የጉራፋርዳ ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ተጓጓዙ
ሕገወጥ ሰፋሪዎች ናችሁ በሚል በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ውሳኔ ይኖሩበት ከነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ የተባረሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ያለፍላጐታቸው ወደ ደብረ ብርሃን መጓጓዛቸውን አስታወቁ፡፡ ተፈናቃዮቹ ፍትሕ ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የባሰ በደል እየደረሰባቸው መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የደቡብ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰኔ 2003 ዓ.ም. ለቤንቺ ማጂ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በላኩት ደብዳቤ እስከ ነሐሴ 30 ቀን 1999 ዓ.ም. ድረስ ወደ ክልሉ የመጡና በወረዳና በቀበሌ አመራሮችም ሆነ በራሳቸው መንገድ መሬት የያዙ ዜጐች እስከ ሁለት ሔክታር የእርሻ መሬትና 1,000 ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ እንዲሰጣቸው፣ ባሉባቸው ቀበሌዎች እንደ ሕጋዊ ሰፋሪ ተመዝግበው የክልሉ ነዋሪ መሆናቸውን አውቀው በክልሉ ሕጐች መሠረት እንዲተዳደሩ እንዲደረግ፣ ከ1999 ዓ.ም. ነሐሴ 30 ቀን በኋላ የመጡ ማናቸውም ዜጐች ወደመጡባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲሸኙና ይህም ከቀሪዎቹና ከሚሄዱት ዜጐች ጋር በሚደረግ ውይይትና መደበኛ የሕግ አፈጻጸም ተከትሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይህንን የፕሬዚዳንቱት ትዕዛዝ ተከትሎም በጉራፋርዳ ወረዳ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የቆዩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ሀብትና ንብረታቸውን ጥለው በአጭር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ የሰፈሩበትን ቦታ በወረዳና በቀበሌ አመራሮች ውሳኔ በሕጋዊ መንገድ ተረክበው ግብር ሲከፍሉ መቆየታቸውን በመግለጽ ውሳኔው እንዲሻሻልላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የትኛውም አካል ችግራቸውን ተረድቶ ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ፌስታል ያንጠለጠሉ በርካታ ተፈናቃዮች ሀብትና ንብረት አፍርተው ይኖሩበት የነበሩበትን አካባቢ ጥለው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መገደዳቸውን፣ መፍትሔ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም የፈለጉትን አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት የተጓዙት ተፈናቃዮች በፌዴራል ፖሊሶች ተይዘው ፓርላማ ፊት ለፊት በሚገኘውና ለመልሶ ግንባታ በታጠረው ቦታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ በተሽከርካሪ ተጭነው ተወስደዋል፡፡
ከምንጮቻችን ለመረዳት እንደቻልነው ይኖሩበት ወደነበረው ጉራፋርዳ ወረዳ እንዲመለሱ ወይም ደግሞ ወደ አማራ ክልል ተመልሰው ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው በግብርና ሥራ የሚሰማሩበት ሁኔታ ይመቻችላቸው ዘንድ አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ ከመጡት 600 ገደማ ከሚደርሱት ተፈናቃዮች መካከል፣ አብዛኛዎቹ ባለፈው ዓርብ ከሰዓት በኋላ በፖሊሶች በኃይል እየተገፈተሩ በአራት የሕዝብ ማመላለሻና በአንድ ታክሲ ተጭነው ወደ ደብረ ብርሃን ተወስደዋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ወጣቶች ክበብ ውስጥ ከቀሩት ጥቂት ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ዓርብ ምሽት ለሪፖርተር በስልክ እንደገለጹት፣ ተፈናቃዮቹ ከክበቡ ወጥተው እራት ለመብላት ሲሞክሩ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶች አትወጡም ብለው ከልክለዋቸዋል፡፡ ‹‹ሕፃናት ምግብ ስጡን እያሉ ነው ወደ ደብረ ብርሃን የተወሰዱት፣ መፍትሔ ፍለጋ መጥተን ግፍና በደል ደርሶብናል፡፡ የ22 ቀበሌ ሕዝብ ሲፈናቀል መንግሥት እንዴት ዝም ይላል?›› ሲሉ የሚጠይቁት እኝሁ ግለሰብ፣ መንግሥት ተፈናቃዮችን ሰብስቦ ወደ ደብረ ብርሃን የሚወስድበት ምክንያት ሊገባቸው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡
ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆነው ወጣት በዕለቱ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ (ፖሊስ መሀል ገብቶ ቃለ ምልልሱን እስካቋረጠበት ጊዜ ድረስ) እሱና ሌሎች መሰሎቹ በ1998 ዓ.ም. ወደ ጉራፋርዳ ወረዳ በመሄድ የቀበሌውና የወረዳው አመራሮች በሰጧቸው ፈቃድ መሠረት በሕጋዊ መንገድ መሬት ተረክበው ሀብትና ንብረት አፍርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ ቢቆዩም፣ አሁን ሕገወጥ ሰፋሪ ናችሁ ተብለው ተባረዋል፡፡
ከሦስት ሳምንት በፊት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቤንች ማጂ ዞን አስተዳዳሪ ከአማራ ክልል መጥተው በሕገወጥ መንገድ የሰፈሩ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ይደረጋል እንጂ፣ ሕገወጥ ስለሆኑ ብቻ ሰብዓዊ መብታቸው የሚጣስበት ሁኔታ እንደማይኖር ገልጸው ነበር፡፡ ይህንን ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩም የደቡብ ክልልና የአማራ ክልል ኃላፊዎች ከሁለት ዓመት በፊት ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ከ800 በላይ የሚሆኑ በደቡብ ክልል ሰፍረው የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ወደ ባህር ዳር እንዲጓጓዙ መደረጉን በማስረጃነት ጠቅሰው ነበር፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ግን በወረዳው ኃላፊ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ እነሱ እንደሚሉት በቆዩባቸው ጊዜያት ላፈሯቸው ንብረቶች ካሳ ሳይሰጣቸው፣ ንብረታቸውን የሚሸጡበትም በቂ ጊዜ ሳይሰጣቸው ነው በግዴታ አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ የተደረጉት፡፡
ከደቡብ ጐንደር ፎገራ ወረዳ በ1986 ዓ.ም. ለቡና ለቀማ ወደ ደቡብ ክልል ሄደው ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ በሕጋዊ መንገድ ባገኙት አራት ሔክታር መሬት ላይ በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸውን ለሪፖርተር የገለጹት አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ በአካባቢው የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች እስከ 48 ሔክታር የሚደርስ መሬት ይዘው እያሉ፣ እርሳቸውን ጨምሮ ከ1999 ዓ.ም. በፊት በአካባቢው የሰፈሩ ሌሎች ዜጐች ሁለት ሔክታር መሬት ይበቃችኋል ተብለው ይዘውት የቆዩትን መሬት መነጠቃቸውን ይናገራሉ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፣ በደቡብ ክልል ቤንቺ ማጂ ዞን ጉራፋርዳ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ በሆኑ ዜጐች ላይ የደረሰውን ከቀየ የማፈናቀልና፣ ሀብትና ንብረትን አላግባብ የመውረስ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
‹‹መኢአድ በጉራፋርዳ ወረዳ እየተካሄደ ያለው ሕዝብን ከቀየው የማፈናቀልና የማሳደድ ተግባር በቀጥታ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የተሰጠ መመርያ በመሆኑ ምክንያት፣ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ብሎ በማሰብ ለክልሉ ፕሬዚዳንት ለአቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ እንዲሁም በግልባጭ ለእርስዎና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጻፈ ደብዳቤ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጾ መፍትሔ እንዲበጅለት ቢጠይቅም፣ ጉዳዩ እስከዛሬ ድረስ ምንም መፍትሔ ሊያገኝ አልቻለም፤›› ሲል በደብዳቤው ያመለከተው መኢአድ፣ ጉዳዩ የሃያ ሁለት ሺሕ አባወራዎችን ኑሮ እንዲሁም የብዙ ሺሕ ሴቶችንና ሕፃናትን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
በሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት መሬት ተሰጥቷቸው፣ ይህንንም የሚያረጋግጥ ሕጋዊ ሰነድ በእጃቸው ላይ ባለበት ሁኔታ፣ ከዚህም ባለፈ ቋሚ ተክሎችን ተክለው ሀብት ባፈሩበት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጐችን፣ በሕገወጥነት ፈርጃ ለረጅም ዓመት ከኖሩበትና ቤተሰብ ካፈሩበት ቀየ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ እንዲሁም ያለ ምንም ካሳ ሀብትና ንብረታቸው በካድሬዎች ያለአግባብ እንዲወረስ ማድረግ፣ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት በፍፁም የማይጠበቅ በመሆኑ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት ለአገሩ ዜጐች እንዲያስብና ለመብቶቻቸውም መከበር እንዲቆም መኢአድ አክሎ ጠይቋል፡፡
የክልሉን ውሳኔ ተከትሎ በተፈናቃዮቹ ላይ የደረሰውን በደልም መኢአድ እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ ‹‹ነፍሰ ጡር እናት ሌሊት ወልዳ ሲነጋ የሰዓታት ዕድሜ ካለው ልጇ ጋር ከነፍራሿ ደጅ ተጥላለች፤ ነፍሰ ጡሮች ተሰደዋል፤ የስምንት ወር ዕድሜ ካላቸው ጨቅላ ሕፃናት ጀምሮ በርካታ ሕፃናት ከሚያጠቡ እናቶቻቸው ጋር አብረው ታስረዋል፤ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በረሃብ ተጠብሰዋል፤ በነፍስ ወከፍ እስከ 3 ሺሕ እግር ቡና ዛፍ፣ አቡካዶ፣ ማንጐ፣ ፓፓያና ሙዝ የተከለ እንዲሁም በርካታ የንብ ቀፎ የሰቀለው፣ በከብትና በዶሮ እርባታ ላይ የተሰማራው ገበሬ ያመረተውንና ያፈራውን ሀብትና ንብረት ጥሎ ጨርቁን በፌስታል አንጠልጥሎ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ‘ምንም ይዛችሁ ስላልመጣችሁ ምንም ይዛችሁ አትሄዱም’ እየተባሉ ንብረታቸውን ሜዳ በትነው እንዲሄዱ ተደብድበዋል፤›› ብሏል በደብዳቤው፡፡
ሕዝቡን ያስተባበሩ የነበሩና ከዚህ በፊት ከጉራፋርዳ ወረዳ ታፍሰው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ላይ ታግተው የነበሩ አሥራ ሦስት ያህል አባወራዎች እስካሁን የደረሱበት አለመታወቁን የጠቆመው መኢአድ፣ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዲሞክራሲያዊ ድርጊት የተፈጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሚያስተዳድሩት አገርና በሚመሩት ሕዝብ ላይ በመሆኑ ምክንያት፣ ‹‹በአስቸኳይ የእርስዎን [የአቶ መለስን] ጣልቃ ገብነት የሚሻ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤›› ብሏል፡፡
መኢአድ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በላከው በዚሁ ደብዳቤ በጉራፋርዳ ይኖሩ የነበሩ የአገሪቱ ዜጐች እየተፈጸመባቸው ያለው ግፍና በደል እንዲቆም፣ ሕፃናትና ሴቶች በከፍተኛ የምግብ እጥረትና በጤና መታወክ እየተሰቃዩ በመሆኑ የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በእስር ላይ የሚገኙ አባወራዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፣ በዞኑ በማጐሪያ ጣቢያዎች ውስጥ የተቀመጡ አባወራዎች፣ ሕፃናትና ሴቶች እንዲሁም ወደ ጋምቤላ የተሰደዱ ዜጐች ያሉበት ሁኔታ እንዲጣራ፣ ይህም በገለልተኛ አካል እንዲረጋገጥ፣ ተፈናቃዮቹ ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው በመሆኑና ሕጋዊ ግብር ከፋይ ዜጐች በመሆናቸው ወደ መኖሪያ ቀያቸውና ወደ ሀብት ንብረታቸው አንዲመለሱ እንዲደረግ፣ አካባቢው ለሌላ ልማት ያስፈልጋል ቢባል እንኳን ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ለቋሚ ተክሎቻቸው ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው በሕጋዊና አግባብ ባለው መንገድ እንዲፈጽም ይደረግ የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች አንስቷል፡፡