ለመለስ የውሸት ድርድር ጥሪ ጆሮ የሚሰጥ የለም!!!

ሰሞኑን መለስ ዜናዊ ስለልዩ ልዩ ጉዳዮች በቀባጠረበት ጋዜጣዊ መግለጫ ከግንቦት 7 ጋር ሊኖር ስለሚችል ድርድርም ጥቂት ዓረፍተ ነገሮችን ተናግሯል። መለስ እንዲህ ጊዜ እየጠበቀ በሚወረውራቸው ዓረፍተ ነገሮች አዲስ አጀንዳ እየሰጠ ኢትዮጵያዊያንን ከትግል ማዘናጋት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ተጠቅሞበት ውጤታማ የሆነበት ስልት እንደሆነ እናውቃለን። አሁንም ይህንን ሲወረውር ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያስገኝለት ተስፋ በማድረግ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ጠያቂው “ኢትዮ ቻናል” የተባለው አስመሳይ ጋዜጣ መሆኑም የድርድሩ ጉዳይ ሳይታሰብበት በነገር መሃል የመጣ ላለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

ሆኖም ጊዜው ተቀይሯል። መለስን ማመን ብቻ ሳይሆን ከወያኔ ጋር ስለሚደረግ “ድርድር” “ብልህነት” ማውጠንጠን ቂልነት መሆኑ ሕዝባችን ተረድቷል። በዚህም ምክንያት ለአሁኑ የመለስ ንግግር ጆሮውን የሚሰጥ አዕምሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብለን ባንገምትም አጋጣሚውን በመጠቀም ከወያኔ ጋር ሊኖር ስለሚችል “ድርድር” የንቅናቄዓችንን አቋም በድጋሚ ማሳወቅ ይጠቅማል በሚል ለመለስ የውሸት ጥሪ የንቅናቄያችንን እውነተኛ ምላሽ እንሰጣለን።

እንደሚታወቀው በወያኔ ባህርይ ምክንያት ሁሉንም ዓይነት የትግል ስልቶች እንደአመቺነታቸው ለመጠቀም ቆርጠን ተነስተን ተግባር ውስጥ ገብተናል። ይህንን የተለያዩ የትግል ስልቶች ኅብር “ሁለገብ የትግል ስልት” ብለነዋል። ሁለገብ የትግል ስልት የመረጥነው ወያኔ “ሰላማዊ” ብሎ በሚጠራው የባርነት መንገድ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ሞክረን ካረጋገጥን በኋላ ነው። የወያኔን ባህርይ የሚመጥን የትግል ስልት ሁለገብ መሆን እንደሚኖርበት ሕዝባችንም በማያሻማ ሁኔታ የተረዳበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በንቅናቄዓችን መርሃ ግብር በተራ ቁጥር 6 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው ሁለገብ የትግል ስልት “ልዩነቶችን በውይይት፣ በድርድርና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በየወቅቱ ለሚፈጠሩ እውነተኛ እድሎች በሩን የማይዘጋ” ነው። እንዲያውም ግንቦት 7 ለእውነተኛ ድርድር ቅድሚያ እንደሚሰጥ በዚሁ ሰነድ ላይ በሚገባ አብራርቷል።

ይሁን እንጂ መዘንጋት የሌለበት አንድ ዓቢይ ነጥብ አለ። የድርድሮች ሁሉ እስትራቴጂያዊ ግብ የወያኔን ዘረኛ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻው አምባገነን በማድረግ የመንግሥት ሥልጣን በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ የሚያዝበትን ሥርዓት መገንባት ነው። ስለሆነም ከወያኔም ጋር የሚደረገው ድርድር ወደዚያ ሥርዓት የሚያቀርበን ሊሆን ይገባል። በሌላ አገላለጽ ከወያኔ ጋር የሚደረግ “ድርድር” በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የወያኔን ሥልጣን ማብቃትን ማብሰሪያ ነው መሆን የሚችለው። ወያኔ ተገዶ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ዓይነቱን ድርድር በመልካም ፈቃዱ ያደርገዋል ተብሎ አይጠበቅም። ስለሆነም የሰሞኑ የእንደራደር ጥሪም ከተለመዱ የመለስ ፓለቲካዊ ጅምናስቲኮች አንዱ ነው፤ ሌላ ምስጢር የለውም።

መለስ በዚህ ቃለ መጠይቁ ውስጥ “ተደራዳሪ” ወገኖች ህገመንግሥቱንና ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር እንዳለባቸው ተናግሯል። ህግ አለ የሚባለው በሥራ ላይ ሲውል ነው። እኛ እንደምናውቀው ወያኔ የሚመራበት አንዳችም ህግ የለም። ህግ ሳይኖር ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሊኖር አይችልም። ለወያኔ መለስ ህግ ነው፤ መለስ ህገመግሥትም ነው። እኛ ለዚህ ህግና ህገመንግሥት አንገዛም!!!

መለስ መለወጥ ከፈለገ የራሱ ድርጅት ጽፎና ጠርዞ ላስቀመጠው፤ ሆኖም እስከዛሬ ሥራ ላይ ውሎ ለማያውቀው “ህገመንግሥት” ብሎ ለሚጠራው ድንጋጌ ራሱን ተገዢ ያድርግ። በርካታ ጉድለቶች ቢኖሩበትም “ህገመንግሥት” ተብሎ የሚወደሰው ድርሳን ተግባራዊ ሆኖ ቢሆን ኖሮ አገራችን ዛሬ በምትገኝበት አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ባልተገኘችም ነበር።

በዚሁ ቃለ መጠይቅ መለስ “ህገመንግሥቱን ከተቀበለና በሰላም ለመታገል ከፈቀደ ማንኛውም ቡድንም ሆነ ግለሰብ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ነን” አለ። ይህን የተናገረው በዚህ “ላም አለኝ – በሰማይ” ዓይነቱ ባዶ ተስፋ የሚታለሉ ጥቂት ቡድኖች፤ ያም ባይሆን ግለሰቦችን አገኛለሁ ብሎ ይሆናል። “ላም አለኝ በሰማይ …” ከኢኮኖሚው አልፎ ፓለቲካም ውስጥ እየገባ መሆኑን ልብ ይሏል። የሕዝባችን መጎሳቆል በዓይኖቻችን እያየንም ቢሆን የ11 በመቶ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት “ሰማይ ላይ ካለች ላሙ” እንደሚያልብ በተደጋጋሚ ሲናገር ጥቂቶቻችን ግራ በመጋባታችን የልብ ልብ ተሰምቶት ቁጥሩን ወደ 15 በመቶ ማሳደጉን ያስተዋለ ሰው፤ መለስ ነገ “እንደኔ ለአገር አንድነት የቆመ”፤ “እንደኔ ልቡ በአገር ፍቅር የነደደ”፤ “እንደኔ ለአገር መስዋዕት የሆነ የለም” ሊለን መዘጋጀቱን ይረዳል። መለስ እንዲህ የእኛን ድክመቶች እየተጠቀመ ኢትዮጵያዊያንን የመበተንና የራሱን ተክለ ሰውነት የመገንባት ሥራ እየሠራ ነው።

በግንቦት 7 እምነት የኢትዮጵያ ጉዳይ የግለሰብ ቀርቶ የአንድ የፓለቲካ ፓርቲ ጉዳይ መሆኑ አክትሟል። እንደድሮው “የኢትዮጵያ ጉዳይ ከኔ በላይ ላሳር” የሚል ፓርቲም ሆነ ቡድን ዛሬ ቦታ የለውም። የኢትዮጵያ ጉዳይ በፀረ-ወያኔ የትግል ጎራ ያለነውን ሁሉ በጋራ የሚመለከት በመሆኑ ማንም በግል ተነስቶ ከወያኔ ጋር ልደራደር ቢል ራሱን ከማቅለል በስተቀር የሚያመጣው ፋይዳ የለም። የተናጠል ትግል እና የተናጠል ውሳኔ ወቅት አልፏል። ይህ ሃቅ ዘግይቶም ቢሆን እየገባን ነው። የዚህ ግንዛቤ መሠረት እየያዘ መምጣት ሊሆን ይችላል ይህን የመጨረሻውን የመበተኛ ሙከራ ለማድረግ መለስን ያነሳሳው።

ሁሌም ለእውነተኛ ድርድር አክብሮት ያለን ቢሆንም ልማደኛ ዋሾ እና ቃለአባይ መሆኑ በተደጋጋሚ ያስመሰከረውን የመለስ ዜናዊን ጥሪ የሚሰማ ጆሮ የለንም።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!!