ዋልድባን መተሐራ፣ ስኳሩንም መራራ
ዳንኤል ክብረት
[PDF]
ኢትዮጵያ ካሏት ጥንታዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ቦታዎች ዋልድባ አንዱ ብቻ ሳይሆን ዋነኛው ነው፡፡ በሰሜን ጎንደር እና በምዕራብ ትግራይ ተንጣልሎ፣ ከሰሜን ተራራዎች ሠንሠለት ግርጌ ተዘርግቶ የሚገኘው ይህ ገዳም፣ በብዙ ወጣ ገባ መልክዐ ምድሮች እና ኮረብታዎች የተሞላ፣ አብዛኛውም በደን የተሸፈነ ነው፡፡ እንደ ኤዶም ገነት አራት ጅረቶች የሚያጠጡት ሲሆን ሴሞ በሰሜን፣ ተከዜ በምሥራቅ፣ ዘወረግ በምዕራብ፣ ዜዋ ደግሞ በደቡብ ያረሰርሱታል፡፡
የዋልድባ ገዳም ታሪክ ሳብ ብሎ ወደ መጀመርያው የክርስትና ዘመናት ይጓዛል፡፡ በ5ኛው መክዘ በአካባቢው በተባሕትዎ ይኖሩ የነበሩ መናንያን እንደነበሩበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በ485 ዓም ከሰሜን ሸዋ የተነሡ ምእመናን ወደ አካባቢው ተጉዘው መጋቢት 27 ቀን ዋልድባ መግባታቸውን የቦታው ታሪክ ያሳያል፡፡ በ574 ደግሞ ሌሎች ከቡልጋ መጥተው ተቀላቅለዋቸዋል፡፡
በዘመነ ዮዲት ቦታው ከጠፋ በኋላ እንዲሁ ሲኖር አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ከሰሜን ሸዋ ቡልጋ የመጡ ክርስቲያኖች አንሥተውት ነበር፡፡ በኋላ ግን በንጉሥ አግብዐ ጽዮን ዘመን (1278 – 1286 ዓም) ለጊዜው ባልታወቀ በምክንያት ገዳሙ ጠፍ ሆነ፡፡ ዋልድባ እንደገና የቀናው እና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስ ቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ የያዘው በንጉሥ ዓምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት በተነሡት በአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ነው፡፡
በ1319 አካባቢ ከደብረ ሊባኖስ የተንቀሳቀሰ አንድ የመነኮሳት ቡድን (አባ ሙሴ፣ አባ እስጢፋኖስ፣ አባ ገብረ መስቀል እና አባ ገብረ ክርስቶስ) ዋልድባ በመግባት ሥርዓተ ገዳሙን አጽንተውታል፡፡ በገዳሙ እህል መመገብ የቀረው ከእነርሱ መምጣት በኋላ መሆኑ ይነገራል፡፡ የዚህ ሃሳብ አመንጭም አባ ሙሴ መሆናቸውን የገዳሙ ታሪክ ያትታል፡፡ እነዚህ መነኮሳትም የእርሳቸውን ሃሳብ በመቀበል የገዳሙ ምግብ ቋርፍ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ በገዳሙ እህል የሚበላው ለልደት፣ ለትንሣኤ እና ለካህናተ ሰማይ በዓል ብቻ እንዲሆንም ደነገጉ፡፡
በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት (1426-1440 ዓም) የዋልድባ ገዳም ክልል በአራቱ ወንዞች መካከል እንዲሆን ዐዋጅ ተደንግጎ ነበር፡፡ ዐዋጁ ማንኛውም የሀገር ገዥ እና አራሽ ወደ ክልሉ ገብቶ ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሠራ የሚከለክል ነበር፡፡
የዋልድባ ገዳም እስከ ግራኝ ወረራ ጊዜ ቆይቶ በመከራው ሰዓት ጠፍ ለመሆን ደርሶ ነበር፡፡ በኋላ ግን ከወረራው የተረፉ መነኮሳት ተሰባስበው እንደገና አቀኑት፡፡ በመካከልም እየጠፋ እየቀና ለብዙ ዘመናት ኖረ፡፡ በተለይም በዘመነ መሳፍንት በነበረው የእምነት ክርክር የዋልድባ መነኮሳት ዋነኛ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡
የዋልድባ ገዳም ቦታ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ
የዋልድባ ገዳም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ካላቸው ገዳማት አንዱ ነው፡፡
በረዥም ታሪኩ፡- የዋልድባ ገዳም ከአንድ ሺ ዘመን በላይ የተሻገረ ታሪክ ያለው ገዳም ነው፡፡ በዚህም ከተሰዓቱ ቅዱሳን እና ከደብረ ሊባኖስ ታሪክ ጋር የሚተካከል ታሪክ አለው፡፡ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የረዥም ዘመን ታሪክ ለማጥናት ሕያው ከሆኑት ምስክሮች መካከል የዋልድባ ገዳም አንዱ ነው፡፡ በጥንታዊው የክርስትና ዘመን፣ በመካከለኛው ዘመን፣ በዘመነ መሳፍንት እና በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የታሪክ ምዕራፎች ውስጥ የተሻገረ በመሆኑ ማን ይናገር የሚለውን የሚያሟላ ነው፡፡
እመቤታችን በኪደተ እግሯ ከባረከቻቸው ቦታዎች አንዱ መሆኑ፡ የዋልድባ ገዳም እመቤታችን ወደኢትዮጵያ በስደቷ ጊዜ መጥታ በኪደተ እግሯ ከባረከቻቸው እና ጌታችን በሕፃንነቱ ትንቢት ከተናገረላቸው ቦታዎች አንዱ ነው፡፡
ከሌሎች ቦታዎች አያሌ ቅዱሳን የሚጎበኙት ቦታ ነው፡ የዋልድባ ገዳምን ለመሳለም አያሌ ቅዱሳን ወደ ቦታው ይመጣሉ፡፡ በታሪክ እንኳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ሦስት ጊዜ ወደ ቦታው መጥተው ተሳልመውታል፡፡ ገድለ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም አባ ጊዮርጊስ ወደ ገዳሙ መምጣቱን ይተርካል፡፡ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም የተጓዙ ኢትዮጵያውያን መናንያን እና ቅዱሳን ሁሉ በዋልድባ ገዳም አልፈው፣ ተሳልመው እና ተባርከው፣ በሱዳን በኩል ያልፉ ነበር፡፡
በጥንታዊ ቅርሶቹ፡- የዋልድባ ገዳም ከሺ ዓመታት በላይ ያጠራቀማቸው የሀገሪቱን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርሶች ጠብቆ እና አቅፎ የያዘ ገዳም ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ገዳሙ ሲፈታ እንኳን በአካባቢው በሚገኙ የተፈጥሮ መከለያዎች ውስጥ ቅርሶቹን እያስቀመጡ በማትረፍ አቆይተውልናል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከሚገኙ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድላት መካከል አንዱ የዋልድባው ገድለ ተክለ ሃይማኖት ነው፡፡
በልዩ የምናኔ አኗኗሩ፡- የዋልዳባ ገዳም ጥንታዊውን የነእንጦንስን የምናኔ ሕይወት ጠብቆ የኖረ፣ከቋርፍ በቀር የላመ የጣመ የማይበላበት፣ መናንያን ከአራዊት ጋር የሚኖሩበት፣ የጽሞና ቦታ ነው፡፡ አንዳንድ መናንያንም ከብቃት ሲደርሱ ማኅበሩን አስፈቅደው የተባሕትዎ ሕይወትን በመያዝ በዱር በገደሉ እንደወደቁ ይቀራሉ፡፡ በገዳሙ ጫካዎች የተዘዋወሩ እንደሚገልጡት በቁም ጸሎት ላይ እንዳሉ ያረፉ አበው ባረፉበት ቦታ ቆመው ለብዙ ዘመናት በመቆየታቸው፣ በአካባቢው ለሚዘዋወሩ ሌሎች መናንያን ያሉ መስለው ይታያሉ፡፡
በቦታው አቀማመጥ፡- የዋልድባ ገዳም በሁለት ክልሎች ውስጥ የሚገኝ ሰፊ ገዳም ነው፡፡ በአራት ወንዞች ተከልሎ በአያሌ አጥቢያዎች የተዋቀረ አንድ አውራጃ የሚያህል ገዳም፡፡
በትምህርት ቤቱ፡- የዋልድባ ገዳም አያሌ ሊቃውንትን ያፈሩ የአብነት ት/ቤቶች ቦታ ነው፡፡ መናንያኑ ከምናኔያዊ ሕይወት በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርቶች በገዳሙ ይማራሉ፡፡
ብዙ አበውን ያፈራ ነው፡- የዋልድባ ገዳም ለቤተ ክርስቲያን ታላላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ ብዙ አባቶችን ያፈራ ገዳም ነው፡፡ በየአጥቢያው ከሚገኙ መነኮሳት መካከል ቢያንስ አንድ የዋልድባ መነኩሴ አይጠፋም ይባላል፡፡ የዋልድባ መነኮሳት በግብጽ፣ በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ለአገልግሎት ተሠማርተዋል፡፡ ይህም የገዳሙን ሁለገብ አስተዋጽዖ ያመለክታል፡፡
ዋልድባ በኢትዮጵያ ውስጥ ነባር ደኖች ከሚገኙበት የምናኔ ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ የዋልድባ ደን አንድ አውራጃ የሚያክል እና በሀገር በቀል ዛፎች የተሞላ፣ የአራዊት እና የአዕዋፍ ማደርያ የሆነ ቦታ ነው፡፡ ዛሬ ለአካባቢ ጥበቃ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ገበሬውን ሁሉ በአካባቢ ጥበቃ ተግባር በማሳተፍ ላይ ባለበት ጊዜ የዋልድባን ጥብቅ የግዝት ደን ክልል ማረስ የሚጋጭ ተግባር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ዐቀፍ መድረኮች ድምጽዋን ከፍ አድርጋ እየተከራ ከረችባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች አንዱ የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ እንኳንስ ነባር ደኖችን መንካት ሊፈቅድ አዳዲስ የዛፍ ቦታዎችንም ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚሟገት ነው፡፡
የዋልድባ ይዞታ ከሥነ ምሕዳር አንፃር ሲታይ የሀገሪቱ አንዱ የመተንፈሻ ሳንባዋ ነው ያሰኛል፡፡
የዋልድባ ሰሞነኛ ነገር
ዋልድባ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሞነኛ ጉዳይ እንዲሆን ያደረገው በአካባቢው የስኳር እርሻ እና ፋብሪካ ይከፈታል መባሉ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የገዳሙ መነኮሳት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደረሰ አቤቱታ ያሰሙ ሲሆን ሕዝቡም ሁኔታውን መወያያ አድርጎታል፡፡ አካባቢውን በቅርብ ከጎበኙ አካላት እንደ ተገኘው መረጃ ከሆነ በአካባቢው የስኳር ኢንዱስትሪ ለማቋቋም መንግሥት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴውም እህል አይግባብሽ፣ ዘር አይዘራብሽ ተብሎ ከተከለለው የገዳሙ ክልል 2.5 ኪሎ ሜትር ዘልቆ ለመንገድ የሚሆን ቦታ አርሷል፡፡ ገዳማውያኑ እና የአካባቢው ምእመናን በጋራ የሚጠቀሙባቸው አራት አብያተ ክርስቲያናት ማለትም
· ማየ ሕርገጽ ቅዱስ ጊዮርጊስ (የሴቶች ገዳም)
· ዕጣኖ ቅድስት ማርያም (የገዳሙ እህል ቤት)
· ደላስ ቆቃ አቡነ አረጋዊ እና
· ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ናቸው
መንግሥት እንደሚለው እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መነሣታቸው የማይቀር ሲሆን ለዚህም ካሣ እንደ ሚከፍል ገልጧል፡፡
የአካባቢው ምእመናን የዋልድባን ቅዱስ አፈር በመሻት ቀብራቸውን በገዳሙ ማድረጋቸው የተለመደ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም ወደ ክልሉ ሳይደርሱ የዛሬማን እና የአንሽያን ወንዞች ተሻግረው የሚቀብሩ አሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አካባቢው ሲታረስ 27 ዐጽሞች ተገኝተዋል፡፡ በገዳሙ ክልልም ተቀብረዋል፡፡ ወደፊትም በቀጣይ ሥራ ሌሎች ሊገኙ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡
በአካባቢው የሚገኘው ነዋሪ ሲገለገልባቸው የነበሩ 14 የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ይነሣሉ፡፡ የአካባቢው ሕዝብ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ የሚሠፍርበት አሥራ አንድ መንደሮች ተመቻችተዋል፡፡ እነዚህን የተነሡትን የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በአዲሶቹ የሠፈራ ቦታዎች እንደሚገነባ መንግሥት ተናግሯል፡፡
እጅግ አከራካሪ የሆነው አባ ነጻ የሚባለው እና በገዳሙ የግዝት ክልል የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ አቡነ ተስፋ ሐዋርያትን ጨምሮ አያሌ ቅዱሳን ዐጽም ያረፈበት ይህ ቤተ ክርስቲያን በግዝት ክልሉ ውስጥ በመሆኑ አይነሣም፡፡ ነገር ግን የግድቡ ውኃ ወደ አካባቢው ስለሚደርስ የገዳሙን ሕልውና ሊያሠጋው እንደሚችል ገዳማውያኑ ተናግረዋል፡፡ የመንግሥት አካላት የግድቡ ግንባታ ገዳሙን እንዳ ይነካው ተደርጎ ሊሠራ እንደሚችል ቢገልጡም ገዳማውያኑ ግን ሥጋታቸውን የሚቀርፍ ነገር ባለ ማግኘታቸው አልተቀበሉትም፡፡
በአደርቃይ በኩል ያለውን የገዳሙን ክልል በርክነት ለመከለል የቀረበው ዕቅድ በገዳማውያኑ ተቀባይነት ባለማግኘቱ መሠረዙን ምንጮች ገልጠውልናል፡፡
የዋልድባ ጉዳይ ለምን ይህንን ያህል መነጋገርያ ሆነ?
ዋልድባ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዓይነተኛ ገዳም ነው፡፡ የዋልድባ ገዳም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ቀርቶ በምእመናንም ዘንድ የሚታወቅ እና የሚጠበቅ ገዳም ነው፡፡ «አልፎ አልፎ በዋልድባም ይዘፈናል»፣«ላወቀባት ገረገራም ዋልድባ ናት» የሚባለው አባባል ዋልድባ ገዳም ለሥነ ቃል የበቃ የሕዝብ ገዳም መሆኑን ያሳያል፡፡ የዋልድባ መነጋገርያ መሆን ገዳሙ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ታላቅ ቦታ አመላካች ነው፡፡
የሰሞኑ ትኩሳት መመርያን እንጂ መረጃን መሠረት የማያደርገው አሠራራችን ያመጣውም ችግር ነው፡፡ መቼም አንድ የስኳር ኢንዱስትሪ እንደ ታዴዎስ እርሻ በአንድ ቀን ታስቦ በአንድ ቀን አይጀመርም፡፡ የብዙ ጊዜ ዕቅድ እና ፕሮጀክት ውጤት ነው፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ሊካተቱ ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ የፕሮጀክቱ አካባቢያዊ ተቀባይነት ነው፡፡ በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ነባር ነዋሪዎች ፕሮጀክቱ በእነርሱ ላይ ስለሚያመጣው ጉዳትም ይሁን ስለሚሰጠው ጥቅም ማወቅ፣መወያየት፣ሃሳብ ማቅረብ እና መሰማትም አለባቸው፡፡
እንኳንና የአካባቢው ሰዎች ሌላውም ግብር ከፋይ ዜጋ ቢሆን በእርሱ ግብር ስለሚሠራው ሥራ በዝርዝር ማወቅ ያስፈልገዋል፡፡
ዋልድባ አካባቢ በሚሠራው ሥራ ይህ የሆነ አይመስለኝም፡፡ መመርያው ተግባራዊ መሆኑን እንጂ መረጃው ሕዝቡ ዘንድ ደርሶ በጎ ምላሽ መግኘት አለማግኘቱን ያየው አካል የለም፡፡ ዋልድባ ገዳም ነው፣ በሀገሪቱ ታሪክ የማይተካ ሚና የነበረው ገዳም ነው፣ አያሌ አባቶችን አፍርቶ ያሠማራ ገዳም ነው፡፡ አብ ሲነካ ወልድ ይነካ እንደሚባለው ዋልድባ ሲነካ አብረው የሚነኩ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ይህ እየታወቀ እንዲሁ በድፍረት ወደ ሥራው መገባቱ እስከመቼውም የማያባራ ችግር ለገዳሙም ለሚጀመረው ኢንዱስ ትሪም መፍጠር ነው፡፡
ስኳሩን እንደሚፈልጉት፣ በስኳሩ ኢንዱስትሪ ተቀጥረው እንደሚሠሩት የሀገሪቱ ዜጎች ሁሉ የገዳሙ መናንያንም የዚህች ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡ በሀገሪቱ ሂደት የመጠቀም እንጂ ያለ መጎዳት መብት ያላቸው ዜጎች፡፡ የሚጎዱት ጉዳት እንኳን ቢኖር አምነውበት፣ ተቀብለውት፣ መሥዋዕትነት ለመክፈል ወስነውበት፣ ከዚያም በላይ ደግሞ ያሥምረው ብለው አቡነ ዘበሰማያት ደግመውበት መደረግ አለበት፡፡ ይህ አለ መሆኑን በቀላሉ ከሚያሳዩን ነገሮች አንዱ ወደ ግዝቱ የገዳሙ ክልል ሁለት ኪሎ ሜትር ተኩል ከራ ከመንግሥት ዕቅድ እንኳን በተቃራኒው ተገብቶ መታረሱ ነው፡፡
የዋልድባ ገዳም መነጋገርያ ከሆነ በኋላ እንኳን የሚመለከታቸው አካላት (ቤተ ክህነት እና መንግሥት) ለሕዝብ መረጃ ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ሁሉም ነገር የሚሰማው በሹክሹክታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሜት እንደ ባህል ለተያዘበት ማኅበረሰብ ያልተገባ ሥጋት እና ጭንቀት መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ መንግሥታት ማኅበራዊ የመረጃ መረቦችን እየተጠቀሙ የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን ለሕዝባቸው መንገር በጀመሩበት ዘመን ብሔራዊ የሚዲያ ተቋማት እንኳን ነገሩን ዝም ማለት አልነበረባቸውም፡፡
ሌላው ችግር ደግሞ ነገሮችን አጣጥሞ ያለ መጓዝ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ልማት ያስፈልጋታል፡፡ ሌላም ልማት ያስፈልጋታል፡፡ ነገር ግን ዕድገታችን አንዱን ገድሎ በሌላው መቃብር ላይ የሚቆም መሆን የለበትም፡፡ ከ90 በመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ ሃይማኖተኛ መሆኑን በሕዝብ ቆጠራዎች ላይ አሳይቷል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የሃይማኖት ጉዳይ የሀገሪቱ ዋና ጉዳይ ነው ማለት ነው፡፡ የምንጓዘው ጉዞም ይህንን የሀገሪቱን ዋና ጉዳይ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡
የኢትዮጵያ ዕድገት ከታሪኳ፣ ባህልዋ፣ ሃይማኖቷ እና ቅርሷ ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡ አዲስ ሕንፃ ለመሥራት ብለን ላሊበላን ማፍረስ ወይንም አኩስምን መጣል የለብንም፡፡ አዲስ ደን የምንተክለው የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን የሱጳ ደን ነቅለን በምናገኘው ሜዳ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ነባር እሴቶቻችን ከአዳዲስ እሴቶቻችን ጋር የሚጣጣሙበትን ወይንም አብረው የሚጓዙበትን መንገድ መፈለግ ነው ዋናው ሥራችን፡፡
በዋልድባ አካባቢ የልማት ሥራ ለመሥራት መነሣቱ አይደለም ችግሩ፡፡ ከልማት ሥራው በፊት የዋልድባ ገዳም ይቀድማል፡፡ ቢያንስ በ1000 ዓመት ይቀድማል፡፡ የልማቱ ሥራ ከዋልድባ ገዳም ጋር መጣጣም አለበት እንጂ፣ የዋልድባ ገዳም ከልማት ሥራው ጋር እንዲጣጣም መጠየቅ የለበትም፡፡ እንዲህ ባለ አካባቢ ምን ዓይነት ልማት መደረግ አለበት? ይህ ሲከናወንስ የገዳሙ እሴቶች፣ መብቶች እና ሀብቶች እንዴት መጠበቅ ይችላሉ? ከሚሠራው ሥራ ገዳሙ የሚጠቀምበት እንጂ የማይጎዳበት መንገድም ቀድሞ መፈለግ አለበት፡፡
እዚህ ላይ ከግምት ውስጥ መግባት የነበረባቸው ቢያንስ ሦስት ጉዳዮች አሉ፡፡
አካባቢያዊ መስተጋብር፡- ይህ አካባቢ የገዳም አካባቢ ነው፡፡ ይህ ገዳምም በዚያ ቦታ ከሺ ዓመታት በላይ ኖሯል፡፡ እናም በአካባቢው የሚደረጉ ሥራዎች የገዳሙን ገዳማዊ እሴቶች የማያጠፉ መሆን አለባቸው፡፡ ገዳሙ ከዓለም ሰዎች እንቅስቃሴ የራቀ፣ ጸጥታ የነገሠበት እና ጥብቅ ክልል ያለው ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የገዳሙን ክልል መንካቱ ብቻ አይደለም ነገሩ፡፡ ከገዳሙ ክልል ውጭ የሚሠራ ሥራም ቢሆን እነዚህን የገዳሙን እሴቶች የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በገዳሙ አካባቢ ይሠራል የተባለው የስኳር ኢንዱስትሪ ነው፡፡ የስኳር ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በዚህ ከፍተኛ የሰው ኃይል የተነሣም በሀገራችን የስኳር እርሻ እና ፋብሪካ ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከተሞች ተመሥርተዋል፡፡ ወንጂ እና መተሐራን ይጠቅሷል፡፡ ይህ ማለት አካባቢው ከፍተኛ የሰው ኃይል እንቅስቃሴ ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
ይህንን ዓይነት እንቅስቃሴ የማይጠይቅ ተግባር በአካባቢው ማከናወን አንዱ አማራጭ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የአካባቢው የሰው እንቅስቃሴ ገዳማዊ ሕይወቱን እንዳይረብሸው በሚያስችል መንገድ የሚከናወንበትን ሥራ መሥራት ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው በዚህ ጉዳይ የታሰበ ነገር ስለመኖሩ ምንም ዓይነት ግልጽ መረጃ የለም፡፡
በአንዳንድ ሀገሮች በአንድ ቦታ ላይ የአካባቢውን ነባራዊ መልክዐ ምድር፣ መልክዐ ጠባይ እና መልክዐ እሴት የሚቀይሩ ተግባሮች ከመከናወናቸው በፊት ነባር ነዋሪዎች አስተያየት እንዲሰጡባቸው ይደረጋል፡፡ የነዋሪዎቹን ስምምነት ማግኘትም መሠረታዊ ነገር ይሆናል፡፡ በአሜሪካን ሀገር በአንድ መንደር አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ለማቋቋም የአካባቢው ነዋሪ ፈቃድ መገኘቱ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡
ከአካላዊ ጉዳት ነጻ መሆን፡- ገዳሙ የሀገሪቱ መንፈሳዊ ሀብትም ቅርስም ነው፡፡ የአኩስም ሐውልትን ወደ አኩስም የመለስነው በሮም አደባባይ መቀመጡ ክብካቤ ስላሳጣው አይደለም፡፡ የአኩስም ሐውልት መንበሩ፣ ክብሩም አኩስም ስለሆነች እንጂ፡፡ ከአኩስም መነቀሉን ስለ ተቃወምን ነው ያስመለስነው፡፡ የዋልድባም እንደዚሁ ነው፡፡ ዋልድባ በሀገሩ ከነ ሙሉ ክብሩ የመኖር ኢትዮጵያዊም ሕጋዊም መብት አለው፡፡ በአካባቢው የሚሠሩ ሥራዎች በገዳሙ ላይ አካላዊ ጉዳት የማያስከትሉ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን እንደምናየው ግን የገዳሙ የግዝት ክልል ታርሷል፡፡ የገዳሙ የእህል ቤት ወይንም ሞፈር ቤት የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ሊነሣ ነው፡፡ የሴቶቹ ገዳም ሊነሣ ነው፡፡ በአንደኛው የገዳሙ ቤተ ክርስቲያንም ግድቡ አደጋ ሊያደርስ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህን ሁሉ አደጋዎች በሚቀንስ እና የገዳሙን ህልውና በማይነካ መልኩ ፕሮጀክቱን መቅረጽ የገዳማውያኑ ጭንቀት ሳይሆን የአጥኚው እና የአስጠኚው ጭንቀቶች መሆን ነበረባቸው፡፡ ልማቱ ከአካባቢው እሴት ጋር ተጣጥሞ በሚሄድበት መንገድ ላይ ገዳማውያኑ በነጻ መክረው፣ የሃሳቡ ባለቤቶች እና ተሳታፊዎች መደረግም ነበረባቸው፡፡ ወይ በሥጋታቸው መሠረት መሠራት፣ ያለበለዚያም ደግሞ ሥጋቱን በሚያስቀር መንገድ መሠራት ነበረበት፡፡
መንፈሳዊ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ፡- አስቀድሞ የገዳሙን ማኅበረሰብ ባሳተፈ፣ ችግሮችን በሚፈታ እና ሁለቱም አካላት ሳይጣረሱ በተዐቅቦ ሊኖሩ በሚችሉበት መንገድ ባለመካሄዱ ገዳማውያኑ ምን ሊመጣ ይችላል? በሚለው መንፈስ ተረብሸዋል፡፡ አሁን ክርክሩ የተነሣበት ወቅት በዋልድባ ገዳም ዋናው የሱባኤ ጊዜ ነው፡፡ መነኮሳቱ እና መናንያኑ ከገዳማቸው አይወጡም፡፡ በዚህ ወቅት የነገሩ መነሣት በገዳሙ እና በምእመናኑ ዘንድ መንፈሳዊ ረብሻን ፈጥሯል፡፡ ነገሩ በመገባ ቢታብበት ኖሮ ይህንን ወቅት ማስቀደም ወይንም ማሳለፍ በተገባ ነበር፡፡
ለምሳሌ አሁን እርሻው በሚታረስበት አካባቢ ከጥንት ጀምሮ ቀብር እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ዐጽሙ ይፍለስ ከተባለ እንኳን ይህንን ጉዳይ ከገዳሙ ጋር ተነጋግሮ ገዳማዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ማከናወን ይገባ ነበረ፡፡
አዙረህ አዙረህ ካገሬ መልሰኝ
በሹም የታዘዘ አፈር አታልብሰኝ
እያለ በሚያንጎራጉር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የመቃብር ቦታ ያለውን ዋጋ ዘአስቀድሞ መተንበይ አስቸጋሪ አይመስልም፡፡ ዐጽሞቹ የት የት ይገኛሉ? መፍለስ ካለባቸው በምን ዓይነት ሃይማኖታዊ እና ሰብአዊ ሥርዓት? ማን ያፍልሳቸው? የት ይረፉ? የሚሉት እንደ አንድ ተግባር ሊታሰብባቸው ይገባ ነበር፡፡ ለነገሩ የአዲስ አበባ አጥቢያዎች በግዴለሽነት ያለ በቂ ሃይማኖታዊ፣ ሰብአዊ ሥርዓት እና ክብር ነባር ዐጽሞችን በሚያነሡበት በዚህ ዘመን መንግሥትን በዚህ ረገድ መውቀስ ከባድ ይሆናል፡፡ እነዚህ አበው እና እማት ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጸልዩ ናቸው፡፡ ጸሎታቸው እንጂ ኀዘናቸው ማንንም አይጠቅምም፡፡ ይህ የዋልድባ ገዳም ጉዳይ በተገቢው መንገድ ባለመያዙ ከዋልድባ አልፎ ሌሎችን ገዳማውያንም የሚያሳስብ ነገር እየሆነ ነው፡፡
ጉዳዩ እና ቤተ ክህነት
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ነባር ይዞታዎች በውል ለይቶ ማወቅ፣መብታቸውን ማስጠበቅ፣ በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሚዎች እንጂ ተጎጅዎች እናይሆኑ መጠበቅ፣ ችግሮች ሲፈጠሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም በሚያስከብር፣ የሀገርንም ዕድገት በሚራዳ መልኩ እንዲፈቱ ማድረግ የቤተ ክህነቱ ሥራ ነው፡፡
አሁን በታየው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ቤተ ክህነቱ ሕዝቡ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ፣ ችግሮች ቀድመው እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም እንዲታረሙ፣ ወሬዎች እንዳይጋነኑ፣ ማድረግ ይገባው ነበር፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶስም ከዚህ የሚበልጥ ጉዳይ አልነበረውም፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ልዑካንን ልኮ ተገቢውን መረጃ መሰብሰብ፣ በተሰበሰበው መረጃ ላይ የተመሠረተ መግለጫ መስጠት፣ ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገር እና የደረሰበትን ማስታወቅ ይገባው ነበር፡፡ ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም እንዲሉ፡፡ አስቀድሞም እንዲህ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ አሁን የተከሰተውን ችግር በማያ ስከስቱበት መንገድ እንዲከናወኑ የበኩሉን ማድረግ ነበረበት፡፡
ገዳማውያኑ ለአቤቱታ አዲስ አበባ ሲመጡ ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ችግራቸውን መስማት፣ ከሚመለከ ታቸው አካላት ጋር ማገናኘት፣ ጉዳያቸውን መከታተል እና የነገሩ ባለ ቤት ሆኖ መሥራት ይገባው ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ግን ችግሮችን የመፍታት ዐቅማችንን ሳይሆን ቤተ ክህነታችን ያለበትን ደረጃ የሚያሳዩን እየሆኑ ነው፡፡
«ኢውልድብና»
አንድን ሃይማኖታዊ፣ ታካሪዊ፣ ባህላዊ እና ጥንታዊ እሴትን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ፣ መብቱን እና ክብሩን ብሎም እሴቶቹን ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሌላ ጠቃሚ ነው የተባለን ነገር ማከናወን «ኢውል ድብና» ተብሏል፡፡ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ትውፊታዊ እሴቶችን ጠብቆ ለሀገራዊ ተግባራትን ማከናወን ደግሞ «ማወልደብ፣ ውልድብና»፡፡ ዋልድባ ላይ የደረሰውን መሠረት በማድረግ ነው ስሙን የወሰድኩት፡፡
ይኼ ጉዳይ ነገም የሀገሪቱ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ መነጋገርያ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ኢውልድብና መንግሥት እና ሕዝብን የሚቀያይም፣ የሕዝብን ተሳታፊነት የሚቀንስ፣ የሚሠሩ ተግባራት ቅቡል እና ዘላቂ እንዳይሆኑ የሚያደርግ፣ ነገሮችን በአንድ ዓይን ብቻ የሚያሳይ አሠራር ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት ጊዜ የገበሬውን ቅቡልነት ሳያገኙ የተሠሩ ተግባራት የደረሰባቸውን ማየቱ ብቻ ትምህርት በሆነን ነበር፡፡ አያሌ ቦታዎች በደን ተሸፈኑ፡፡ ደን አስፈላጊ ነገር ነበር፡፡ ይሁንታ ስላላገኘ ግን ደርግ ሲወድቅ ደኑ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ አንድ ነገር ጥሩ እና ጠቃሚ ስለሆነ ብቻ እድሜ አይኖረውም ሕዝባዊ ተቀባይነት ሲኖረውም ጭምር እንጂ፡፡
ኢውልድብና መልካሙ ነገር በመስተጋብር ችግር ምክንያት እንዲጠላ የሚያደርገ አሠራር ነው፡፡ ኢውልድብና አንድ ነገር በሚያስገኘው ቁሳዊ ውጤት ብቻ ከዐውዱ ውጭ እንዲታይ አድርጎ አካባቢያዊ ስሙምነት እንዳይፈጠር የሚያደርግ ነው፡፡
እናም አሁንም አልረፈደምና አሉ የሚባሉ ችግሮችን በቀና መንፈስ እንፍታቸው፡፡ ልማቱም ታሪኩም፣ እምነቱም፣ ቅርሱም ተጣጥመው የሚሄዱበትን መንገድ እንፈልግ፡፡ እንደ ሜዶን እና ፋርስ ሕግ የተቆረጠ የማይቀጠል ከምናደርገው፣ ነገሩን እንደገና ብናየው፡፡ እነዚህ መናንያን በኢንዱስትሪው ላይ ከሚያዝኑበት ቢባርኩት ይሻለናል፡፡
የሀገሬ ሰው «ገብስ እና ፈረስ የሚያጣላ» እንደሚለው የማይጣሉትን ጉዳዮች በኛ ችግር ምክንያት አናጣላቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን አካሄዳችን ዋልድባን መተሐራ፣ ስኳሩንም መራራ የሚያደርገው ይሆናል፡፡