ትውስታዬ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር (የመጨረሻ ክፍል)
ከይሁኔ ነጻነት
በክፍል አራት መለሰ ተ/ማሪያም አሰላ ሂዶ በምስኪን እናቱ ቤት ታንቆ መሞቱን ተርኬ ነበር ያቆምኩት።እነሆ የመጨረሻው ክፍል።
ራሱን ሰቅሎ የሞተው መለሰ ተ/ማሪያም ጥሩ አንባቢ፤ጸሃፊ እና ጨዋ ሰው ነበር።እርሱ አገሬ በሚላት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ምናምንቴዎች ስልጣኑን ይዘው ፍትህን ሲቀልዱበት ሲያይ ተስፋ ቆርጦ ራሱን ሰቅሎ ገደለ።ለዚህ ሰው ሞት ኃላፊነቱን የሚወስዱት ህወሃት የተባለው ዘረኛ ድርጅት፤የመስሪያ ቤቱ የብአዴን ተወካይ ዘሪሁን ረታ፤እና ተቀዳ ዓለሙ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው።
ተቀዳ አገሪቷ እንዲህ መከራዋ በዝቶ፤ዜጎቿ በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው ራሳቸውን ሲገድሉ ወይም ደግሞ ተሰደው በየደረሱበት ሲዋረዱ ዓይኑ እያየ ጆሮውም እየሰማ ድምጹን አጥፍቶ እንደመዥገር የአገሪቷን ወዝ የሚመጠምጥ ነው።ይህ ሰው አጼው በነበሩ ግዜ ውጭ ጉዳይ ገባ፤ደርጉ አጼውን ገድሎ ሲመጣ ተቀዳ ከዚያ ፈቀቅ አላለም፤ህወሃቱም መጥቶ “አማራ የትግሬ ቀንደኛ ጠላት ነው” ሲል አሁንም ተቀዳ ከዚያ ዞር አላለም።በምንስትር ማእረግ ያገለገለውን ደርግን በሃሜት ደሙን እየጠጣ አድጎና ተስፋፍቶ እርሱ ኑሮ የሚለውን እየኖረው ቀጠለው። ተቀዳ ዓለሙ አንድ ጋዜጠኛ አግኝቶት አንተ አማራ በመሆንህ የትግራይ ቀንደኛ ጠላት ነህ እንዴ ብሎ ቢጠይቀው “አይደለሁም” ማለት የሚችል አይደለም።አይደለሁም ማለት የነስዩም መስፍንን ፖሊስ መቃወም ስለሚሆንበት ህወሃት እንዲህ አይልም ብሎ እውነቱን ይክዳል እንጂ አይናገርም።ይህ ግለሰብ አንድ ግዜ ሚንስቴር ዴእታ፤ሌላ ግዜ ደግሞ ወርዶ አምባሳደር ሁን ሲሉት ሁን ያሉትን እየሆነ በከተቱት ሰገባ ውስጥ ሳይከፋው እየገባ ከስዩም የተራረፈውን እየለቃቀመና ደርግን በሃሜት ደሙን እየጠጣ ይኖራል።
ሌላው ደግሞ ዘሪሁን ረታ የሚባለው ሲሆን ህወሃቶች ከገቡ በኋላ ውጭ ጉዳይ የገባ ነው።ዘሪሁን ረታ አጭርና ብልጣ ብልጥ ነገር ነው።በመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ “ቀራጩ ዘኬዎስ” ተብሎም ይጠራል።ቀራጩ ዘኬዎስ ያሉትም ጉቦ ስለሚቀበል እንጂ በእጠሩት አይደለም።ጉቦ የሚቀበለውም ውጭ አገር ካሉ ዲፕሎማቶችና አምባሳደሮች ነው ተብሎ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ይወራል።እርሱ የአስተዳደርና ፋይናንስ ዋና ዳይሬክተር ስለነበረ ከየኢምባሲው የሚጠሩትንና ወደየ ኢምባሲው የሚመደቡትን ሥም ዝርዝር እያዘጋጀ ለስዩም መስፍን ያቀርባል።በዚህ መካከል በልዩ ልዩ መንገዶች ይቀርጣል እየተባለ ሲወራ ቆይቶ አንዱ “ቀራጩ ዘኬዎዝ” ብሎ ስም አወጣለትና ብዙዎቻችን ዘሪሁን የሚለውን ትተን ቀራጩ ዘኬዎስ እንለው ጀመር።
ዘሪሁን ረታ የአስተዳደርና ፋይናንስ ዋና ዳይሬክተር ሁኖ ሲሰራ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላይ ፎቅ ቤት ሰርቶ ጨርሷል።ከሰራው ቤት ግን ሳይገባበት አምባሳደር ሁኖ እስኪመደብ ድረስ ካዛእንቺስ አካባቢ የመንግስት ቤት ውስጥ ይኖር ነበር።በወቅቱ የዘሪሁን ደሞዝ ቢበዛ ሶስት ሺህ የኢትዮጵያ ብር ነው።ሙሉ ደመወዙን ሳይበላና ሳይጠጣ ለመቶ ዓመት ቢያጠራቅም እንኳ እንዲያ ያለ ቤት ሊሰራ አይችልም።ታዲያ ያን ሁሉ ብር ከየት አምጥቶ ነው ያን “ground plus “ ህንጻ ሊሰራ የቻለው ?በዚያን ግዜ ሚስቱስ የምታሽከረክረው መኪና ከየት የመጣ ነው ? ዘሪሁን ረታ ዘው ብሎ የገባበት የሙስና አዘቅት መኖሩን ላፍቶ ከተማ ላይ ጉብ ያለውና እዚያ አዲስ አበባ ላይ ሚስቱ ታሽከረክረው የነበረው መኪና ህያዋን ምስክሮች ናቸው።እንግዲህ ይህ ሰው እንደ ቀራጩ ዘኬዎስ ያደረገውን ሁሉ ተናዞ፤የደበቀውን አውጥቶ ለድሆች አድሎ ወደ ሰው ልጅነቱ ይመለስ ዘንድ እመኝለታለሁ።ያን ግዜ የእውነት ባለቤት የሆነው አምላክ ከእርሱ ጋር ይሆናል።እኛም ደስ ይለናል።
በምናምን የሞላዋት ሆዴ ላይ ያንጠለጠልኳትን ካራባት እየነካካሁ እንደ አደይ አበባ ፍክት ብየ እኖራለሁ ማለትን ከመረጠ ግን በነውረኞች መንገድ መሄድን መርጧልና የሚመሰገን ሰው አይሆም።ልጆቹም ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ ለመቆም ሃፍረት ይሆንባቸዋል።የአምባሳደር ዘሪሁን ረታ ልጅ ነኝ ማለትም የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሸማቅቅ ይሆንባቸዋል።
እንግዲህ ዘሪሁንም ተቀዳም እያዩ ከተባረሩት ሠራተኞች መካከል ሁለቱ ወዲያውኑ ሞቱ።
መለሰ ተ/ማሪያም የሰው ልጆችን በምንም ሁኔታ ለማስቀየምም ሆነ ለመጉዳት የማይፈልግ እና በጥንቃቄ ለመኖር ጽኑ እምነት የነበረው ሰው ነበር።ይሄ ጽኑ እምነቱ ነው ማንንም ሳይጎዳ ማንንም ሳይጠቅም ታንቆ እንዲሞት ያደረገው።ብዙዎቻ መሞቱ ካልቀረ ለምን ለዚያ ደረጃ ካደረሱት ሰዎች መካከል አንዱን ገድሎ አይሞትም ብለው እንደተናደዱበት አውቃለሁ።መለሰ ተ/ማሪያም ግን ማንንም በምንም ሁኔታ ለመጉዳት ፍላጎት አልነበረውም።ይሄ የእርሱ እምነት ነው።በዚህ መሠረት ለዚህ ያበቁትን ሰዎች ለሂሊና ፍርድ ትቷቸው ዳግም ላይመለስ ሂዷል።
ሰዩም መስፍን እንኳ ደም በማፈሰሰ ከኖረ ድርጅት ውስጥ የወጣና ደም ማፈሰስ ልማዱ ስለሆነ ሂሊናው ይወቅሰዋል ብለን አንጠብቅም።ስዩም ማታ የተኛትን ሴት ቀን በመርዝ ለመግደል ወደ ኋላ እንደማይል ከቀድሞ ጓዱ ሰምተን ተገርመናል።ከእርሱ ምንም በጎ ነገር አይጠበቅም።
ተቀዳ ዓለሙ፤ ዘሪሁን ረታ እና ሌሎች ግን ስሙ !!! ዓይኖቻችን በእናንተ ላይ ናቸው !!! “አማራ የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነው” ብሎ ከሚያስብ ሃይል ጋር ነው አብራችሁ የተሰለፋችሁት።እናንተ አማሮች ናችሁ። ግን ምን ዓይነት አማሮች ትሆኑ !? በእርግጠኝነት እነስዩም መስፍን “አህያ” እያሉ የሚሰድቧችሁ እንደእናንተ ዓይነቱን ሆድ አደር ነው።እናንተን አቶ ሃዱሽ ሳይቀር ይንቋችኋል።ምክንያቱም እነርሱ የሚያምኑበትን ሲያደርጉ እናንተ ልትቀበሉ የማይገባችሁን ለምትበሉትና ለምትጠጡት ከንቱ ነገር ስትሉ አለቦታችሁ አለሰገባችሁ ተገኝታችሁ ለአማራው ህዝብ ውረደትና መከራን አትርፋችኋል።እናንተን በኢትዮጵያ ደረጃ ከፍ አድርጎ ለማሰብ ሞራላችሁ ብቁ አይደለምና በታጠራችሁበት ድርጅት እየተለካችሁ ትመዘናላችሁ።ስለዚህ በህወሃት ዘንድ የተናቃችሁ፤በአማራው ህዝብ ዘንድ ደግሞ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
እኔና ሌሎች አርባ አንድ ሠራተኞች ተባረን ጦም ማደር የጀመርነው እናንተ ዓይናችሁ እያየ ነው።መለስ ተ/ማሪያምም ተስፋ ቆርጦ ራሱን አንቆ የገደለውም በእናንተ ዓይነት ሆድ አደሮች ምክንያት ተስፋ ቆርጦ ነው።ይሄን እንድታውቁት ይስፈልጋል።
ሌላው ሟች ደግሞ አቶ አክሎግ እምሩ የሚባል ነው።የአማሟቱ ሁኔታ ግልጽ አይደለም።እንደተሰማው ከሆነ ተከራይቶ የሚኖርበት ቤት ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።አቶ አክሎግ እምሩ ከአስር ዓመት በላይ በውጭ ጉዳይ የሠራ ቢሆንም ከትምህርቱና ከሥራ ልምዱ ጋር በማይመጥን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መድበውት በቁጭት የሚኖር ሰው ነበር።ምክንያቱ ደግሞ ከእለታት አንድ ቀን ሸራተን ይሁን ሂልተን ሆቴል ውስጥ ተደርጎ በነበረው ግብር ላይ አቶ አክሎግ ገስግሶ ሂዶ ስዩም መስፍንን “እኔን መቸ ነው የሚመድቡኝ ሲል ይጠይቀዋል” ሰዩምም እንዴት ደፍሮ እንዲህ ይጠይቀኛል ብሎ ቂም ቋጠረበት።ከዚያች ጥያቄ በኋላ አቶ አክሎግ እምሩ ከደረጃው ዝቅ ብሎ ወደ ማይመጥነው ቦታ ተመድቦ እንዲሰራ ተደረገ።ቅንጅት ሲመጣ ምክንያት ተገኘና “ዲ” ተሰጥቶት ከተባራሪዎቹ አንዱ ሆኖ አረፈው።ከተባረረም በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሞቶ ተገኘ ተብሎ ሰማን።በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ ብዙ ሠራተኞች በድንገት ሞተዋል።ለምሳሌ ደሳለኝ ዓለሙ የዓለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ተ/ዋና ዳይሬክተር ሆኖ በመስራት ላይ እያለ መታመሙ ሳይሰማ ሞተ መባሉን ሰምተናል።አምሳሉ መለስም የሚባል እንዲሁ በድንገት ሙቶ ተገኝቶቷል።ነፍሳቸውን ይማረው።
አሁን አሁን የገባኝ የህወሃት እና የሌሎች ኢትዮጵያዊያን ልዩነት የጭካኔና የሂሊና ጥያቄ ጉዳይ ነው።እነርሱ የጭካኔያቸው መጠን ልክ ሲያጣ ሌሎች የሚጨክን ልብ ማጣታችን።ደጋጎቹ ኢትዮጵያዊያን የሂሊናና የሞራል ጥያቄ ጠፍንጎ ይዟቸው ሰውስ እግዜርስ ምን ይለናል የሚሉ ሲሆኑ ህወሃቶች ከእነዚህ ነገሮች ጋር ፈጽሞ አለመተዋወቃቸው ከልዩነቶቻችን አንጓዎች መካከል ይመደባሉ።
42 ሠራተኞችን ለቃቅመው አባረው ጦም ሲያሳድሩ የሂሊና ወቀሳ አልነበረባቸውም።እኔንም የአገሪቷን አመራሮች ብቃት ትጠራጠራለህ ብለው ሲያባርሩኝ ቅንጣት ታክል ሃዘን አልተሰማቸውም ነበር።አንድ ጓደኛየንም ጠቅላይ ሚንስትሩን መላጣ ብለህ ሰድበሃል ብለው አባረውታል።ሌላውም የተባረረውም ከጓደኞችህ ጋር ስታወራ የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት “እንደ በሽተኛ ህጻን ይውተረተራል” ብለህ ተናገረሃል ተብሎ ነው።ህወሃት ማለት እንዲህ ነው።የመናገር ነጻነት ተክብሯል እያለ ገና ዜጎች ያሰቡትን እየለቀመ ለመከራ ይዳርጋል።ህወሃት ማለት የነጻነትን ጣእም ሳያውቅ ነጻ አውጪ ነኝ ብሎ ራሱን የሚጠራ የነውረኞች ስብስብ ነው።
በዚህ ጽሁፍ ስማቸው የተጠቀሱ ግለሰቦች የነውረኞች ድርና ማግ ሁነው ሥርዓቱን ለሃያ ዓመት በማቆማቸው ወቀሳ ይገባቸዋል።እነዚህ በየመሥሪያ ቤቱ ተሸጉጠውና ድምጻቸውን አጥፍተው የአገሪቷን ወዝ የሚመጠምጡ መዥገሮችን ሰው ሊያውቃቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።ተቀዳ ዓለሙን የመሰሉ ሆድ እንጂ ሂሊና የሌላቸው ባይበዙ ኑሮ መለስ ዜናዊ አገሪቷን እንዲህ ባላዋረደ ነበር።ዜጎችም እንዲህ ለመከራና ለስደት ባልተዳረጉ ነበር።በአገራችን ውስጥ እንዲህ ፍትህ ትርጉሟን ባታጣ ነበር።
ከዚህ በኋላ ልቤ ቂም እንደቋጠረ ተነሳሁና ወደ ወላጆቼ ክፍለ ሃገር ሄድኩ።ሁላችንም ተያይዘን ሃዘን ተቀመጥን።ምኞታችን ሲሞት፤ ተስፋችን ሲጨልም በራሳችን ላይ ትቢያ ነስንሰን ፤ማቅም ለብሰን ሃዘን ብንቀመጥ የሚፈርድብን ይኖር ይሆን ?ከላይ የተጠቀሱ ስሞችንስ መለሼ መልሼ ባነሳ ለምን ብሎ የሚጠይቀኝ ይኖር ይሆን?
አባቴም “ልጄ አንተንም አባረርሁ ሲል ተክዞ ጠየቀኝ”
አዎን እኔንም አባረሩኝ።
አየህ እነዚህ ሰዎች እንዲመጡ ትንቢት ተነግሯል።እንደመጡም የሚሄዱበት ግዜም እንደሚመጣ ተነግሯል።ጉንዳኖች ናቸው።ጉንዳን ሲገባ ጸጥ ብሎ ይገባል የሚፈጅውንም ፈጅቶ በየት በኩል እንደሄደ ሳይታወቅ ይጠፋል።
ይህን ትንቢት ማን እንደተናገረው የሚታወቅ ነገር የለም።በአገራችን እንዲህ ያሉ ምንጫቸው ያልታወቁ ብዙ የታመኑ ትንቢቶች አሉ።
ልጄ አንተ በእግዚአብሄር ታምናለህ አለኝ አባቴ።አዎን በእግዚአብሄር እንድታምን ሆነህ ነው ያደከው።አንተ ከእነዚህ ሰዎች የምትለየው በዚህ ነው።አንተ በእግዚአብሄር ታምናለህ እነርሱ ግን አግዚአብሄር ከላይ ሁኖ ሁሉን እንደሚያይ ነገም እንደሚፈርድባቸው አይረዱትም።አንተ ከእነርሱ ከፍ ትላለህ።አዎን እነርሱ ከሰው ልጅነት ስብእና የወረዱ እንደ አራዊት ኑረው እንደአራዊት የሚሞቱ ናቸው።ልጄ ሌላ ክፍ ነገር እንዳታስብ።ላንተ ያለውን ነገ አታጣውም አለኝ።
እናቴ እንደተከዘች ከበርጩማዋ ቁጭ እንዳለች ደጅ ደጁን ትመለከታለች እንጂ አስተያየት አትሰጥም። ህወሃቶች አባት፤ እናትንና ልጅን ባንድነት ያስለቅሳሉ ያሳዝናሉ። ከተባረርነው መካከልም አግብተው ልጅ ያላቸው የሚጦሯቸው አባትና እናትም ያሏቸው አሉ። ህወሃቶች የሚያስለቅሱት ሁለት ትውልድን ብቻ ሳይሆን አያት፤ አባትና የልጅ ልጅን ነው። ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት ሦስት ትውልድ በአንድነት ያለቀሰበት ዘመን ብለው መናገራቸው ይሄው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ተገልጧል።
እንግዲህ የዚህ ጽሁፍ ፋይዳ አጭርና ግልጽ ነው።ህወሃቶች የሚታወቁትንም የማይታወቁትንም ዜጎች እንዴት አድርገው በየቦታው እንደሚያሰቃዩ ማሳየት ነው።ህወሃት ዝም ልበል እንኳ ብትሉት ዝም ማለታችሁ እያባነነው ዜጎችን ለመከራ የሚዳርግ እጅግ በጣም ክፉ ድርጅት መሆኑን መመስከር የዚህ ጽሁፍ ሌላው ዓላማ ነው።በውጭ ጉዳይ ውስጥ ጥግ ጥጋቸውን ይዘውና ድምጻቸውን አጥፍተው የአገሪቷን ወዝ የሚመጠምጡትን በከፊልም ቢሆን ለዜጎች ማሳወቅ የዚህ ጽሁፍ ተጨማሪ ተልእኮ ነው።
ይህችን ጦማር ስጽፍ አባቴ ዳግም ወደማይመለስበት ዓለም ሂዷል።የትንቢቱንም ፍጻሜ አላየም።እኔ የትንቢቱን ፍጻሜ አያለሁ ብየ ተስፋ እያደረኩ ነው።እንደ ጉንዳን እንደገቡ እንደ ጉም ብን ብለው እነደሚጠፉ እያሰብኩ በተሰፋ እየኖርኩ ነው።ተስፋየም እውነት እንዲሆን የምችለውን አደርጋለሁ።
በመጨረሻም እግዚአብሄር ከላይ ከሰማይ ሁኖ እንባችንና ሃዘናችንን ይመለከታል።ዝም አይልም።እኔም ዝም አልልም።አሁን ስሜን አልናገርም።ለምን ብየ ጠላቶቼ ማን እንደሆንኩ ይወቁት ?የብእር ስሜን እነሆኝ።ነጻነት ለሁላችን ይሁን ነኝ።
ከዚህ ቀደም በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስትሰሩ የነበራችሁ ወገኖች ለወደፊቱ መረጃ መቀያየር ከፈለጋችሁ እነሆ ኢ-ሜይሌ [email protected].ገና በየኢምባሲው አማባሰደር ተብየ ደናቁርት ካድሬዎች የሚፈጽሟቸውን ዝሪፊያዎች እና በወገኖቻቸው ላይ የሚፈጽሙትን ወንጀሎች እናጋልጣለን።ዝም አንልም።
ቸር እንሰንብት!!
ነጻነት ለሁላችን ይሁን።