በዋሽንግተንና አካባቢው ከሚገኙ የESFNA አባላት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

በPDF ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

የአንድ ወጣት እድሜ ያስቆጠረው መኩሪያችንና አገናኛችን የሆነው ብቸኛው የስደተኞች ዓመታዊ መተያያ ጐዳና ሆኖ የቆየው በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርትና የባሕል ፌዴሬሽን -ESFNA- ከትውልድ ወደ ትውልድ ይቀጥል ዘንድ፣ እንቅፋቶችን ለማሶገድ ማርች 25 ቀን 2012 በዲሲ ሜርየት ስብሰባ አካሂዷል። ፌዴሬሽኑ የዲሲ አካባቢ ማህበረሰብ ግልፅ ውይይት ያካሂድ ዘንድ ባደረገው ጥሪ፣ ቁጥራቸው እጅግ በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተው፣

ሀ) ባለፉት 28 ዓመታት በብዙ ትግልና ሰፊ ማሕበራዊ ተሳትፎ የተገነባው ተቋማችን -ESFNA- ከውስጡ በማፈንገጥና መደበኛ የተቋሙ መጠሪያ ላይ ቅጽል በመለጠፍ የጀመሩትን አፍራሽ ሙከራ በተመለከተ፣

ለ) ከESFNA ካፈነገጡት ወንድሞቻችን በስተኃላ፣ ይህንን ማህበረሰባችንን የሚጎዳ ተግባር ከፍተኛ ገንዘብ በማቀበል በሚዲያ በገንዘብ ኃይል የሁኔታውን አጥፊነት ያልተረዱ ንፁሕ ወገኖቻችንን ለማሳሳት እየተደረጉ ያሉትን ጥረቶች በተመለከተ፣

ሐ) በብዙ ድካምና በመላው ስደተኛ ማህበረሰብ ብርታት የተገነባውን ESFNA በተደገሰለት አፈራሽ ተግባር ቢዳከም ወይም ቢፈርስ በማህበረሰባችን ላይ የሚያመጣውን የሞራልና ማህበራዊ ጉዳት በተመለከተ፣ ሰፊና ዝርዝር ውይይት አድርገናል።

በውይይቱ ላይ ከቀረበው ዘገባ ESFNA እንደተከፈለ በማስመሰል የሚደረገው አስተያየት መሰረት እንደሌለውና ተሳታፊዎቹ ክለቦች በሙሉ አሁንም ከESFNA ጋር መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል። አሁን በESFNA ዙሪያ ለመፍጠር እየተሞከረ ያለው ውዥንብር ከተቋሙ አመራር በዲሞክራሲያዊነትና ግልፅ ምርጫ ከአመራሩ የተነሱ ጥቂት ወንድሞቻችን፣ ESFNA በሚለው መጠሪያችን ላይ ቅፅል በመለጠፍ ESFNAን ለመምሰል የሚያደርጉት ሙከራና፣ ራሳቸው በየአደባባዩ እደሚያወሩት ከኃላቸው ሆነው ለዚህ የጥፋት ስራ በገፍ በሚያገኙት ገንዘብ የሚያሰራጩት የሚዲያ ዘመቻ ነው። እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች ወንድሞቻችን ከኛው መሀል ወጠተው ይህንን ነባርና ሁላችንም የምንኮራበትን ተቋም ለማዳከም የሚደረጉት ሙከራዎች በጅጉ አሳዝኖናል።

ከላይ ያነሳናቸውና ሌሎችንም በESFNA ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በጥሞና ከተወያየን በኃላ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ በአንድ ድምጽ አውጥተናል፣

የ29 አመት የእድሜ ባለፀጋና የህብረተሰባችን መኩሪያ የሆነውን ESFNAን ለማዳከም ጥቂት ወንድሞቻችን የሚያደርጉትን ማንኛውንም ሙከራ ባስቸኩዋይ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን። አውቀውም ይሁን ባለማወቅ በዚህ ህብረተሰቡን ባሳዘነ ተግባር የተሰማሩ ወገኖቻችን፣ ይህን መጥፎ ተግባር አቁመው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ስናሳስብ፣ ይህን ቀና መንገድ ከመረጡ ESFNAም ሆነ ማህበረተሰቡ በቅንነት እደሚቀበላቸው ልናሳስብ እንወዳለን።

ይህንን ማህበረተሰብ ጐጂና አፍራሽ ተግባር ከኃላ ሆነው የገንዘብ ኃይል በመሆን የሚደግፉት ግለሰቦች ከዚህ አጥፊ ተግባር እዲታቀቡ እናሳስባለን።

በጁላይ 4 ሳምንት የESFNA የዘንድሮው ዥግጅት የሚካሔደው – በዳላስ ቴክሳስ – ስለሆነ፣ መላው የሰሜን አሜሪካ ማህበረተሰባችን ዝግጅቱን ለማክበር ወደዚያው እንዲጓዝና በአሉን ከመቼውም በላይ እንዲያደምቅ ጥሪ እናቀርባለን። ዋሽንግተን ዲሲ ላይ በስማችን ይካሄዳል የሚባለው የመከፋፈያ ዝግጅት ሙከራ ህብረተሰቡ ከህፃን እስከ አዋቂ እንዳይሳተፍ (boycott) እንዲያደርግ ለመላው ወገኖቻችን ጥሪ እናቀርባለን።

የማህበረተሰባችን የንግድ ተቋማትና ኩባንያዎች በሙሉ ይህንን የመከፋፈል ተግባር ስፖንሰር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ወገናዊ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያዊያን የኪነጥበብና የሙዚቃ ባለሙያዎች ዋሽግተን ዲሲ ይደረጋል ለተባለው ከፋፋይና ማህበረሰብ ጐጂ ዝግጅት ላይ ከመሳተፍ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ወገናዊ የፍቅር ጥሪ እናቀርባለን።

ESFNAን በገንዘብ ለማገዝና፣ በያካባቢያችን ያሉ ክለቦችም እንዲጎለብቱ በሚያደርጉት የገንዘብ ተዋፅዖ እንቅስቃሴ ሁሉ ህብረተሰቡ በስፋት እንዲሳተፍ ጥሪ እናቀረባለን።

ESFNA እስከዛሬ ሲያደረግ እንደነበረው ሁሉ ከሃይማኖት፣ከብሔረተሰብና፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በመሆን፣ ህብረተሰባዊና ባህላዊ መድረካችን ሆኖ እንዲቀጥል ስናበረታታ፣ ለዚህ ተግባራዊነት ሁል ጊዜም ከጎን እንቆማለን። ተቋሙ የስከዛሬ ችግሮችን በመመርመር ደነቦቹን አሻሽሎ የበለጠ ግልፅ፣ አሳታፊና ተጠያቂ ሆኖ እንዲቀጥል እያሳሰብን፣ የመላው የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከESFNA ጐን በመቆም ከፋፋዮቻችንን እንዲያሳፍር ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

March 25, 2012
Washington, DC
የዋሺግተን ዲሲ ሕዝባዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች