አቡነ ሺኖዳ ሞታቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የጎዳ ነው

ነፍስ ኄር ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛን ቀርቤ የማየት ዕድል ያገኘሁት የዛሬ ዓመት ነበር፡፡ ግብጽ ካይሮ በሚገኘው አባስያ መንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ፡፡ በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ አራት አብያተ ክርስቲያናት ሲገኙ ትልቁ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ነው፡፡ ያሠሩት ከአቡነ ሺኖዳ በፊት የግብጽ ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ ቄርሎስ 6ኛ ሲሆኑ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውም በ1968 ዓም ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በኩል አስተዋጽዖ ያደረግንበት ካቴድራል ነው፡፡

እኔ ግብጽ ስገባ በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው አብዮት ሙባረክን አውርዶ ከፍተኛውን ወታደራዊ ምክር ቤት ተክቶ ነበር፡፡ ያም ቢሆን ግን የታሕሪር አደባባይ አሁንም ከአብዮቱ ውጥረት ነጻ አልነበረም፡፡ በተለየም ከዓርብ የጁምዐ ስግደት በኋላ ወደ ታሕሪር ማምራት የወቅቱ ልማድ ነበር፡፡
በየአካባቢው ከፍተኛ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ ታላላቅ መሥሪያ ቤቶች በወታደሮች ጥበቃ ይደረግባቸዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም እንዲሁ፡፡ የገናን በዓል ለማክበር በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ፈንጅ ተጠምዶ ብዙዎቹን ከገደለ በኋላ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚደረገው ጥበቃ እና ፍተሻ ጠበቅ ብሏል፡፡

በጠዋቱ ቁርስም አልቀመስን፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወኪል የሆኑት አባ ገብረ ሕይወት ወይንም ግብጻውያን እንደሚጠሯቸው አቡነ ሐያት ከፖፕ ሺኖዳ ጋር የተያዘው ቀጠሮ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት መሆኑን ትናንት ማታ ነግረውናል፡፡
እኛ ያረፍነው መዲናት ናስር ከሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ አትናቴዎስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ የእንግዶች ማረፊያ ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ አለ፡፡ እኛ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ነው ያረፍነው፡፡

ከመዲናት ናስር ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ወደ አባስያ ለመጓዝ የተጨናነቀውን የካይሮ ትራፊክ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ እዚህ ሀገር መኪናው ከሰው ቁጥር ይበዛል፡፡ እስካሁን የትራፊክ መብራት ሲበራ እንጂ በመብራት መኪና ሲቆም አላየሁም፡፡ ጡሩንባ እየነፉ መጓዝ ብቻ ነው፡፡ መኪኖቹ ጡሩንባ እንጂ ፍሬን ያላቸው አይመስሉም፡፡

የመንበረ ፓትርያርኩ አካባቢ በወታደሮች እየተጠበቀ ነው፡፡ ወደ ግቢው የምትገቡት በደኅንነት መፈተሻ ሳጥኑ በኩል አልፋችሁ ነው፡፡ ከግቢው ሰፊውን ክፍል የያዘው ቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል ሲሆን የፓትርያርኩ መኖርያ በካቴድራሉ ፊት ለፊት፣ ከዋናው መግቢያ ጀርባ ይገኛል፡፡
ይህ መንበረ ፕትርክና የተገነባበት ቦታ ጥንት የግብጻውያን ክርስቲያኖች መቃብር የነበረበት ቦታ ነው፡፡ ቦታው ለቤተ ክርስቲያኒቱ የተሰጠው በ969 ዓም ለቤተ መንግሥቱ መሥሪያ ተብሎ በተወሰደባት ቦታ ምትክ ነው፡፡ በቦታው ላይ ጥንታዊው የአባ ሮዩስ ቤተ ክርስቲያን ነበረበት፡፡
በ12ኛው መክዘ በአካባቢው 12 አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ፡፡ በ1280 ዓም አብያተ ክርስቲያናቱ ተቃጠሉ፡፡ ከዚያም በቦታው ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ፡፡

ወደ መንበረ ፕትርክናው ልትደርሱ ስትሉ ከግራ እና ከቀኝ ተራራ የሚያህሉ ሁለት ውሾች አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜያት በግብፃውያን ክርስቲያኖች ላይ አደጋዎች እየበዙ ሲመጡ ለጥበቃ የገቡ የመንግሥት ፈታሾች ናቸው አሉን፡፡

ወደ ውስጥ ስንዘልቅ አያሌ እንግዶች ተኮልኩለዋል፡፡ ወደ እንግዶች መጠበቂያ ቤት ወሰዱንና አንድ ሠላሳ ደቂቃ ተቀመጥን፡፡ ከዚያም ወደ ልዩ ጸሐፊያቸው ወደ አቡነ ኤርምያስ ቢሮ ገባን፡፡

ፖፕ ሺኖዳ ሦስት ልዩ ጸሐፊዎች አሏቸው፡፡ ሦስቱም ኤጲስ ቆጶሳት ናቸው፡፡ ሃያ ደቂቃ ያህል በልዩ ጽሕፈት ቤቱ ካረፍን በኋላ ተራችን ደርሶ ገባን፡፡

አቡነ ሺኖዳ አጭር ናቸው፡፡ መንበራቸውም እንደ እርሳቸው አጭር ነው፡፡ ጥቁሩን የጳጳሳት ልብስ ለብሰዋል፡፡ በእድሜ እና በአገልግሎት ብዛት መዳከማቸውን የፊታቸው ገጽታ ይመሰክራል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ረቡዕ እና ዓርብ በካይሮ እና በእስክንድርያ ምእመናኑን ማስተማራቸውን አልተውም፡፡ እኤአ ኦገስት 3 1923 ዓም በላዕላይ ግብጽ አስዩት አብኑብ በተባለ ቦታ የተወለዱት ሺኖዳ ዛሬ በሰማንያ ስምንተኛው እድሜ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጻፏቸው ከአንድ መቶ በላይ መጻሕፍት በመንበረ ፓትርያኩ ቤተ መጻሕፍት ልዩ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ወላጆቻቸው የሰጧቸው ስም ናዚር ጋዪድ የሚል ነበር፡፡ ገና በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ እናታቸውን ያጡት ሺኖዳ ከአምስት እኅቶቻቸው እና ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ብቻቸውን ቀሩ፡፡ የመጀመርያውን ትምህርት በዳማንሁር ባንሐ ካይሮ የተከታተሉ ሲሆን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወሰዱ፡፡

ከዚያም ከኮፕቲክ ሴሚናሪ በነገረ መለኮት የመጀመረያ ዲግሪ አግኝተው በዚያው ሴሚናሪ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳን መምህር ሆኑ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ከድካም ያበረታት ሐቢብ ጊዮርጊስ የሰንበት ት/ቤቶችን እንቅስቃሴ ሲጀምር ዋናው የተልዕኮው አንቀሳቃሽ ሺኖዳ ነበሩ፡፡ እርሳቸው በዚያ ወቅት የኮፕቲክ ወጣቶች ኅብረትን መሠረቱ፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች መጽሔቶች የተለያዩ ጽሑፎችን በማበርከት ወጣቱን ያበረቱት ነበር፡፡ በኋላ ዘመን የመንፈስ አርነት (The release of the Sprit) ተብሎ የታተመው መጽሐፋቸው የእነዚህ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡
በሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓም እኤአ በዋዲ ኤል ናትሩን ወደሚገኘው የሶርያውያን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ የገዳሙ አበ ምኔት እንጦንስ የሚል ስም ሰጧቸው፡፡ በዚያ ገዳም ሺኖዳ አያሌ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ማንበባቸው ይነገራል፡፡ በመነኮሱ በዓመታቸው ክህነት ተቀብለው ቄስ ሆኑ፡፡

ሺኖዳ ከምንም በላይ ለምንኩስና እና ለምናኔ ሕይወት ልዩ ትኩረት አላቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመን በግብጽ የነበሩት እና ለግብጻውያን ገዳማዊ ሕይወት እንደገና ማንሠራራት ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት የኢትዮጵያዊው አብዱል መሲሕ (ገብረ ክርስቶስ) ደቀ መዝሙር ነበሩ፡፡ የገብረ ክርስቶስን ፍጹማዊ መንገድም ለመከተል ይጥሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ለብዙ ዓመታት የኖሩትም በተባሕትዎ ነበር፡፡ መጀመርያ ከገዳሙ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፤ በመቀጠልም ከገዳሙ ዐሥር ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቅ እና በባሕር አል ፋሪግ ወደሚገኝ ዋሻ ገብተው ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ፡፡

ባሕታዊው (The Hermit) የተሰኘውንና በኋላ እኤአ በ1954 የታተመውን ቅኔያቸውን የጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡

በ1959 እኤአ ቄርሎስ ስድስተኛ ልዩ ጸሐፊያቸው አድርገው ሾሟቸው፡፡ ሺኖዳ ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከገዳማቸው መውጣት እና በኣታቸውን መልቀቅ አያስደስታቸውም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜያቸውንም የሚያሳልፉት በዋሻቸው ውስጥ በጸሎት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያትም ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይጠሩ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡

በ1962 እኤአ ሺኖዳ በነበሩበት ገዳም ውስጥ አንድ አስተዳደራዊ ችግር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዩም ወደ ፓትርያርክ ቄርሎስ ስድስተኛ ዘንድ ቀረበ፡፡ በዚያ ጊዜ ሺኖዳ በገዳሙ አስተዳደር ውስጥ ነበሩበት፡፡ ገዳማውያኑ እንደ ጥንቱ አበው ሆነው እንዲኖሩ፣ ገዳማት የችግር ቦታዎች ሳይሆኑ የጸሎት ቦታዎች እንዲሆኑ፤ የግብጽ ገዳማት አዲሱን ትውልድ ለመቀበል በሚችሉበት መንገድ እንዲደራጁ፤ ገዳማውያኑ ሥራ፣ ጸሎት እና ትምህርትን አጣምረው እንዲይዙ ይታገሉ ነበር፡፡ ይህ የሺኖዳ ሃሳብ ያልተስማማቸው አንዳንድ ገዳማውያንም ሺኖዳን ከስሰው ወደ ቄርሎስ ዘንድ አቀረቧቸው፡፡

አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ ሺኖዳን አስጠሯቸው፡፡ ሺኖዳ በቄርሎስ እግር ሥር ተደፍተው «አጥፍቻለሁ፣ ድሮም ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ያለ ዐቅሜ ነው፡፡ እባክዎ ከኃላፊነት ያንሱኝና በዋሻዬ ብቻ ተወስኜ ልኑር፡፡ እኔ ደካማ ሰው ነኝ» ሲሉ ለመኗቸው፡፡

ቄርሎስም «ዛሬ እንደርና ነገ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ» አሉ፡፡

በማግሥቱ መስከረም 30 ቀን 1962 ዓም እኤአ ፓትርያርክ ቄርሎስ እና ሌሎች ጳጳሳት የሺኖዳን ጉዳይ ለማየት በመንበረ ፓትርያርኩ ተሰባሰቡ፡፡ ሺኖዳ ውሳኔውን በጉጉት ነበር የጠበቁት፡፡ ኃላፊነት ከሚባለው ነገር ተገላግለው የምናኔ ሕይወታቸውን ብቻ ለመያዝ ፈልገዋል፡፡
ሺኖዳ ተጠሩ፡፡ ጳጳሳቱ ቆሙ፡፡ ሁሉም ቄርሎስን ያይ ነበር፡፡ ሺኖዳ እንዲንበረከኩ ተነገራቸው፡፡ ተንበረከኩ፡፡ ቄርሎስ እጃቸውን በሺኖዳ ላይ ጫኑ፡፡ ሌሎች ጳጳሳትም ወደ እርሳቸው መጡ፡፡

ሳይታሰብ አቡነ ሺኖዳ ተብለው የግብጽ የመንፈሳውያን ኮሌጆች እና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ሺኖዳ ደነገጡ፡፡ አለቀሱም፡፡
በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥናት በማድረግ የታወቀው የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ጀርመናዊው ኦቶአ ሜናድረስ የአቡነ ሺኖዳን መሾም ሲሰማ እንኳን ደስ ያለዎት የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ሺኖዳ ግን የመለሱለት የሚከተለውን ነበር:

«የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ካንተ ጋር ይሁን፡፡ እንኳን ደስ ያለዎት ብለህ በቅንነት ስለላክህልኝ መልእክት አመሰግንሃለሁ፡፡ ያንተን ወዳጅነት እና ፍቅር መቼም አልዘነጋውም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ለእኔ መላክ ያለበት የኀዘን ደብዳቤ እንጂ የደስታ ደብዳቤ አይደለም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የተሞላበትን የጸሎት በረሃ ለቅቆ ጫጫታ እና ሁካታ በተሞላበት ከተማ እንዲኖር ሲደረግ እንዴት እንኳድ ደስ ያለህ ይባላል? ማርያምን ከክርስቶስ እግር ሥር ተነሥታ ማርታን ልታግዝ ወደ ጓዳ ስትገባ ማነው እንኳን ደስ ያለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ ደስታ ሳይሆን ሀፍረት ነው፡፡ እኔ ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ የተሾምኩበትን ቀን በደስታ ሳይሆን በኀዘን እና በለቅሶ ነው የማስታውሰው፡፡ ብሕትውና እና የተጋድሎ ጸሎት ከምንም በላይ የሚበልጥ ነገር ነው፡፡ ብሕትውና እና ምናኔ ከኤጲስ ቆጶስነት ቀርቶ ከፓትርያርክነት ጋር እንኳን የሚወዳደር አይደለም፡፡

«ወዳጄ ሆይ እውነተኛው ቅድስና ሲመት ሳይሆን ልብን ቤተ መቅደስ አድርጎ ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን የልባችንን ንጽሕና እንጂ የክህነታችንን መዓርግ አይጠይቀንም፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ በምወድዳት ዋሻዬ፣ በባሕር አል ፋሬግ፣ በዋዲ ኤል ናትሩን ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እዚህም እስከ ጥምቀት ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡»

አቡነ ሺኖዳ እያለቀሱ ያቺን የዋዲ ኤል ናትሩን ዋሻ ትተው ካይሮ ቢመጡም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ዋሻቸው መሄድ ያዘወትሩ እንደ ነበር ታሪካቸውን የጻፈላቸው የቅርብ ወዳጃቸው እና በእምነቱ ፕሮቴስታንት የነበረው ኦቶአ ሜናድረስ ይናገራል፡፡

እስከ 1969 እኤአ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ አደራጇቸው፡፡ በዚህ የተነሣም በሙሉ ጊዜያቸው የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ወደ 207 አደገ፡፡ ሺኖዳም በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ ሕዝቡን የሚያስተምሩበት እና የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱበት የትምህርት መርሐ ግብር ከፈቱ፡፡ እስከ አሥር ሺ የሚጠጋ ሕዝብም መርሐ ግብሩን ይከታተለው ነበር፡፡ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጻሕፍትን፣ መዝሙሮችን እና ትምህርቶችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራንንም ያሠለጥኑ ነበር፡፡ በዚህ የሥራ ብዛት ውስጥ እያሉ እንኳን የሳምንቱን ግማሽ በካይሮ ቀሪውን ደግሞ በገዳማቸው ዋሻ ውስጥ ያሳልፉ ነበር፡፡

በዚሁ ዓመት ሺኖዳ የመካከለኛው ምሥራቅ የነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሌሎቹ ጋር የማቀራረቡን ሥራ የጀመሩት ገና በጳጳስነታቸው ዘመን ነው፡፡ በእርሳቸው መሪነት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአያሌ የነገረ መለኮት ውይይቶች ላይ ተሳትፋለች፡፡

ፓርትያርክ ቄርሎስ በመጋቢት 9 ቀን 1971 ዓም ዐረፉ፡፡ በመጋቢት 22 የተሰበሰበው የግብጽ ሲኖዶስም ተተኪውን ለመምረጥ ዝግጅት ጀመረ፡፡ አምስት እጩዎችንም መረጠ፡፡ ነገር ግን በመካከሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አያሌ ፈተናዎች ገጠሟት፡፡ በዚህም ምክንያት ፓትርያርክ ሳይመረጠ ረዥም ጊዜ ቆየ፡፡ በጥቅምት 29 ቀን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ የእጩዎችን ቁጥር ወደ ሦስት ዝቅ አደረገው፡፡ የሦስቱም እጩዎች ስም በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል መንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡ እና ገዳማውያኑም ለሦስት ቀን ሱባኤ ያዙ፡፡

ጥቅምት 31 ቀን 1971 እኤአ በሰንበት ዕለት ሕዝቡ፣ ካህናቱ፣ ገዳማውያኑ እና ጳጳሳቱ በተገኙበት ጸሎት ከተደረሰ በኋላ አንድ ዓይኑን በሻሽ ለተሸፈነ አይማን ሙኒር ካሊል የተባለ ሕፃን በመንበሩ ላይ የተጸለየባቸው ስሞች ቀረቡለት፡፡ እጁን ዘርግቶ አንዱን ዕጣ አወጣው፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በጊዜያዊነት ይመራ የነበረው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ለሆኑት ለሜትሮጶሊጣን አንቶኒዮስም ሰጣቸው፡፡

ወረቀቱን ዘረጉት፡፡ «እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን አባት ይሆኑ ዘንድ አቡነ ሺኖዳን መርጧል» ሲሉ አካባቢው በጭብጨባ እና በእልልታ ተናጋ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ የዛሬ ዐርባ ዓመት ኅዳር 14 ቀን 1971 እኤአ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል፣ ሺኖዳ 3ኛ 117ኛው የግብጽ ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ፡፡

በእራሳቸው ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደገና ኃይል አገኘች፡፡ አሁንም በነገረ መለኮት ኮሌጅ ያስተምራሉ፡፡ የኮሌጁ ዲንም ነበሩ፡፡ የኤልኬራዛ መጽሔት አዘጋጅ ናቸው፡፡ ዓርብ ዓርብ ያስተምራሉ፡፡ ገዳማትን እና ትምህርት ቤቶችን አስፋፉ፡፡ ወጣቱን ወደ አገልግሎት ጠሩ፡፡

አሁንም በፓትርያርክነታቸው ዘመን በአባ ቢሾይ ገዳም የሳምንቱን ግማሽ በገዳማዊ ሕይወት ማሳለፋቸውን አልተውም፡፡ መጻሕፍትን ይጽፋሉ፡፡ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ይጎበኛሉ፡፡ እርሳቸው ሲሾሙ በውጭ ያሉት አጥቢያዎች ሰባት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በአሜሪካ እና ካናዳ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ከሰማንያ በላይ አድርሰዋቸዋል፡፡ በአውስትራልያ 26፣ በአውሮፓ 30 አጥቢያዎች ይገኛሉ፡፡

ሺኖዳ ለአቋማቸው እና ለእምነታቸው ሲሉ ስደትን የቀመሱ ፓትርያርክ ነበሩ፡፡ አንዋር ሳዳት የግብጽ መሪ በነበረ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመናኗ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመቃወም ሺኖዳ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ በዚህ ያልተደሰተው ሳዳት መስከረም 3 ቀን 1981 እኤአ ባወጣው ዐዋጅ ሲኖዳን ከመንበራቸው አሳደዳቸው፡፡ በግዞትም ወደ አባ ብሶይ ገዳም ተላኩ፡፡

ሕዝቡ ሌላ አባት አንመርጥም ብሎ ተከትሏቸው አባ ብሶይ ገዳም ገባ፡፡ እዚያም በሚወዱት ገዳም ተጋድሏቸውን እና ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በገዳሙ በግዞት ለአራት ዓመት ተኩል ከቆዩ በኋላ ሳዳት ሞቶ ሙባረክ ሲተካ በጥር 2 ቀን 1985 እኤአ ወደ መንበራቸው ተመለሱ፡፡

ሺኖዳ ቀልድ ዐዋቂ ናቸው፡፡ በተለይ ሕፃናትን ማስተማር ይችሉበታል፡፡ ሕዝቡን ሲያስተምሩም ቀልድ እና ታሪክ ጣል ማድረግ ይወዳሉ፡፡ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን የአገልግሎት ተሳትፎ በማሳደግም ሺኖዳ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሺኖዳ ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ልክ የለውም፡፡ «በልባችን ውስጥ ያለችው ግብጽ ከምናያት ግብጽ ትበልጣለች» የሚለው አባባላቸው በግብጻውያን ልብ ለዘለዓለም ታትሞ ቀርቷል፡፡ ክርስቲያን እና ሙስሊሙ ሕዝብ ተከባብሮ እና ተባብሮ እንዲኖር በብርቱ ጥረዋል፡፡

በዐርባ ዓመት አገልግሎታቸው ከአንድ መቶ በላይ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ንግግር ዐዋቂ፣ ባለ ቅኔ፣ ሰባኪ እና ደራሲ ናቸው ሲኖዳ፡፡ እንደዚህ ያለ ታላቅ ሰው በሀገራችን ሲሞት «አራት ሰው ሞተ ይባላል፡፡ እኔም

አራት ሰው ሞተ ደረሰና ጥሪ
ደራሲ፣ ሰባኪ፣ ጳጳስ እና መሪ
ያልኩት ለዚህ ነበር፡፡

በሙስሊሞች፣ በፕሮቴስታንቶች እና በካቶሊኮች ዘንድ የሚወደዱ እና የሚከበሩ አባት ሆነዋል፡፡ የታላቁ የአልአዝሐር መስጊድ ኢማም የፖፕ ሺኖዳን ሞት ተከትሎ «ግብጽ እኒህን ጥበበኛ ሰው በምትፈልግበት ወሳኝ ጊዜ እርሳቸውን ማጣታችን የሚያንገበግብ ነው» ነበር ያሉት፡፡

ሞታቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የጎዳ ነው፡፡ ተወዶ የሚኖርና ተለቅሶለት የሚቀበር የሃይማኖት መሪ በዓለም ላይ እየጠፋ ባለበት በዚህ ጊዜ ሺኖዳ በሕይወታቸውም በሞታቸውም ያስተማሩ አባት ሆነዋል፡፡

እነሆ ፊት ለፊታቸው ቆሜ ዝም ብዬ አያቸዋለሁ፡፡ የተቀመጡበት መንበር ይህንን ያህል የተብለጨለጨ አይደለም፡፡ አንዳች የሚስብ ነገር ግን አለው፡፡ የርሳቸውም ልብስ ከመደበኛው የመነኮሳት ልብስ የዘለለ ልዩ ጌጥ የለውም፡፡ አንዳች ነገር ግን ረቦበታል፡፡

ከእርሳቸው ጋር ፎቶ ለመነሣት አስፈቅጄ ስቀርብ የወጣቱን እንቅስቃሴ በተመለከተ ጠየቁኝ፡፡ እኔም በአጭሩ ነገርኳቸው፡፡ «እንደ አባቶቻችሁ ለእግዚአብሔር ብቻ ስትሉ አገልግሉ፡፡ የናንተ አባቶች ለእግዚአብሔር ብቻ ሲሉ የሚያገለግሉ ነበሩ» አሉ፡፡

ስንለያቸው ለእያንዳንዳችን ፊርማቸው ያረፈበት ስጦታ ሰጡን፤ ከዚያም

«አሁን ለሕክምና ወደ አሜሪካ በቅርብ እጓዛለሁ፡፡ እግዚአብሔር ጤና እንዲሰጠኝ እና በሚገባ እንዳገለግል ጸልዩልኝ» አሉ ሺኖዳ፡፡

ወይ አልጸለይንላቸውም፣ ወይም ጸሎታችን አልረዳቸውም መሰል ባገኘናቸው በዓመቱ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓም ዐረፉ፡፡ በሚወዱት በአባ ብሾይ ገዳምም ተቀበሩ፡፡