የሰሜን አፍሪቃ ህዝባዊ አመፆችና ያገራችን እጣ ፈንታ
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ – እሁድ ፌብሩዋሪ 13፣ 2011 ዓ:ም:: በዳላስ ከተማ ግንቦት ሰባት በጠራው ሀዝባዊ ስብሰባ ላይ የቀረበ ንግግር
ሆሳም ካሊፍ የ50 አመት እድሜ ባለጸጋ የሆነ ግብጻዊ መሃንዲስ ነው:: ጣህሪር አደባባይ ሲዘዋወር ያገኘውን አንድ ምእራባዊ ጋዜጠኛ ተጠግቶ እኛ ከቱኒዝያ ምን እንደተማርን ታውቃለህ? ይለዋል:: የደረሰን መልእክት የሚለው “ራስህን አታቃጥል: ማቃጠል ያለብህ በውስጥህ የሰፈረውን ፍርሃት ነው:: የሚለውን መልእክት ነው” ይለዋል::
የዚህን የጣህሪር አደባባይ ትእይንት የሚመለከት ጋዜጠኛ በአግራሞት ከታዘበው ነገር ዋነኛው በህዝቡ ውስጥ ያየው የመሰረቅ ስሜት ነው:: ይህ የሙባረክ ስርአት የሰረቀባችው የህዝቡን ንብረት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ውድ የሆነ ነገር ነው:: የአንድን የግብጽ ትውልድ እጣ ፈንታ ነው የሰረቀባችው ሆኖ የተሰማቸው::
በካይሮ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑ አንድ ምሁር በዚሁ የንጻነት አደባባይ ሲዘዋወሩ ውለው ማታ አሜሪካ ለሚኖር ወዳጃቸው ደውለው ያሉት ደግሞ “ናስር: ሳዳትና ሙባረክ ለ40 ዓመታት በዘረጉት የግፍ የአገዛዝ ስርአት በመንገፍገፍ እነጥፍጥፍ አድርገው ያራገፉብኝን የአገሬን የግብጽን ፍቅር: እነኝህ የጣህሪር አደባባይ ወጣቶች በ 15 ቀናት ውስጥ መለሱልኝ:: አሁን ከነሱ ጋር ሆኘ ብሞትም አይቆጨኝም” ነበር ያለው::
በመጀመሪያ በቱኒዚያ ከዚያም በግብጽ ያየናችው ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ብዙ ጉዶች አያሳየን ነው:: እጅግ በሚዘገንን የአፈና ስርዓት ውስጥ ተወልደው ያደጉ ወጣቶች እምቢ ለመብቴ ብለው ያሳዩት የሚገርም ጀግንነት: ልጇ በእንቅስቃሴው የሞተባት እናት በልጇ መሰዋት የተሰማትን ክብር የገለጸችበትና ሌላው ወንድ ለጇ የሞተው ልጇን አላማ ከዳር እንዲያደርስ ስትማጸን በሰማንበት: አዲሱ የሙባረክ ምክትል ፕሬዜዳንት ሱሌይማን የግብጽ ህዝብ ገና ለዴሞክራሲ አለመብቃቱን ለአለም ህዝብ ያለማፈር ሲነግሩ: ከኛ በላይ ዴሞክራሲ ላሳር ነው ሲሉ የነበሩት የምእራብ መንግስታት በቶኒ ብሌር አማካኝነት ለግብጽ ህዝብ ከነጻነትና ከዴሞክራሲ ይልቅ መረጋጋት የበልጣል: የኛም ጥቅም የሚጠበቀው በሱ ነው ብለው ያለማፈር ሲናገሩ የሰማንበት ጊዜ ነው:: ይህ የብሌር ንግግር እጅጉን ያስከፋው እውቁ የዘመናችን ፈላስፋ እስላቮይ ጂጄክ ይህንን የምእራባውያን የታመቀ የዘረኛነት መገለጫ: “አረቦች ወይንም አፍሪካኖች ለዴሞክራሲ አልበቁም” የሚል የነጻነትን አለም አቀፋዊነት መርህ የሚጋፋ አሳፋሪ ትእይንት ብሎ ተሳልቆ: ግብጾች ለኛ ዴሞክራሲን ያስተማሩበት ክስተት ነው ብሎታል:: ወይዘሮ አና ጎሜዝ በግንቦት 97 ምርጫ ወቅት የህዝቡን የዴሞክራሲ ፍላጎት በምርጫው እለት ለሰአታት ተሰልፎ ዝናብና ሀሩር እየተፈራረቀበት በትእግስት: በሚገርም ዲሲፕሊንና በነቂስ ወጥቶ ሲመርጥ ተመልክተው ያሉትም ይህንንው ነበር ::
ይህንን ተአምራዊ የነጻነት እንቅስቃሴና በወቅታዊ የሃገራችን ፖለቲካ ላይ ያለው እንድምታ ላይ ያለኝን አስተያየት ከማቅረቤ በፊት በዚህ ስብሰባ ላይ ተካፋይ እንድሆን ስለጋበዛችሁኝ ምስጋና ላስቀድም::
ንግግሬን ፈር ለማስያዝ እንደሚከተለው ከፋፍዬ አቀርባለሁ። በመጀመሪያ በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ እያየነው ባለው ክስተት ምንነት ላይ የራሴን ግንዛቤ አቀርባለሁ። ቀጥዬም ለዚህ ህዝባዊ መነሳሳት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ የማምናቸውን ጉዳዮች እያነሳሁ እኔ በገባኝ መንገድ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ከዚያ ቀጥሎ እስካሁን ካየነው የምንወስዳቸው ትምህርቶች ላይ አተኩራለሁ። በመጨረሻም ቱኒዚያ ውስጥ ተለኩሶ እየተቀጣጠለ ያለው የነፃነት ችቦ እኛ አገር እንዲደርስ ማድረግ ይኖርብናል ብዬ የማምናቸውን ነገሮች እነሳለሁ።
ምንድነው እየሆነ ያለው?
ሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ መሠረታዊ የሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ ናቸው። “አብዮት” የሚለውን ቃል መጠቀምም እንችላለን። ይህ አብዮት የአካባቢውን ጂኦ-ፓለቲካ ሙሉ በሙሉ ይለውጣል ተብሎ ይገመታል። አንዳንድ ሰዎች አብዮቱን የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ክስተት ብቻ አድርገው ሲወስዱት ይስተዋላል። ይህ ትክክል ስላለመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃዎች አሉ። የቱኒዚያው ችቦ ነፀብራቅ በአውሮፓ በአልባኒያና ሰርቪያ፤ በሩቅ ምሥራቅ ደግሞ በኢራቅ ውስጥ በጉልህ ታይተዋል። በዩጋንዳና ናጄሪያም ውስጥ ብልጭታው ታይቷል። የያዝነው የአውሮፓውያን 2011 በሃይማኖትና በዲሞክራሲ ሽፋን ተንሰራፍተው ለተቀመጡ አምባገነኖች በሙሉ የሚመች ዓመት እንደማይሆን መልዕክቱ የተላለፈላቸው ይመስላል። ህዝብ ለአስር ዓመታት የሰማው ባዶ ስብከት የሰለቸው መሆኑ በግልጽ የተናገረበት አጋጣሚ ነው። ይህ ለውጥ የጽንፈኝነት አደጋ ባለባቸው አገሮች ውስጥ በሲቪል መብቶች ዙርያ ያጠነጠነ ንቅናቄ መሆኑ ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል።
የሁኔታዎች ፍጥነት እጅግ አስገራሚ ነው። በቱኒዚያ ለሃያ ሶስት ዓመታት የተንሰራፋው አምባገነን በወር ውስጥ ወደቀ። በግብጽ ለ30 ዓመታት የተደላደለውና የኃያላን አገሮች ከፍተኛ ድጋፍ ያለው መንግሥት በ15 ቀናት ውስጥ ተነቀነቀ። በዮርዳኖስ፣ በየመንና አልጄሪያ ውስጥም የመንግሥታቱ ጥርሶች ተነቃነቁ። በአካባቢው ያሉት አምባገነኖች ካቢኔን መፐወዝ፤ ደመወዝ መጨመር፤ ዋጋ መቆጣጠር፤ “በሚቀጥለው ምርጫ አልወዳደርም” እያሉ ቃል በመግባት ማዕበሉን ለማቀዝቀዝ እየጣሩ ነው። ህዝባዊው ንቅናቄ ግን ይበልጥ ሥር እየሰደደና እየተሰራጨ እንጂ እየበረደ አይደለም።
የየመኑ አሊ አብደላ ሳልህ ገና የቱኒዚያውን ህዝባዊ አብዮት ሲያይ ለእሱም እንደማይቀርለት ተገንዝቦ በሚቀጥለው ምርጫ እንደማይሳተፍ፤ ሥልጣንን በማውረስ እንደማያምን በመግለጽ የወጣቱን አጀንዳ ለመንጠቅ ያደረገው እሽቅድድም አስገራሚ ነው። የሱዳኑ አልበሽርም “ብትፈልጉ በድጋይ ውገሩኝ እንጂ ከአገር አልወጣም” ሲል የአገሩን ወጣቶች “አንጀት ለማራራት” ሞከረ። የኢራቁ አልማለኪም ለሶስተኛ ጊዜ እንደማይወዳደር ቃል ገባ። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቱኒዚያ ላይ የተለኮሰው ችቦ እየጎመራ ነው። ሌላው ቀርቶ ፍጹም የተዘጋች አገር በምትመስለው ሳዉዲ ዓረቢያ ውስጥ እንኳን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ። በጎረቤታችን በጅቡቲም እየተንተከ ነው:: ይህ አብዮት እያዳረሰ ያለው በሃይማኖት ሰበብ የሲቪል መብቶች በሚረገጥባቸው አገሮች ውስጥም መሆኑ በአይነቱ ልዩ ያደርገዋል። ይህንን ሁሉ በአንድነት ስናስተውል ነው “ምንድነው እየሆነው ያለው?” የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ መሆኑ የምንገነዘበው።
በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በርካታ ጥናቶች እንደሚደረጉ ጥርጥር የለውም። ወደፊት ብዙ ሊጨመሩባቸው የሚገቡ ነገሮች ቢኖርም እስካሁን በአየነው መነሻነት የሚከተሉት ድምዳሜዎች ላይ መድረስ ይቻላል ብዬ አምናለሁ።
- ይህ ህዝባዊ አመጽ ያሳየን ነገር የነፃነትና የዲሞክራሲ ፍላጎት ዘርን፣ ባህልንና ሃይማኖትን ተሻጋሪ መሆኑን ነው። ነፃነትና ዲሞክራሲ ለምዕራባዊያን ባህልና ሃይማኖቶች የተመቹ፤ ለሌሎች ባህሎችና ሃይማኖቶች ጋር አብረው የማይሄዱ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል። “አረብና አፍሪካዊ ለሆዱ ሲል ቢረገጥ አይከፋውም” የሚል ሃሳብ ብዙ ጊዜ በስውር፤ አንዳንዴም በግልጽ ሲነገር ቆይቷል። የሰሞኑ የሰሜን አፍሪቃ ህዝባዊ አመጾች ይህንን አስተሳሰብ በማያንሰራራ ሁኔታ በታትኖታል። በተደጋጋሚ በፓሊሶች የሚደርስበት ውርደት ተሸክሞ ከሚኖር ራሱን ያቃጠለው ቱኒዚያዊው ወጣት መሃመድ ቦዛዚ በተግባር የነገረንም ይህንን ነው። እንደ አሜሪካዊ ወይም አውሮፓዊ ወጣት ሁሉ እሱም በራሱ ህይወት ላይ ራሱ የመወሰን መብት ያለው መሆኑን፤ ይህ መብት ከሚገፈፍ አለመኖሩ የሚመርጥ መሆኑን አሳይቶናል። ከካይሮው የጣህሪር አደባባይ ሰልፈኞች ጥያቄ በተለያየ መንገድ ይቅረብ እንጂ ማጠቃለያው “ባርነት በቃን! ውርደት በቃን!!” የሚል ነው።
- ሰው ነፃነቱን ሲጎናፀፍ ለራሱ የሚሰጠው ክብር ምን ያህል ከፍ እንደሚል የሰሜን አፍሪካው ንቅናቄ አሳይቶናል። “እኔ ምን አቅም አለኝ” “የመጣውን መቀበል እንጂ ምን ማድረግ እችላለሁ” የሚል ሰው በታህሪር አደባባይ ህዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ ማግኘት አይቻልም። እዚያ የተሰበሰ ሰው በሙሉ “የኔ ተሳትፎ ዋጋ አለው” ብሎ የሚያምን፤ በመሳተፉም ክብር የሚሰማው ነው። እንዲያው በዚህ ንቅናቄ ውስጥ መሳተፍ ራሱ የክብር መገለጫ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ነው በርካታ ግብፃዊያን ከህዝባቸው ጋር ለመራብ እና ለመታገል ክብር ሲሉ ከአውሮፓና አሜሪካ የተመለሱት። በዚህም ምክንያት ነው ሰልፎቹ የተቃውሞ ሰልፍ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የአንድነት ማሳያ የሆኑት። ሰልፎቹ የደስታና የተስፋ ቦታዎች ሆነዋል። ሠርጋቸውን በታህሪር አደባባይ ያደረጉ ጥንዶችንም ሳይቀር አይተናል።
- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የባለቤትነት ስሜት ነው። ወጣቶች የተቃዉሞ ሰልፎችን ለመጥራት እና ራሳቸውን በግንባር ቀደምትነት ለማሰለፍ ከማንም ፈቃድ ይሁን እርዳታ አልጠበቁም። ፓርቲዎች ወይም የታወቁ ሰዎች እንዲመሯቸው አልጠበቁም። ኃያላን መንግሥታት እንዲደግፏቸው አልተለማመጡም። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ኃላፊነት ራሱ ወስዷል። ሰልፈኞች የግብጽ ባለቤቶች እኛ ነን ብለው በማመናቸው እርምጃዎቻቸው ሁሉ ኃላፊነት የተሞላው ነው። የግብጽ ሙዚየም ከዘረፋ የተከላከሉት ራሳቸው ሰልፈኖች ናቸው። ፓሊስ በጠፋ ጊዜ የፀጥታ አስከባሪዎች የወጡት ከራሱ ከሰልፈኛው ነው። መንገድ የሚጠርጉት እነኝሁ ታጋዮች ናቸው::
በህዝባዊ አመፁ ዋዜማ አገራቱ የነበሩበት ሁኔታ
ቱኒዝያ፣ ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ የመንና አልጄሪያ ከአረብነት እና እስላም ሃይማኖት በተጨማሪ በርካታ የሚያመስሏቸው የጋራ ባህሪያት አሉዋቸው። አንዳንዶቹን ከዚህ በታች እዘረዝራለሁ።
1. አምባገንነት፡ በእነዚህ አገሮች ሥልጣን በአንድ ግለሰብ ወይም በአንድ አነስተኛ ቡድን መያዝ የተለመደባቸው ናቸው። ብዙዎች አምባገነኖች ከሃያ ዓመታት በላይ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ቆይተዋል። እኚህ አምባገነኖች በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት መሪነት መቀየር ካስፈለጋቸው የሚመጠቀሙት ስልት ርስ በርሳቸው መተካካትን ነው። በዚህም ምክንያት ሥልጣን በአንድ ቤተሰብ የተያዘባቸው ነበሩ።
2. የሴራ ምርጫዎች፡ በእነዚህ አገሮች ሁሉ የሴራ ምርጫ ሲደረግባቸው የቆዩ ናቸው። የሴራ ምርጫ በስልጣን ላይ ያለው ኃይል እንደገና የሚመረጥበት አሊያም በሥልጣን ላይ ያለው አካል በሚፈልጋቸው ሰዎች የሚተካበት ድግስ ነው። እነዚህ አገሮች ተደጋጋሚ የሴራ ምርጫዎችን ማድረጋቸው “ዲሞክራሲ አስፍነናል” ብለው ለመመፃደቅ ረድቷቸዋል። ምዕራባዊያንም እውነተኛ ዲሞክራሲ ከምዕራቡ ዓለም ውጭ የማይሆን ነገር አድርገው ስለሚወስዱት “ሙከራ ማድረጋቸው” እራሱ እንደ ትልቅ ነገር እየቆጠሩት ሲያሞካሹዓቸው ቆይተዋል።
3. ፀረ-ሽብርተኝነት: እነዚህ አገሮች በፀረ-ሽብር ትግል የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት አገሮች አጋሮች የሆኑ በዚህም ምክንያት የአሜሪካና የአውሮፓ መንግሥታት እንክብካቤና ጥበቃ ያልተለያቸው ናቸው። በተለይም ሙባረክ የአሜሪካ ሁነኛ ወዳጅ መሆኑ የአሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያገኝ የነበረ ከግብጽ ይልቅ ለአሜሪካ ጥቅም የቆመ ሰው ነበር።
4. የተቃዋሚዎች መዳከም፡ በቱኒዚያና በግብጽ ህዝባዊው ተቃውሞው የፈነዳው የተቃዋሚ ኃይሎች በተዳከሙና በተከፋፈሉበት፤ ህዝብም ውስጥ በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ በነበረበት ወቅት ነው።
5. የኑሮ ሁኔታ ማሽቆልቆል: የእነዚህ አገራት ውስጥ መንግሥታት ስለ ኢኮኖሚ እድገት ሲሰብኩ የቆዩ ቢሆንም የአብዛኛው ህዝቡ የእለት ተእለት ኑሮ በዋጋ ንረትና በሥራ እድሎች እጦት እያሽቆለቆለ ሄዷል።
6. ከፍተኛ የሃብት መበላለጥ: የአብዛኛው ህዝብ የእለት ተእለት ኑሮ እያሽቆለቆለ የየአገራቱ ገዢዎችና ተባባሪዎቻቸው የተንደላቀቀ ህይወት፤ ዓይን ያመጣ ዘረፋና ሙስና ሌላው የጋራ ባህሪያቸው ነበር።
ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች አንፃር አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታ ስንገመግም በሁሉም ነጥቦች ከሁሉም በባሳ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። ስለሆነም የሰሜን አፍሪካን ህዝባዊ አመጽ የቀሰቀሱት ከላይ በተዘረዘሩት ነገሮች ምክንያት ከሆነ ተመሳሳይ ነገር ኢትዮጵያም ውስጥ የመነሳቱ እድል ከፍተኛ ነው።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በጎጂ መልኩ የምትለይባቸውን አራት ነጥቦችን ማንሳት ያስፈልጋል።
- በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ባህርይ። በአገራችን በሥልጣን ላይ ያለው ገዢ ቡድን ራሱን እንደ አገሪቱ ዜጋ የማያይ፤ ዜጎችም “ወገናችን ነው” ብለው ለመቀበል የሚቸገሩበት ሁኔታ መኖሩ በህዝብና መንግሥት መካከል የፊት ለፊት ግጭት ቢነሳ ወደ ጠቅላላ ውድመት ያመራል የሚል ስጋት በአንዳንድ ሰዎች ውስጥ እንዲኖር አድርጓል፤
- የጦር ሠራዊት፣ የፓሊስና የስለላ ተቋማት ዘረኛ በሆነ መንገድ የተደራጁ በመሆናቸው ህዝቡ በአንድነት እንዳይነሳ እንቅፋት ይሆናሉ፤ ቢነሳም የተቃውሞውን ሲቪል ባህርይ በማሳጣት ዘርን መሠረት ወደ አደረገ ግጭት ያመራ ይሆናል የሚል ትንተናም የሚሰጡ ሰዎች አሉ፤
- በምርጫ 97 ማግሥት በደረሰት አፈናና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መከፋፈል ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ተስፋ ቆርጧል፤ ህዝቡ ቢነሳሳም ትግሉ በመሪ እጦት መሰናከሉ አይቀርም የሚል ትንተናም ይሰጣል።
- በኢትዮጵያ ውስጥ የመረጃ ስርፀት በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ እንደ ቱኒዝያና ግብጽ በTweeter እና Facebook ሰልፉን ማስተባበር አይቻልም የሚል ሃሳብ በተደጋጋሚ ይነሳል።
አራቱም ነጥቦች በተወሰነ መጠን እውነት አላቸው። ሆኖም ግን እነዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ እንዳይነሳ ይከላከላሉ ብዬ በበኩሌ አላምንም።
ከቱኒዚያና ግብጽ ህዝባዊ አመፆች ትምህርት
- የወጣቶች ተሳትፎ: በቱኒዚያና ግብጽ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ውስጥ ወጣቶች ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል። እንዲያውም ንቅናቄዎቹ ባለቤት ይኑራቸው ቢባል “የወጣቶች ንቅናቄ” ነው መባል የሚችለው። የቱኒዚያና ግብጽ ወጣቶች ወላጆቻቸው ባስቀመጡላቸው ሥርዓት መኖር አልፈለጉም። ወላጆቻቸው ያኖሩላቸው ሥርዓት ባርነት ነበር። እነሱ ሊኖሩበት የሚፈልጉትን ሥርዓት ወላጆቻቸው ሊገነቡላቸው እንዳልቻሉ ተረድተዋል። እናም ለራሳቸው የሚመኙትን ሥርዓት ራሳቸው ለመገንባት ቆርጠው ተነሱ።
ኢትዮጵያም ውስጥ ለለውጥ ሌላ ጎዳና ያለው አይመስለኝም። ያለፉት ትውልዶች መልካም ተግባራትን አከናውነዋል። ሆኖም ጀምረው ያልጨረሷቸው እና ጭራሹን ያልጀመሯቸው በርካታ ነገሮች ለአሁኑ ወጣት ተላልፈዋል። የዛሬው የኢትዮጵያ ወጣት ብዙ እዳ ከወላጆቹ መረከቡ እጅግ የሚያሳዝን ነው። የሆነ ሆኖ ወጣቶቻችን አንድ ቁም ነገር መረዳት ይገባቸዋል – ወላጆቻቸው ለእነሱ የሚመች ሥርዓት አልገነቡም፤ አይገነቡምም። ለራሳቸው የሚሆን ሥርዓት መገንባት ያለባቸው ራሳቸው ናቸው። የቱኒዚያና የግብጽ ወጣቶች ኃላፊነት መወሰድ ሲጀምሩ ነው ጉርምርምታ ወደ አመጽ የተሸጋገረው። ወጣቶች በዚህ ትግል ውስጥ ካልገቡ የሚኖረው ማጉረምረም ብቻ ይሆናል።
- ፈጠራ፤ የራሱን ነፃነት ያወጀ ትውልድ የፈጠራ ችሎታው ምን ያህል እንደሚጎለብት በተደጋጋሚ የታየ ጉዳይ ነው። በቱኒዚያና ግብጽ ወጣቶች ያለ አንባገነኖች ጣልቃገብነት የሚደራጁበት ነፃነት ስላልነበራቸው ህልሞቻቸውን የሚጋሩባቸው መድረኮች አልነበሯቸውም። የነፃነት መንፈስ በውስጣቸው በሰረፀ ጊዜ ግን ይህ ችግር ህልሞቻቸውን አላጨናገፈውም። ለሌላ ተግባር የተዘጋጁትን Facebook እና Twetter ለዓላማቸው ማስፈፀሚያነት ተጠቀሙባቸው። የሚገርመው ነገር እያጣጣረ ያለው የሙባረክ መንግሥት ኤንተርኔትን የዘጋው ወጣቶቹ በአካል ከተገናኙ በኋላ መሆኑ ነው። ታሂር አደባባይ ማራኪ ያደረገው የወጣቹ ፈጠራ ጭምርም ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ስርጭት አነስተኛ መሆኑ የሚያሰጋቸው ወገኖች እምነታቸው ማረፍ ያለበት በወጣቶች የፈጠራ ችሎታ ነው። ወጣቶች አምርረውና ቆርጠው ከተነሱ እነዚህ ችግሮች የሚወጡባቸው መንገዶች አያጡም። [በምርጫ 97 ዋዜማ በአንድ የገጠር ከተማ የወያኔ ደጋፊዎች ሰልፍ ይወጣሉ። ብዙ የንብ ምልክት የታተመበት ወረቀት በየቤቱ ተበተነ። በዚህ የተናደደው ወጣት የአባቱን አንድ የንብ ቀፎ ከነንቦቹ ተሸክሞ “አርማችን ነው” እያለ ሰልፍ ወጣ። ግርግሩ ንቦቹን ረበሻቸውና ሰልፈኛው በመንደፍ ሰልፉን በተኑት። ነፃነት የሚሰማቸው ወጣቶች የሚያመጡት መፍትሄ ይገርማል]
- በራስ የመተማመን ስሜት: ቱኒዚያዊያንና ግብፃዊያን ፍርሃትን ማሸነፍ የቻሉ በራስ የመተማመን ስሜት በመፍጠራቸው ነው። ግብጽ መለዮ ለባሽ ከሆነው የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውጭ 350 000 የሚደርስ ሰላይና ነጭ ለባሽ አላት ተብሎ ይገመታል። ይህ ሁሉ ሠራዊት ግን አመጹ እንዳይነሳ ማገድ፤ ከተነሳም በኋላ ማፈን አልቻለም። በራስ የመተመመን ስሜት መተሳሰብን፣ መተጋገዝን፣ የጋራ ጥቅምን ማስቀደምን ይፈጥራል።
- የሚዲያ ሚና፤ ለእነዚህ ህዝባዊ መነሳሳቶች በመጀመሪያ Facebook እና Tweeter ቀጥሎ ደግሞ አልጀዚራና CNN የተጫወቱት ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያዊያን ከዚህ የምንወስደው ትልቅ ትምህርት አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ አመጽ ቢነሳ የትኛው ሚዲያ ነው የሚዘግብልን? በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉት ወገኖቻችንን እርስ በርሳቸው በምን መንገድ ይገናኛሉ። የኢሳትን አይነት ነፃ የሚዲያ ተቋም መኖር ለትግላችን የሚኖረው ፋይዳ አሁን ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባል።
- ጽናት፤ በተለይ ግብፃውያን ዓለምን ያስደመመ ጽናት አሳይተዋል። ህዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማ እንዲሆን በጽናት መታገልን ይጠይቃል። በነገራችን ላይ የሙባረክ ደጋፊዎች በፈረስና ግመል መምጣታቸው ራሱ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ከአስራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጋር የመፋለማቸው ገላጭ ይመስላል።
- መቻቻል፤ ሰዎች ለትላልቅ ዓላማዎች ሲሰለፉ መለስተኛ ቅራኔዎች ፋይዳ አይኖራቸውም። የነፃነት ትግል ግብፃዊያንን አፋቅሯል። በክርቲያኖች ጥበቃ ሞስሊሞች ሲሰግዱ፤ ለክርስትያኖች ቅዳሴ ሞስሎሞች ከለላ ሲሰጡ ማየት ችለናል። የሁለቱም ሃይማኖቶች ተከታዮች በጋራ በየእምነቶቻቸው ለነፃነት ፀልየዋል።
- የምዕራባዊያን ድጋፍ፤ ምዕራባዊያን የዓለም ህዝቦች ነፃነታቸውን ቢቀዳጁ እና ዲሞክራሲን ቢያሰፍኑ ደስተኞች ይሆናሉ። ሆኖም ግን ከሌሎች አገራት ህዝቦች ነፃነት የራሳቸውን ደህንነት ያስቀድማሉ። ይህ የአገሮች ባህርይ ነው። ለነፃነታችን በምናደርገው ትግል የዲሞክራሲያዊ አገሮች ድጋፍ ለማግኘት መሬት ላይ ያለው ሁኔታ መቀየር እንዳለበት ቱኒዚያም ግብጽም አረጋግጠውልናል። መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ሲቀየር ደግሞ ትላንት እሹሹሩ ያሉትን አምባገነን አንስቶ ከማፍረጥ እንደማይመለሱ በመጀመሪያ ከቱኒዚያው ቤን ዓሊ: ከዚያም ከግብጹ ሙባረክ የተማርነው ትልቅ ቁም ነገር ነው። አምባገነኖቹ የዘረፉትን ገንዘብ እንኩዋን እንዳይበሉ ከመቼው በውጭ ያስቀመጡትን ገንዘብ እንዳያወጡ እንደዘጉባቸው አይተናል::
- የሲቪክ ድርጅቶች ሚና፤ በጉልህ ባይዘገብም ሲቪክ ማኅበራት ያደረጉት አስተዋጽኦ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባም። በርካታ የበጎ አድራጎት ማኅበራት እዚያው እሰልፉ ሜዳ ውስጥ ተፈጥረው ፋፍተዋል። የጤና ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የኢፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በተደራጀ መንገድ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል። የእነዚህ መጠናከር ማኅበራዊ ትስስርን አጠናክራል። በተጨማሪም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች በስፋት እንዲቀሳቀሱ የመብትጥሰቶች እንዲመዘገቡ ረድቷል።
ከካይሮ ወደ አዲስ አበባ
የመብት ረገጣ፣ አፈናና ችጋር ኢትዮጵያ ውስጥ በከፋ ሁኔታ መኖሩ የካይሮው ህዝባዊ አመጽ ወደ ኢትዮጵያ የመዛመት እድሉን ከፍ ያደርገዋል። ኢትዮጵያዊያን ለሰብዓዊና የዜግነት ክብራቸው፣ ለነፃነታቸው፣ ለፍትህና ለተሻለ ህይወት ሲሉ በጋራ መነሳታቸው የማይቀር ነገር ነው። ነገር ግን የአመፃው አነሳስ፣ ፍጥነቱና ጥልቀቱ ከአገር አገር የተለያየ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነም ካይሮ ያየነውን ፎቶ ኮፒ አዲስ አበባ ውስጥ አናይ ይሆናል። በሰሜን አፍሪቃ ውስጥ ያየናቸው ህዝባዊ አመጾች በጥንቃቄ ታቅደው የተሰሩ ነገሮች አይደሉም። ሆኖም በመጀመሪያ ሌሎች አገሮች ሰርተው ያሳዩን ነገሮች መኖራቸው እኛን በእጅጉ ይጠቅመናል ብዬ አምናለሁ። ከእነሱ ተምረን፤ ራሳችንን መርምረን የጎደሉንን ለመሙላት እድል አግኝተናል። ይህንን ታሪክ የፈጠረልንን እድል በሚገባ ለመጠቀም በቶሎ ልንፈጽማቸው ይገባሉ ብዬ የማስባቸውን ነገሮች ላንሳ።
- ኢትዮጵያ በቁጥር ከብዙ እስላማዊ አገሮች የበለጡ ሙስሊም ዜጎች ያሏት አገር ናት፡፡ በሙስሊም ዜጎች ብዛት ኢትዮጵያ ከሳዉዲ አረቢያ፣ ከሱዳን፣ ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ ትበልጣለች፡፡ በዚህም ምክንያት የሙስሊሙን ማኅበረሰብ በስፋት ያላሳተፈ ንቅናቄ ህዝባዊ ሊባል አይችልም፤ ግቡንም አይመታም። የሰሜን አፍሪቃ ሙስሊሞች ለሲቪክ መብቶች መቆም ኢትዮጵያዊያን ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ያበረታታል ብዬ አምናለሁ። በግብጽ ሞስሊሞችና ክርስቲያኖች በአንድ ላይ መቆማቸው ለኢትዮጵያም ሞስሊሞችና ክርስቲያኖች ትልቅ ትምህርት ነው።
ወያኔ የኦርቶዶክስና የእስላም፤ የእስላምና የፕሮቴስታንት፤ የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን እያናከሰ እስካሁን እድሜው አራዝሟል። አሁንም መሠሪ በሆኑ መንገዶች በሃይማኖቶች መካከል ያሉት ግኑኝነቶች እንዲሻክሩ እየተደረገ ነው። በግብጽ እንዳየነው ለሰብዓዊ ክብር፣ ለነፃነትና ለእኩልነት የሚደረግ ትግል የሁሉም ሃይማኖቶች አማኞች የጋራ ትግል ነው።
ስለዚህም በተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች መካከል ያለው አላስፈላጊ ንትርክ በአስቸኳይ በማቆም ትኩረታችንን በነፃነት ትግሉ ላይ ማድረግ ይኖርብናል። የተፈጠረው ሁኔታ ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን የነፃነት ትግልን በስፋት እንዲቀላቀሉ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ ሊያመልጠን የማይገባ ትልቅ እድል ነው።
- ዘረኝነት ለሃያ ዓመታት የወያኔ መንግሥት የፓሊሲ ምሰሶ ሆኗል። የወያኔ ዘረኝነትና ኢፍትሃዊነት ፍጹም ዓይን ያውጣ በመሆኑ ህዝባዊ አመጽ ቢነሳ በፍጥነት ወደ ዘር ግጭቶች ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ስጋት ምንም መሠረት የሌለው አይደለም። በዚህም በተጨማሪ ለነፃነት የምንሰጠው ትርጉምም የተለያየ መሆኑ አንዱ ትልቁ ችግራችን ሆኖ ቆይቷል። በግለሰብ ነፃነት እና በቡድን ነፃነት መነሻነት የተደራጁ ድርጅቶች ተቀራርበው ለመሥራት በመቸገራቸው ሁሉም በወያኔ ለመረገጥ የተመቹ ሆነዋል።
በቱኒዝያና በግብጽ የታየው ህዝባዊ አመጽ አገራችን እንዲደርስ ይህ ሲለያየን የቆየው አጥር ፈርሶ በአንድነት መቆም መቻል አለብን። በብሄርም ይሁን በአገር መደራጀታችን ሳይለያየን ለክብራችን፣ ለነፃነታችንና ለተሻለ ኑሮ በጋራ መቆም አለብን።
ወያኔ ሲወድቅ አገር እንደማይፈርስ ብቻ ሳይሆን የተሻለች አገር እንደምትኖረን ለህዝባችን ማረጋገጫ የምንሰጠው ዛሬ በምናሳየው መግባባት፣ መተጋገዝና መተባበር ጥልቀት ነው።
- የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያ እንጂ የወያኔ ሠራዊት አለመሆኑ እንዲገነዘብ ማድረግ አጣዳፊ ተግባር መሆን ይኖርበታል። ሠራዊቱ ከፓለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርበታል። ይህንን እውን የማድረግ ሥራ አሁን ካሉት የወያኔ አዛዦች ትዕዛዝ አለመቀበልንም ሊያጠቃልል ይችላል። የፓሊስና የደህነቱም ክፍል አባላትም አገራዊ ስሜት እንዲኖራቸው፤ እነሱም የነፃነትን ጣዕም እንዲረዱ የመቀስቀሱ ሥራ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባዋል።
- የፓለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ወያኔን ለመጣል ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ የምትኖረዋንም ኢትዮጵያ በጋራ ለመምራት የሚተባበሩ መሆኑን ዛሬውኑ ማሳየት ይኖርባቸዋል። የመንግሥትን ሥልጣን ለመረከብ ብቃት ያላቸው መሆኑን የገዛ ራሳቸውን፣ ሌሎች ድርጅቶችን: ህዝብን እና ሌሎች አገራትን ማሳመን ይጠበቅባቸል።
- የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ጋር ያላቸውን ቅርበት ማሻሻል ይኖርባቸዋል። የኤለክትሮኒክስ ፓስታዎች (email)፣ Facebook, Tweeter እና ሌሎችንም የኔትዎርክ ዘዴዎችን መፈተሽ ይኖርብናል።
- አስተማማኝ የሚዲያ ተቋማት መኖር እጅግ አስፈላጊ ነገር በመሆኑ ኢሳትን የማጠናከር ተግባር እንደ አገራዊ ሥራ መወሰድ ይኖርበታል። ከዚህም ሌላ በግልም ሆነ በቡድን የተጀመሩ የሬድዮ ስርጭት አገልግሎቶች የሚቀናጁበት መንገድ ሊፈለግ ይገባዋል።
- የወያኔን አፋኝ ሥርዓት በትጥቅ ትግል ለመፋለም የተሰለፉ ኃይሎች ብርታት የካይሮዉን ችቦ አዲስ አበባ ለማድረስ ትልቅ ጉልበት ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ በስትራቴጄ ምርጫ ልዩነት ምክንያት የሚነሱ ክርክሮች ቆመው ሁሉም አንድ የጋራ ግብን አስበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል እላለሁ።
- በመጨረሻም ይህ አብዮት ዓለም ዓቀፍ ይዘት ያለው በመሆኑ በትግል ላይ ላሉ በየትም አገር ላሉ ህዝቦች ወገናዊ ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው። በተለይ የግብጽ አብዬት ውጤታማ መሆን ወደፊት ለሚመጡት ወሳኝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን ለግብጽ ህዝብ ያለውን ድጋፍ ማሳየት ይኖርብናል እላለሁ። የአካባቢውና የአለም አምባገነኖች ሙባረክን አይዞህ እንደሚሉት ሁሉ እኛም ታጋዮችን አይዞአችሁ ማለት ይጠበቅብናል::
ማጠቃለያ
በሰሜን አፍሪካ ተነስቶ ወደ መላው ዓለም እየተዳረሰ ያለው አብዮት በአይነቱ አዲስ የሆነና ጥልቅ የሆነ እንድምታ ያለው ክስተት ነው። የነፃነት ፍላጎትና ዲሞክራሲ የምዕራቡ ባህል አካል አድርጎ በመውሰድ እኛ ለዲሞክራሱ ያልበቃን አድርጎ ሲመለከት የነበረው አስተሳሰብን ያሳፈረ ክስተት ነው።
ይህ ክስተት ወደ ኢትዮጵያ ሊደርስ ይችላል፤ ስለሆነም መዘጋጀት ይኖርብናል። ዝግጅቶቻችንን በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች መመደብ ይቻላል።
- አንደኛ በውስጣችን ያለውን ልዩነት መቀነስ ይገባናል፤ ቢያንስ የልዩነቶችን ደረጃ መመዘንና ቅደም ተከተል ማውጣት: አውጥተንም በዚያ ቅደም ተክተል መሰረት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል::
- ሁለተኛ የሚዲያ አጠቃቀማችን ማሳደግ: ማዘመንና በወሳኘ ቁምነገሮች ላይ ማነጣጠር ይኖርብናል፤
- ሶስተኛ የተለያዩ የትግል ስልቶች በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተደጋጋፊ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅብናል።
እነዚህን በጊዜ ከከወንን ይህን እጹብ ድንቅ የሆነ አጋጣሚ ተጠቅመን ስብዕናችንን አስከብረን፣ በሰላምና በፍቅር የምንኖርባት አገር እንድትኖረን ማድረግ እንችላለን። አለበለዚያ ግን ሳንጠቀምበት አለፈ ብለን ከምንቆጭባቸው መልካም አጋጣሚዎች አንዱ ይሆናል። ምርጫው በእጃችን ነው።
መፈክራችን በቃጋዬ ነው::
ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።