እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አትመች!
አትክልት አሰፋ (ቫንኩቨር – ካናዳ)
አራት ኪሎ አካባቢ ትንሽ ቡና ቤት ያላቸውና ቁም ነገርን ጣል በማድረግ ዝናቸው የናኘ እናት በጠባብ የመጠጥ ቤታቸው ውስጥ ሁለት ጠጭዎች ተደባድበው ወደ ጣቢያ ለምስክርነት ተጠርተው ያያቸው የመቶ አለቃ በዝና ያውቃቸው ኖሮ፤ የሚናገሩት የማያጡትን እናት እያየ ‘እማማ ምነው? ምነው?፤ እንዴት ቤትዎ ውስጥ ጠብ ሊነሳ ቻለ?’ ቢላቸው “አረ ዝም ብለው ነው ልጄ ቤቴን ታውቃት የለ እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አትመች” አሉት ይላሉ። ዛሬ በየአረብ ሀገራቱ እየተፈጠረ ያለው የህዝብ የነጻነት ጥያቄ ነገ ከጥቁሮቹ ቤት አይገባም ብሎ እጅን ማጣጠፍ የሚቻልበት ሰዓት ላይ አይደለንም። የአለም የፖለቲካ አዙሪት ያለ ህዝባዊ ይሁንታ በኃይል ብቻ ይዘለቃል የሚባልበት ዘመን አክትሞለታል ማለት ይቻላል። አሁን አሁን መንግስትን ለመገልበጥ የሟች ቁጥር እንደጥንቱ፤ እንደዚያ ዘመን በመቶ ሺህዎች መቁጠር የለም። እድሜ ለቴክኖሎጂ። ህዝብ በቃ ካለ ነገ ስራ አልገባም ብሎ ለማመጽ ደቂቃ የማይወስድበት የስልጣኔ ዘመን እየመጣ ይመስላል።