መሆኑን ለማረጋገጥም የዘመን መቁጠርያ ያስፈልግዎታል፡፡ ቁመታቸው አንድ ሜትር ተኩል እንኳን የማይሞላ፣ ስፋታቸው ከሁለት ካሬ ሜትር ያነሱ፣ ከጭቃ የተሠሩ ታናናሽ ቤቶችን ያያሉና፡፡ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠሩት እነዚህ የጭቃ ቤቶች ቁጥራቸው ሃያ ስድስት ሲሆን ሁለት መቅደሶችንም ይጨምራሉ፡፡ መስኮቶቻው አየር እንጂ ሰው አያሳልፉም፡፡ አንዳንዶች ተሰነጣጥቀዋል፡፡ አንዳንዶች ጠቋቁረዋል፡፡ ሌሎች ተፈነቃቅለዋል፡፡ በተለይም ሁለቱ መቅደሶች ለመፍረስ የሚጠብቁት ቀናትን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዓመት በእሥራኤል የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሞያዎች የተደረገ ጥናት «ገዳሙ እና በመስቀሉ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያለው አደባባይ የመደርመስ አደጋ ተጋርጦበታል»፡፡
የመጸዳጃ ቤቱ ለአንድ ደቂቃ በአካባቢው አያስቆማችሁም፡፡ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ግን ዓመቱን ሙሉ በአካባው ይኖራሉ፡፡ በገዳሙ የውኃ ችግር አለ፡፡ ሁሉም ነገር አርጅቶ መውደቁን ብቻ ይጠብቃል፡፡ በበጋው ማቀዝቀዣ በክረምቱም ማሞቂያ የላቸውም፡፡ የመብራቱ ገመድ እዚህም እዚያም ተቆራርጧል፡፡ ለምን?
ግብጻውያን የወሰዱት የዴር ሡልጣን ቦታ አልበቃቸውም፡፡ የዴር ሡልጣንን ይዞታ በሙሉ መጠቅለል ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም የተነሣ የይገባኛል ጥያቄ በየጊዜው ያነሣሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ገዳሙን እንዳይጠግኑ የእሥራኤል መንግሥት ይከለክላል፡፡ የእሥራኤል መንግሥት እንዲጠግነው ሲጠየቅ ደግሞ ኢትዮጵያውያን እና ግብጻውያን መጀመርያ ይስማሙ ይላል፡፡ በመካከሉ የዴር ሡልጣን ገዳም ሕልውና እያከተመ ይመስላል፡፡
እዚያ ያሉ አባቶች በየጊዜው ይደበደባሉ፡፡ ግብጻውያን የበሮቹን ቁልፎች ሊቀይሯቸው ይችላሉ ብለው በመሥጋት ሌት ተቀን ዕንቅልፍ የላቸውም፡፡ የሚያዩትን ሁሉ በንቃት እና በጥርጣሬ ይከታተላሉ፡፡ የተነጠፈን ምንጣፍ ማንሣት፣የተሰበረን ወንበር መቀየር፣ የተበላሸን ዕቃ መጠገን ያስከስሳቸዋል፡፡
ቤተ ክህነቱ ለዴር ሡልጣን ተገቢውን ቦታ አልሰጠውም፡፡ ግብጻውያን በሲኖዶስ ደረጃ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ ሲኖራቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግን ጉዳዩን በቦታው ላሉ አባቶች ብቻ ትታዋለች፡፡ በፓትርያርኮች ደረጃ ግንኙነት ሲጀመርም የዴር ሡልጣን ጉዳይ አይነሣም፡፡ ችግሩን ለመፍታት የሚደረግ ጥረትም የለም፡፡ የእሥራኤል መንግሥትን የመግፋት እና ጫና የማሳደርም እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ ቤተ ክህነቱ ቢያንስ የባለቤትነት ውይይቱ ቀርቶ እድሳቱን የተመለከተ ውይይት እንኳን ማድረግ አልቻለም፡፡
ይህ ሁኔታ ለግብጻውያን የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል፡፡ ቦታውን ባለቤት አልባ አድርገው እንዲቆጥሩትም አድርጓቸዋል፡፡ በቅርቡ ዴር ሡልጣን እንዲታደስ ለመወትወት የተቋቋመው ኮሚቴም ከመንግሥት ያገኘውን ድጋፍ ያህል ከቤተ ክህነቱ አላገኘም ይባላል፡፡
እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ብቸኛውን የጥቁር አፍሪካውያን የጎልጎታ ርስት ዴር ሡልጣንን ወደ ፍርስራሽነት ሊቀይሩት ቀናት ቀርቷቸዋል፡፡ እነሆ ይህንን በምጽፍበት ሰዓት እንኳን የተወሰነው የሕንፃው ክፍል በመሰንጠቅ ላይ ይገኛል፡፡ ግብጾች በጥንቱ ቦታችን ከከፍታ ላይ ሆነው «እስኪ ምን እንደ ምታmጡ እናያለን?» በሚል ስሜት ያዩታል፡፡ ቤተ ክህነቱ አዲስ አበባ ሆኖ ረስቶታል፡፡ ኢትዮጵ ያውያንም ለትንሣኤ መጥተው ተሳልመውት ይሄዳሉ፡፡ ዴር ሡልጣን ግን በውስጡ ያለፉትን ቆራጥ አባቶች ብቻ እያስታወሰ «ነበር» ለመሆን እየተቃረበ ነው፡፡
ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ
ዴር ሡልጣን፣ ኢየሩሳሌም

