የነፍሴ ጨዋታ

ትናንት ማክሰኞ ማታ በእግር ኳስ ታሪክ አስገራሚ ከሚባሉት ጨዋታዎች አንዱን ተመለከትን፡፡ ስለ እግር ኳስ ልቡን ሞልቶ ማንም ቀድሞ መናገር አይችልም የተባለውን ብሂል ያረጋገጠ ነበር የባርሴሎናና የቼልሲ ጨዋታ፡፡
የዓለም ቁጥር አንድ ቡድን ከእንግሊዝ ስድስተኛ ቡድን ጋር ተጋጥሞ፣ ሰባ በመቶ የኳስ ቁጥጥር የነበረው ቡድን ሠላሳ በመቶ ኳስን በያዘ ቡድን ተሸንፎ፤ ከአራት በላይ አጥቂ ያሰለፈ ቡድን በአንድ አጥቂ ተበልጦ፤ ያጠቃ ቡድን በተከላከለ ቡድን ድል ተመትቶ ያየንበት ጨዋታ ነበር፡፡ የትናንቱ ጨዋታ፡፡
  ከጨዋታው በፊት ባርሴሎና ቼልሲን በኑካምብ ሜዳ ላይ ድባቅ ሊመታው እንደሚችል የሚተነብዩ ነበሩ፡፡ ቼልሲ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያለውን ቦታና ሰሞኑን ያስመዘገባቸውን ደካማ ውጤቶች ተንተርሰው፣ባርሴሎና ያሰለፋቸውን ምርጥ ተጨዋቾች ቆጥረው፣ የአሰልጣኝ ጋርዴዎላን ብቃት አሞካሽተው ለቼልሲ የፈሩለት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ምንም እንኳን በስታምፎርድ ብሪጅ ቼልሲ በድሮግባ ጎል ባርሴሎናን አንድ ለባዶ ቢያሸንፍም፤ ያ ግን አጋጣሚን እንጂ የቼልሲን ብቃት፣ የባርሴሎናንም መውረድ እንደማያሳይ የተከራከሩ ነበሩ፡፡
«ደርሶ አይቼው» አለ አማራ ለልጁ ስም ሲያወጣ፡፡ ትናንት ደረሰና ሁሉንም አየነው፡፡ የተጠበቀው ቀርቶ ያልተጠበቀው ሆነ፡፡ እኔም ከጨዋታው በኋላ ነፍሴን እንዲህ አልኳት፡፡
ነፍሴ ሆይ በርቺ፡፡ ተስፋም አትቁረጭ፡፡ ምናልባት ከፊትሽ የምትጋጠሚው ፈተና በዓለም ላይ ወደር የሌለውና ለማሸነፍ ከባድ መስሎ የሚታይ ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባትም ብዙዎቹን የረፈረፈ፤ ታላቅ ስምም ያተረፈ ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ የዓለም ሻምፒዮናነትን ክብር የተቀዳጀ ታላላቅ የተባሉትን ሁሉ ድል እየመታ የመጣም ሊሆን ይችላል፡፡
ግን ነፍሴ ሆይ በርቺ፡፡
በኑሮ ትግል ውስጥ አይሸነፍም የሚባል ፈተና የለም፡፡ በሕይወት ፈተና ውስጥ እንዳሸነፈ ብቻ የሚኖር የለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ እነ እገሌ የሚያሸንፉት እነ እገሌ ደግሞ የማያሸንፉት ፈተና የለም፡፡ ፈተናን የሚያሸንፉት በእምነት ተስፋ ሳይቆርጡ የታገሉ ብቻ ናቸው፡፡ ስለ ተናቅሽ ታናሽና ደካማ ነሽ ማለት አይደለም፡፡ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ መሆኑን አትርሺ፡፡ እነ እገሌን ያሸነፈ ሁሉ አንቺን ያሸንፋል ማለትም አይደለም፡፡ ዝሆን እንደ ትንኝ የሚፈራው እንደሌለ አትርሺ፡፡
ትናንት አንዱ የቼልሲ ተጨዋች የተናገረውን አልሰማሺምን? «ዓለም በሙሉ በባርሴሎና እንደምንሸነፍ ይነግረን ነበር፡፡ እኛ ግን እንደምናሸንፍ እናምን ነበር፡፡ የእነርሱን ያህል ስምና ዝና አልነበረንም፡፡ የእነርሱን ያህል ስብሰብና ጥምረትም አልነበረንም፡፡ አንድ ነገር ግን ነበረን አለ፡፡ እናምን ነበር፡፡ በማሸነፍ እናምን ነበር፡፡ሁላችንም በዚህ እምነት ውስጥ ነበርን፡፡የጥንካሬያችን መነሻውም ይህ እምነት ነበር አለ፡፡»
ነፍሴ ሆይ አንቺም እንደምታሸንፊ እመኚ፡፡ አታሸንፊም የሚሉሽን አትስሚ፡፡ ተፈታታኝሽን አግዝፈውና አልቀው፣ አክብደውና አምጥቀው የሚያስፈራሩሽን አትመልከቺ፡፡ አንቺም እመኚ፡፡ መጽሐፉም ላመነ ሁሉ ይቻላል ነው የሚለው፡፡ እነ አበበ ብቂላ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ መጥተው በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግራቸው ሲሮጡ ማን ያሸንፋሉ ብሎ ገምቷቸው ነበር? እንዲያውም ኢትዮጵያ ታሸንፋለች ተብሎ ስላልታሰበ ባንዲራ እንኳን በአካባቢው አልነበረም ይባላል፡፡ እነ አበበ ብቂላ በዓለም ሚዲያ አስቀድሞ አልተነገረላቸውም ነበር፤ በሌሎች ዓለም ያለውን ዓይነት የመወዳደሪያ ሜዳ፣ የመለማመጃ መሣርያም አላገኙም ነበር፡፡ አንድ ነገር ብቻ ነበራቸው፡፡ እምነት፡፡ እናሸንፋለን የሚል እምነት፡፡ እናም አሸነፈ፡፡
አይዞሽ ነፍሴ ሆይ በርቺ፡፡
በአንደኛው ውድድር ተሸነፍሽ ማለት በሁሉም ውድድር ተሸነፍሽ ማለት አይደለም፡፡አታይውም ቼልሲን፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ነው፡፡ በአምስት ቡድኖች ተበልጦ፤ አንዳንድ ጊዜ እስከ አምስት ጨዋታ በተከታታይ እየተሸነፈ፡፡ በሽንፈቱ ምክንያትም አሠልጣኙን እስከማጣት ደርሶ አልነበረምን? ነገር ግን ዓለም አንድ የመሮጫ መም ብቻ የላትም፡፡ መሮጫው ብዙ ነው፡፡ በአንዱ ስትሸነፊ በሌላው መንገድ ሞክሪ እንጂ ዓለም ሁሉ የተዘጋብሽ አይምሰልሽ፡፡ አንዱ በር ሲዘጋ ሌላውን አንኳኪ፡፡ አንደኛው ሲያቅትሽ ሌላውን ሞክሪ፤ ባንዱ ስትበለጭ በሌላው ብለጭ፡፡
ምንጊዜም ሌላም መንገድ አለ፡፡ ሌላም በር አለ፡፡ ሌላም አማራጭ አለ፡፡
እነዚህ አንድ ነገር ሞክረው ተስፋ የሚቆርጡ፣ ራሳቸውን የሚጥሉ፣ ዋጋ የለንም ብለው የሚያስቡ፣ ከዚያም አልፈው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያጠፉ ሰዎች አያሳዝኑሽም?
አንቺ ግን እንደዚህ አታድርጊ በፕሪሚየር ሊግ ባይሳካልሽ በኤፍ ዋንጫ፣ በኤፍ ዋንጫ ባይሳካልሽ በካርሊንግ ዋንጫ፣ በካርሊንግ ዋንጫ ባይሳካልሽ በአውሮፓ ዋንጫ ሞክሪ እንጂ አለቀልኝ፣ አበቃልኝ አትበይ፡፡
አታይም በሀገሩ በትንንሽ ቡድኖች የተሸነፈው ቼልሲ የዓለም አንደኛውን ቡድን ሲረታው፡፡ አንቺም በትንንሽ ችግሮች በትረቺም፣ እዚህ ግባ በማይባሉ ፈተናዎች ብትሸነፊም፤ ደካማ ነሽ፣ ጥቅም የሌለሽ ነሽ ማለት ግን አይደለም፡፡በሌላኛው ጨዋታ ዓለም ሁሉ ሊያሸንፈው ያቃተውን ቡድን ታሸንፊው ይሆናልና፡፡
አየሽ አይደል ትናንት ባርሴሎና ሰባ በመቶ የኳስ ቁጥጥር ነበረው፡፡ ግን ተሸነፈ፡፡ አብዛኛውን ሜዳና ኳስ የያዙብሽ ሁሉ ያሸንፉሻል ማለት አይደለም፡፡ በኃይልም፣ በሥልጣንም፣ በዕድልም፣ በችሎታም ምክንያት በንግዱም፣ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በግንባታውም፣ በውድድሩም ሜዳ ሰባ በመቶውን ከያዙ ቡድኖች ጋር ይሆናል ውድድርሽ፡፡ ግን ተስፋ አትቁረጭ፡፡ ሰባ በመቶ የያዘውን ቡድን በሠላሳ በመቶ የኳስ ቁጥጥር ማሸነፍ እንደሚቻል አየንኮ፡፡
ነፍሴ ሆይ «አንዱን ስትታገል ሌላው ሲተካብህ» እንደሚለው መዝሙር በብሆር ላይ ቆረቆር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይገጥምሽ ይሆናል፡፡ አንቺ ኃይለኛ ቡድን ገጥሞሽ እርሱን ለማሸነፍ ስትሯሯጭ እንኳን ተጨማሪ ነገር ልታገኚ ያለሽም ይቀነስብሽ ይሆናል፡፡ ግን ተስፋ አትቁረጭ፡፡
አላየሽም ትናንት ባርሴሎና የቼልሲን የግብ ክልል መፈናፈኛ አሳጥቶ እንደ መድፈኛ ሲቀጠቅጠው፣ ቼልሲ ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ሲራወጥ፣ ቢቻል አሥራ ሁለተኛና አሥራ ሦስተኛ ተጨዋች የሚገኝበትን ዕድል ሲመኙ ጭራሽ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች የሚለውን ለባርሴሎናዎች እንተወውና በአሥራ ሁለተኛው ደቂቃ ላይ ዋናው ተከላካያቸው ተጎድቶ ተቀየረ፡፡ አምበላቸው ጆን ቴሪ በሰላሣ ሰባተኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ወጣ፡፡
አሁን አንቺ ብትሆኚ ምን ትይ ነበር? ተስፋ ትቆርጫለሽ? አለቀ በቃ ትያለሽ? አየሽ የሽንፈት መጀመርያው ውስጥሽ ሲሸነፍ ነው፡፡ ልብሽ ተስፋ ሲቆርጥ፤ ራስሽ ለራስሽ መርዶ መንገር ስትጀምሪ፤ ከዚህ በኋላ የኔ ነገር አበቃ ስትይ፡፡ መታገል ያለብሽ እስክትሸነፊ ድረስ አይደለም፡፡ መኖር እስክታቆሚ ድረስ ነው፡፡ ሽንፈት የትግል መጨረሻ ሳይሆን የትግል መማርያ ነው፡፡
ከቼልሲ ተማሪ፡፡
ሁሉ በኑካምብ ሜዳ ዙርያ የሠፈረ ዘጠና የባርሴሎና ደጋፊ በማያውቁት ቋንቋ የማያውቁትን ዜማ እያዜመ አውራውን ተከትሎ የመጣ የንብ መንጋ ሲያስመስለው፡፡ ከተከላካይ ያመለጠች ኳስ የቼልሲን መረብ ሁለት ጊዜ ስትደፍረው፤ አሁን ከዚያ በኋላ ቼልሲ ነፍስ ይዘራል ብሎ ማን ይጠብቅ ነበር? እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ የሚለው በእንግሊዝኛ የለም እንዴ፡፡
አየሽ የሕይወት መመርያው ሁለት ነው፡፡ ማመንና መታገል፡፡ በቃ ባገኘሺው ትንሽ ዕድል፣ በተፈጠረልሽ ጠባብ ቀዳዳ ተስፋ ሳትቆርጭ በእምነት ታገዪ፡፡ ሞክሪ፣ ሞክሪ፣ ደጋግመሽ ሞክሪ፡፡ ያለችሽ የማለፊያ መንገድ እንደ እሳት ባሕር መንገድ የቀጠነች ብትሆን እንኳን በእርሷ መሄድ ከባድ ነው አትበዪ፡፡ ሞክሪ፣ ሞክሪ፡፡
ነፍሴ ሆይ
ተስፋ ሳይቆርጡ የመታገልን ጥቅም አየሽ አይደል፡፡ ከላምፓርድ እግር የተገኘችዋን ኳስ ብራዚላዊ ራሜሬስ ወደላይ አንሥቶ ወደ ጎል ዶላትና እንደ ሶቪየት ጦር ቀይ መስሎ የተሰለፈውን የባርሴሎና ደጋፊ፣ በኣት እንዳጸና መናኝ ጽሞና ውስጥ ከተተው፡፡ አየሽ ያለቀ ሲመስል እንደገና ይጀመራል፤ የተቆረጠ ሲመስል እንደገና ይቀጠላል፡፡
መቼም ሰው ጭንቀት ውስጥ ሲገባ ብዙ ስሕተት ይሠራል፡፡ አንቺም እንደ ትናንቱ ቼልሲ ትግሉና ፈተናው ሲያስጨንቅሽ ትሳሳች ይሆናል፡፡ ቢጫም ቀይም ካርድ ታገኚ ይሆናል፡፡ ግን አታቁሚ ቀጥይ፡፡ ደግሞ በወዲያኛው የተሰለፉትን አትይ፡፡ ስለ ተፈታታኝሽ ዐቅም ትተሽ ስላለሽ ዐቅም አስቢ፣ ስለ ተፈታታኝሽ ችሎታ ትተሽ ስላለቺሽ አነስተኛ ችሎታ አስቢ፡፡ ሰው የሚሸነፈው ስለ ተፈታታኙ ብቻ ማሰብ ሲጀምር ነው፡፡ ሰው ስለ ተፈታታኙ እያሰበ ሲመጣ መጀመርያ እየፈራ፣ ከዚያም እየተጨነቀ፣ በመጨረሻም እጅ እየሰጠ ይሄዳል፡፡ አንቺ ግን እንደዚያ አታድርጊ፡፡
ፈተናው እየተደራረበ ቢመጣ እንኳን፤ ጨዋታው በአንቺ የግብ ክልል ዙርያ ቢሆን እንኳን፡፤ ከግራ ከቀኝ ቢወጥሩሽ እንኳን አትፍሪ፣ አትጨነቂም፡፡ እንደ ቼልሲ ግብ ከሃያ ሦስት ጊዜ በላይ ብትደበደቢ እንኳን አትጨነቂ፤ ተከላከይ፣ ወጥረሽ ተከላከይ፡፡ ከቻልሽ ደግሞ አጥቂ፡፡ ጊዜው እንደሁ ያልፋል፡፡ የጊዜ ጥቅሙ እርሱ አይደል፡፡ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አይሄድ፡፡ ጊዜ ወደፊት ባይሄድ ኑሮ ስንቱ ፈተና ሳያልፍ ባለበት ተገትሮ ይቀር ነበር፡፡
አይዞሽ ቀን የጣለው ዕለት፣ አንቺም የታገልሽ ዕለት ሜሲም ቅጣት ምት ይስታል፡፡ አይዞሽ ለታገለ ዕድል ከእርሱ ጋር ትሆናለች፡፡ አላየሽም እንዴ አንድ ጆን ቴሪ በቀይ ካርድ ቢወጣ የግቡ ቋሚና አግዳሚ ተከላካይ ሆኖ ሲያመሽ፡፡ ማዳን ከየት እንደሚመጣ ምን ታውቂያለሽ? ረድኤትስ ከየት እንደሚገኝ ማን ሊገምት ይችላል? የምንተማመንባቸውን ሰዎች ስናጣ ያልተጠበቀ አግዳሚና ቋሚ ከእኛ ጋር ይሰለፋል፡፡ ብቻ አንቺ ታገዪ፡፡
ተስፋ ቆርጦ ከሕይወት ትግል የሸሸ ሰው እድሉን መጠቀም አይችልም፡፡ መልካም ውጤት ማለት እድልና ትግል በሚገናኙባት የማቋረጫ ነጥብ ላይ የምትገኚ ናት፡፡ እድል ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ትግል ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ሲጓዙ አንድ ቀን ይገናኛሉ፡፡ አንቺ ትግልሽን ካቆምሺው ግን ሳይገናኙ ይቀራሉ፡፡ ስለዚህ ተስፋ አትቁረጭ፡፡ ታገዪ ታገዪ ታገዪ፡፡
በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል ሲባል አልሰማሽም፡፡ አየሽ አይደል በዘጠናኛው ደቂቃ የተገኘው የቶሬዝ ጎል በባርሳ እድል ላይ እንዴት አድርጎ ሚስማር እንደመታበት፡፡ እስከ መጨረሻው የጸና ማለትም ይሄ አይደል፡፡
ቀን ጥሎኛል ብለሽ ራስሽን አትጣይ፡፡ ቀን ሲጥልሽ አንቺ ተነሺ እንጂ፡፡ ቀን እኮ አንቺን ብቻ ሳይሆን ሜሲንም ይጥለዋል፡፡ ቀን አንቺን ብቻ ሳይሆን ባርሴሎናንም ይጥለዋል፡፡ ለምን ሁሉንም ነገር ባንቺ ብቻ የመጣ አድርገሽ ትማረሪያለሽ? ለምን መከራ ባንቺ ላይ ብቻ የመጣ ይመስልሻል?
ነፍሴ ሆይ በርቺ፡፡