ኢቴቪ እና ተዛማጅ ትዝታዎቼ

  • ኢቴቪ እና ተዛማጅ ትዝታዎቼ (በእውነተኛ ታሪክ ላይ ያልተመሠረተ)
  • /ክፍል አንድ/

    ሴት አያቴ ቲቪ ክፈትልኝ ለማለት “ቲቢውን አብራው” ትለኛለች፡፡ የኢቲቪን አማርኛ ልዋስና “አንዳንድ ጥርሶች” ስለጎደሏት ብቻ አይመስለኝም “ቲቪ”ን “ቲቢ” የምትለው፡፡ ኢቲቪ ሲከፈት ሳሏ ስለሚነሳባትም ጭምር ነው፡፡ ኢቲቪ ሳምባዋን ሳይነካው አልቀረም፡፡ ሴት አያቴ ከጎረቤት ጋር ቡና እየጠጣች አጣጪዎቿ የማይመስል ነገር ካወሩም በተመሳሳይ መልኩ ሳሏ ይነሳባትል፡፡ መቼ ለታ እትዬ ዘነቡ የተባሉ ጎረቤቷ ቀበሌ ተሰብስበው ከመጡ በኋላ በረካ ላይ ደርሰው ቡና እየጠጡ “ሰምተሸል? ኢትዮጵያ ልትመነደግ ነው…” ብለው ወሬ ሲጀምሩ አያቴ ሳሏ ተነስቶባት ትን! ሊላት ለጥቂት! አላህ አተረፋት፡፡
    ኢቲቢ በሴት አያቴ ሳምባ ላይ ብቻ ሳይሆን በወንድ አያቴ ጨጓራ ላይም ቀላል የመቁሰል አደጋን አስከትሏል፡፡ ወንድ አያቴ ባሩድ በደረቱ የሚመክት አርበኛ ነበር፡፡ችግሩ ምንም ዕድሜ ቢጫነው “ኢቲቢ” ካላየሁ ብሎ ችክ ይላል፡፡ “ጋሼ! ቲቢ ምን ይሰራልኸል፣ ቁርዓን የምትቀራበትን አይንህን በከንቱ አታድክም፤ ይቅርብህ” ስለው “ተው ልጄ! እንደሱ አይባልም፤ ጥልያን ደፍራን ቢሆንስ በምን እናውቃለን፤ አገር ነቅቶ መጠበቅ ነው እንጂ!” ይላል፡፡ “ኢቲቢ” ካላየ አገር የተወረረ ይመስለዋል፡፡ በቲቪ ውስጥ አገር ከሚጠብቅ “ወልወል” ላይ ቤት ቢሰራ ይሻለው ነበር፡፡ ሆኖም በደከመ ዐይኑ ዘወትር የሚያየው ቴሌቪዥን የረባ ነገር ሊያሳየው ስላልቻለ ለጨጓራ ህመም ተዳረገ፡፡ እንዲያም ሆኖ ከዛሬ ነገ በቲቢው ውስጥ የረባ የአገር ጉዳይ አያለሁ በሚል የሞጨሞጨ ዐይኑን ቲቢ መስኮት ላይ ተክሎት ያድራል፡፡ ኢቲቪ በበኩሉ “አንዳንድ የቆቦ ነዋሪዎች ጠግበው ማደራቸውና መጸዳጃ ቤት መጠቀም መጀመራቸውን ገለጡ” እያለ ከማላዘን ውጭ ሌላ ለወንድ አያቴ የሚሆን ጫወታ አላውቅ አለ፡፡
    ወንድ አያቴ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ ከዛሬ ነገ የሆነ የአገር ጉዳይ፣ የሆነ የድንበር ጉዳይ በኢቲቢ ለመስማት እንዳቆበቆበ ነው፡፡ በዚህ መሀል “ኅብረ-ትርዒት” ይጀምራል፡፡ መቀመጫቸውን ክፉኛ እየናጡ የሚደንሱ ሴቶች በኢቲቢ መታየት ይጀምራሉ፡፡ ይኼኔ ይጠራኛል፡፡ “አቤት ጋሼ” እለዋለሁ፡፡ “ና እስቲ ቲቢው ተበላሽቶዋል መሰለኝ፤ አንቴናወን አብጀው” ይላል፡፡ “ምን ሆነ?” እለዋለሁ፡፡ “እንጃ ብቻ! የሚንቀጠቀጥ ነገር ይታየኛል!”
    የሴት አያቴ ሳምባና የወንድ አያቴ ጨጓራ በየእለቱ እየተጎዳ እንደሆነ ስመለከት ኢቲቪ በፈረሰው ማስታወቅያ ሚኒስትር ስር ከሚሆን ባልፈረሰው ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ስር ቢሆን ለአስተዳደር እንደሚመች ገመትኩ፡፡

    “ቁጩ”

    እሳቸው ቁጩን ይወዱታል፤ ቁጩም ይወዳቸዋል

    ያም ሆኖ የሰፈሬ ልጆች አሁንም ቢሆን “ቁጩ”ን ከማየት አልቦዘኑም፡፡ ከፕሪምየር-ሊግ የተረፈችውን ሰዓታቸውን ቁጩ ላይ በማፍጠጥ ያሳልፋሉ፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንድ የሰፈሬ ልጆች አንዳንድ የቁጩ ቲቪ ቁጩ ጋዜጠኞችን በስም ያውቋቸዋል፡፡ ጋዜጠኞቹን ብቻ ሳይሆን “አንዳንድ የምናምን–ነዋሪዎች” የሚባሉትንም ሰዎች ያውቋቸዋል፡፡ ከ “አንዳንድ የአዲሳባ ነዋሪዎች” ውስጥ አንደኛው እንዲያውም ቤቱ እኛ ሰፈር ነው፡፡ ቀበሌ ውስጥ መታወቅያ ያድላል፡፡ የወጣቶች ሊግ ውስጥም የሆነ ሥልጣን አለው፡፡ ልጁ በሰፈር ሲያልፍ አንዳንድ የሰፈሬ ልጆች “እንዴት ነህ አንዳንድ! ደኅናደርክ አንዳንድ” እያሉ ይሳለቁበታል፡፡ መቼ እለት እኛ ቤት አካባቢ በቆመ ስልክ እንጨት ላይ የሆነ የወጣቶች ሊግን የሚመለከት ማስታወቅያ ሲለጥፍ የሰፈሬ ልጆች አገኙትና እንዲህ አሉት፡- “የሆንክ አንዳንድ ነገር ነህ! ሰው ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ይጫወታል አንተ ወጣት ሊግ ውስጥ ትጫወታለህ፡፡” እንዳያየኝ ጥርሴን በስልክ እንጨቱ ሸፍኜ ሳቅኩኝ፡፡

    ቁጩ በግ

    የሰፈሬ ልጆች ሌላም ነገር ያውቃሉ፡፡ ሁሌ በቁጩ ቲቪ የምትታየዋን ወፍራም በግ፡፡
    ማን እንዳደለባት የማትታወቅ ይቺ ያልሸረፈች ጠቦት በግ በቲቪ ስትመጣ የሰፈሬ ልጆች ይስቃሉ፡፡ በጓ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅና በምእራብ ኢትዮጵያ የሚገኝ ማንኛውም ሀብታም ገበሬ ለቃለመጠይቅ በቀረበ ቁጥር ማሳው ላይ ጎምለል-ጎምለል ስትል ትታያለች፤ወይም እንደ ሀብታም ቤት ቡችላ ኢንተርቢው ከሚደረገው ሰውየው ፊት መጥታ ግትር ትላለች፡፡ “ቁጩ በግ” ይሏታል የሰፈሬ ልጆች፡፡ ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሀብታም ገበሬ ብዙ አይሱዙ መግዛቱን፣ ባንክ አንድ ሚሊዮን ብር ማስቀመጡን፣ በብር ላይ ብር በሀብት ላይ ሀብት እየደረበ መሆኑን ፍጥጥ ብሎ በቲቪ ሲናገር በጓ ድንገት አፏን በእጇ ያዘች፤ የሰፈሬ ልጆች ናቸው የነገሩኝ፡፡
    ከእለታት አንድ ቀን ደግሞ ከቤት ወደ ሥራ ስወጣ ሥራ አጥ የሰፈሬ ልጆች እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
    አንደኛው፡- ማታ ማን አሸነፈ?
    ሌላኛው፡- ባርሳ፤
    አንደኛው፡- ስንት ለስንት?
    ሌላኛው፡- 5 ለ 2
    አንደኛው፡- አትዋሽ!? 5…ለ…2?
    ሌላኛው፡- ማርያምን! ባይገርምህ ሜሲ ሀትሪክ ሰርቷል፤
    አንደኛው፡- እነ ማን ጋ አየህ?
    ሌላኛው፡- ቤት ነው ያየሁት፤ በኢቲቪ ተላልፏል እኮ! አላወቅክም እንዴ?
    አንደኛው፡- ኢዲ! ተወው በቃ! በኢቲቪ አይተህ ነው እንዴ 5ለ2 የምትለኝ!

    ከዚህ በኋላ ለአገሬ ቴሌቪዥን ክፉኛ አዘንኩ፡፡ በዓለም ላይ ይህን ያህል ያለመታመን አቅም የፈጠረ ሚዲያ ይኖር ይሆን? የበርማን፣ የኩባን፣ የቻይናን የሰሜን ኮሪያን ቁጩዎች አሰብኩ፤ የአገሬን “ቁጩ” የሚስተካከለው አይኖርም፡፡
    ኢቲቪ በተማሩና በተመራመሩ ጓደኞቼ ዘንድ ደግሞ “ቫይረስ” በመባል ይታወቃል፡፡ አንድ ተመራምሯል የምለው ወዳጄ “ኢቲቪ የዜጎች ኢንተለጀንስ እንዲያሽቆለቁል አስተዋፅኦ አድርጓል” ሲል ዘወትር ይሟገታል፡፡በዚህ ረገድ ሰፊ ጥናት /research/ ለማድረግም የረዥም ጊዜ እቅድ እንዳለው ነግሮኛል፡፡

    የአያቴን ዐይን ብዥ የሚያረገው መንቀጥቀጥ

    ይህ ጓደኛዬ በኢቲቪ ያዘነው ገና ዩኒቨርሲቲ ሳለ ነው፡፡ አንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲ አመጽ ተሳተፈ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአመጽ ጭር አለች፡፡ ሁሉም ጊቢውን ለቆ ወጣ፡፡ ለቤተሰቡ ሄዶ ዩኒቨርሲቲውን ቀውጢ እንዳረጉትና እርሱም ከአመጹ መሪዎች አንዱ እንደሆነ ፎከረ፡፡ እናቱ የድንግል ማርያምን ፎቶ ይዛ “ጭንቅ አማላጇ” ስትል መጸለይ ጀመረች፡፡ እርሱና ቤተሰቡ ማታ የዜና ሰዓት እስኪደርስ ተቁነጠነጡ፡፡ ስለ አመጹ መንግሥት በኢቲቪ ቀርቦ አንዳች ልመና እንደሚያቀርብ ገምቶ ነበር፡፡ አይደርስ የለ የዜና ሰዓት ደረሰ፡፡ ከትንሽ እኅቱ ጀምሮ እስከ አያቱ ድረስ ሁሉም ቲቪ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ ዜና አቅራቢው እንደተለመደው “እንደምን አመሻችሁ-ምናምን የሌላችሁ” ብሎ እጅግ አጎንብሶ እጅ ነሳ፡፡ “በመጀመርያም አርእስተ ዜና- ‘በከፍተኛ ተቋማት የትምህርት ጥራት እየተረጋገጠ መምጣቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዳንድ ተማሪዎች ገለጹ፡፡’”

    ልጅነቴና ቲቪያችን

    ድሮ የእኛ ቤት ቲቪ ክብር ነበራት፡፡ ትምህርት ካቋረጠው ታላቅ ወንድሜ ይልቅ ቲቪያችን በሰፈራችን የተሻለ ትከበር ነበር፡፡ የሰፈር ልጆች ከእኔ ጋር ጓደኛ ለመሆን ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ይገቡ የነበሩትም በዚሁ ምክንያት ነው፤ እኔን ወደው አልነበረም፡፡ ከእኔ ጋር የሚፈጥሩት ወዳጅነት በእኛ ቲቪ ‘120’ ለማየት የይለፍ ወረቀት እንዲሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ‘120’ ድሮ እንዴት ውብ ነበር! አሁንስ? ከፊት ያሉትን 1 እና 2 ቁጥር ይፋቋቸው፡፡ መልሱን ያገኙታል፡፡
    በተለይ የአፍሪካ ዋንጫ ሲቃረብ የሰፈሬ ልጆች ያሳዩኝ የነበረው ፍቅር የአሜሪካና እስራኤልን ወዳጅነት ያስንቃል፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ቤት ኳስ እየተጫወቱ እኔ ድንገት ከመጣሁ ተሸቀዳድመው ጫወታ አቁመው ኳሷን ወደኔ ይልኳታል፡፡ ትንሽ አንቀርቅቢያት እሰጣቸዋለሁ፡፡ ተቧድነው እየተጫወቱ ከሆነ ደግሞ አንዱ ተጫዋች ለእኔ ሲል እንዲያርፍ ይደረግና እኔ እገባለሁ፡፡ አጥቂያቸው ያደርጉኛል፡፡ በረኛውን አልፈውም ቢሆን ጎል እኔ እንዳገባ ኳሷን ይሰጡኛል፡፡ በረኛውም ቢሆን እኔ ኳስ እየገፋሁ ከመጣሁ መርበትበት ይጀምራል፡፡ እግሩ ቄጤማ ይሆናል፡፡ ተከላካዮችም እንዲሁ፡፡ እኔ የሞከርኩት ኳስ ፎሪ ወጥቶ ቢሆንም ዳኛው “ጎል” ብሎ ያጸድቀዋል፡፡ አለበለዚያ ከአቢዲ ፔሌ ጋር መቆራረጡ ነው፡፡ ያኔ አቢዲ ፔሌ “ቬጂቡም” ቅባት ሲቀባ ማየት የማይናፍቅ ልጅ አልነበረም፡፡
    ልክ የአፍሪካ ዋንጫ እንዳለቀ ቁጩ ጓደኞቼ ፍቅራቸው መቀዝቀዝ ይጀምራል፡፡ ከዓለምና ከአፍሪካ ዋንጫ ውጭ የሰፈር ልጆች እኔን ይበልጥ የሚወዱኝ ግን ዐርብና ቅዳሜ ነው፡፡ ዐርብና ቅዳሜ እጅግ ፍቅራቸው ይደረጅብኛል፡፡ እሁድ “120”ን እኛ ቤት ለማየት፡፡

    ሳሎናችን እና ቲቪያችን

    ቲቪያችን “ናሽናል” ነበረች፡፡ ልክ እንደ ቤተሰቡ አባል ነበር የምትታየው፡፡ በአንድ ወቅት “ሽሽሽሽ” ማለት ጀምራ ቤተሰባችን መሀል ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዘመድ ሲመጣ “ቴሌቢዥኗ በጎ ሆነች?” ይላል፤ “አሰላሙአለይኩም” ከማለቱ በፊት፡፡ እናቴ አይወዱንም ለምትላቸው ዘመዶቻችን ሲቀር የቲቪያችንን መበላሸት ያልነገረችው ዘመድ የለም፡፡ አንዳንድ ጠላቶቻችን ለምን ደስ ይበላቸው በሚል ግን ሚሥጢር አድርጋባቸው ቆይታለች፡፡ ያን ሰሞን ሠራተኛችን ‘አንቺ ነክተሸው ነው ቲቪው “እሽሽሽሽሽ”ማለት የጀመረው’ ተብላ ከፍተኛ እንግልት ደረሰባት፡፡ እኔም አስር ጊዜ እንደ ጦጣ ጣርያ ላይ እየተንጠላጠልኩ የቤተሰቡን ኀዘን አንቴና በመነካካት ለማስታገስ የበኩሌን ጣርኩ፡፡ ተሳካልኝ፡፡ ያን ቀን ከጣርያ ስወርድ ልክ እንደ ዩሪ ጋጋሪ ደማቅ አቀባበል ተደረገልኝ፡፡

    ይህ ኢቲቪ ነው

    ናሽናል ቲቪያችን የሳሎናችን አድባር ነበረች፡፡ እንደ እንጀራ ሌማት ዳንቴል ለብሳ፣ እንደ ታቦት በሰው ታጅባ፣ እንደ መስጊድ ሚናራ አንቴናዋን ሽቅብ ቀስራ ሳሎናችን ላይ በክብር ስትሰየም ሁሉም የቤተሰብ አባል በስስት ያያት ነበር፡፡ ቤት ውስጥ ልጆች ስንላፋ “ትወድቃላችሁ” የሚለን አልነበረም፤ “ቲቪውን ትጥላላችሁ” ነበር የምንባለው፡፡ ልጅ እያለሁ ወደ ፊት አባቴ ከወደደኝ የሚያወርሰኝ ይችን ቲቪ እንደሆነ አምን ነበር፡፡ በአባዬ ዘንድ ጥሩ ልጅ ለመባል እተጋ የነበረውን ለዚህ ነበር፡፡ አሁን ግን አላህ የልጅነት ምኞቴን እንዳያሳካው በርትቼ እጸልያለሁ፡፡
    (ይቀጥላል)