በድን ሬሣ የሚዘርፍ አረመኔ መንግሥት
ነፃነት ዘገዬ
አንዱ ወዳጄ እንዲህ አለኝ … “ጋሽ ነፃነት፣ ኑሮየን አንተም ታውቀዋለህ። ምኑን እነግርሃለሁ? አሁንስ ምርር ብሎኛል። የት አባቴን ልሂድ? እንደቆራጦቹ በሰውነቴ ላይ ላምባ አርከፍክፌ ልቃጠል ወይንስ ከአንዱ ፎቅ ወጥቼ ቁልቁል ልፈጥፈጥ? በገመድ ልታነቅ ወይንስ የዐይጥ መርዝ ልጠጣ? ዥው ባለ ገደል ልከስከስ ወይንስ እባቡሩ መንገድ አስፋልቱ ላይ ገብቼ በሚበር መኪና ልዳጥ? ምን ልሁን? እስኪ ፍረደኝ!
“ከነገ ዛሬ ይሻላቸው ይሆናል ብዬ ብጠብቅ እንኳንስ ሊሻላቸው ማነቆውን እያጠበቁ መጥተው መተንፈሻችንን ከናአካቴው ሊሰንጉን ምንም አልቀራቸው። አሁን ደግሞ ብለው ብለው ያለ ፈቃዴ ሙሉ ደመወዜን በዓመት ለዚህ መከረኛ የአባይ ግድብ መቁረጥ ጀመሩ። ደመወዜ እንኳንስ ተቀንሶበት ዕጥፍ ድርብ ሆኖ ቢሰጠኝም ወር እስከ ወር ቀርቶ አሥራ አምስት ቀንም አያኖረኝም። ምንድን ነው ይህ እየወረደብን ያለው የመከራና የሥቃይ ዶፍ? ለዚህ ሁሉ መቅሰፍታዊ ውርጅብኝ ጥፋታችን ምን ይሆን? አቶ መለስ ዜናዊ በልጅነቱ አሸንፎት የሚያውቀው አንድም ልጅ አልነበረም ማለት ነው? ማሸነፍ እኮ ብርቅ ሊሆንበት አይገባም ነበር። በቃ፣ በለስ ቀናው፤ አራት ኪሎን በምንም ይሁን በምን ተቆጣጠረ። ከዚያ በኋላ ሕዝብን ባልተለመደ ጭካኔ በመከራ ጅራፍ መግረፍና እንደጊንጥና እባብ መንደፍ ምን ይባላል? …”
የወዳጄ ብሶት እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። ብሶቱ ብሶቴም በመሆኑ በጥሞና አዳመጥኩት። እኔም ያለኝን ጨምሬ ለታዛቢ ላስመዝግብ ከሚል እሳቤ በመነሣት ብዕሬን ከወረቀት አገናኘሁ – አዋደድኩ ነው እሚሉት ጸሐፊዎች – ”ማዋደድ”ን ከግብርና ዕቃዎች ከድግርና ከሞፈር ቀምበር ማዋደድ ተውሰው።
በአንድ ትምህርት ቤት አንድ የሥዕል ይሁን የሒሳብ መምህር አንዲት የጦጣ ሥዕል ሠሌዳው ላይ በጠመኔ ስሎ ሲያበቃ ተማሪዎቹን ”የዚች ጦጣ ጅራት ስንት ሣንቲ ሜትር ወይም ሜትር ይሆናል?” ብሎ ይጠይቃቸዋል። ዕጃቸውን እያወጡ ግምታቸውን መናገር ይጀምራሉ። አንዱ ይነሳና ”አንድ ሜትር ይሆናል” ይላል። መምህሩም ”እሺ አንተ የዳረኛው ስንት ትገምታለህ?” ሲለው ”አምሳ ሣንቲ ሜትር ይመስለኛል”ይላል። መምህሩም ”ጥሩ” ይልና ሌሎች ግምቶችን መሰብሰቡን ይቀጥላል። ”አንቺ ስንት ትያለሽ?” ይላታል በአንደኛው የክፍሉ ጥጋት ከተቀመጡት – ”ሠላሣ ሣንቲ ሜትር ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ” ብላ ትመልሳለች። ”አንተኛውስ ስንት ትገምታለህ” – ”አሥር ሣንቲ ሜትር” – ”አንቺኛዋስ?” – ”አምስት ሣንቲ ሜትር ይመስለኛል ቲቸር” ትለዋለች። ይሄኔ መምህሩ በመገረም ”አሄሄ፣ እናንት ተማሪዎች – ብላችሁ ብላችሁ ይቺን ጦጣ ካለጅራት ልታስቀሯት ነው!” ብሎ መጠየቁን አቆመ ይባላል።
እኛ ግን አልታደልንም። የወያኔው የእፉኝት መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በየጊዜው በሚያወጣቸው ሀገር አፍራሽና ሕዝብ አስለቃሽ ሕግና መመሪያዎቹ መቅኖ አጥተን ስንቀር ካለአንዳች እርባና ያለው ሕይዎት በደመነፍስ መንገላወዳችንን ተመልክቶ ከገባንበት የበድን ኑሮ ነፃ ሊያወጣን የቻለ ኃይል ልናገኝ አልቻልንም። ስለዚህም እንደጦጣዋ ሆነናል – ምንም እንኳ የርሷ ምናባዊ ቢሆንም።
አቶ መለስ የሆነ አእምሮ ለዋጭ የተለዬ ምናባዊ ዓለም ውስጥ በገቡ ቁጥር አሣራችንን ቢያንስ በአንድ ቁጥር የሚያሳድግ ነገር አይጠፋም። እርሱ ወደዚያ የሰመመን ዓለም ውስጥ የሚገባበት አጋጣሚ ደግሞ ብዙ ነው ብቻ ሣይሆን በየቀኑ ነው ማለትም ይቻላል። ታዲያም ቃዥቶ በሚያስቃዣቸው ካድሬዎቹና ምስለኔዎቹ ጅራፍ እየተሸነቆጥን አሣራችንን የምንበላው ተራ ዜጎች በግርፋት ብዛት ሕይወታችን አልፎ በአሁኑ ወቅት በርግጥ በድን ሬሣችን ብቻ ቀርቷል ማለት ይቻላል። እባካችሁ አንባቢያን – እየኖረ የሚመስል በቁሙ የሞተ ሕዝብ እንዳለ በጊነስ የአስደናቂ ነገሮች መመዝገቢያ መጽሐፍ እንዲመዘገብልን ብታደርጉ ለወደፊቱ የማኀበራዊ ሣይንስ ልዩ ምርምር ሳይጠቅም የሚቀር አይመስለኝምና ግዴላችሁም ለባለ ሙያዎቹ ጠቁሟቸው።
የቁም ሞት ምን ይመስላል? ሕዝብስ በቁሙ ሞተ ሲባል ምን ማለት ነው? በኢትዮጵያ እነዚህ ነገሮች በከፍተኛና በ”አጥጋቢ ሁኔታ” ተሟልተው መገኘታቸውን ለመረዳት በሀገሪቱ ውስጥ ባለፉት ሦስትና አራት አሠርት ዓመታት የተመዘገቡ ትኩስ የታሪክ ክስተቶችን መቃኘት ይገባል። ያን ሁሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወነ ሀገርና ሕዝብ የማጥፋት ሁለንተናዊ ዘመቻና ውጤቱን በአንድ መጣጥፍ ማሳየት የማይታሰብ ነው። ይልቁንስ ወደወዳጄ ብሶት ለመልሳችሁ።
ወያኔ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም የራሱን ጩኸት እንጂ የማንንም አቤቱታና ዋይታ የማዳመጥ ፍላጎት የለውም። ”እንዲህ ያለ ነገር አማረኝ!” ማለት በፀረ ልማትነትና በአሸባሪነት የሚያስፈርጅ ወደዘብጣያም የሚያስወረውር ታላቅ የሀገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ማንም ደፍሮ ”ይህ ነገር አማረኝ፤ ዴሞክራሲ ጠማኝ፤ መልካም አስተዳደር በዐይኔ ውል አለብኝ፤ ፍትህ ርትዕ ናፈቀኝ፤ የሰብዓዊና የዜግነት መብቶች ራቡኝ፤ በገዛ የጋራ ሀገራችን አድልዖና መገለል፣ የበይ ተመልካች መሆንና የእንጀራ ልጅነት ሰለቸኝ፤ የራሴ የምለው የሀገር መሪና ብሄራዊ ጦር ማየት አሰኘኝ …” ብሎ መናገር አይደለም ማሰብ ራሱ ትልቅ ወንጀል ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የምንኖር ወገኖች ”ደመወዜን ካለፈቃዴ ለምን ትቆርጣላችሁ? ለኔ ለራሴስ መች በቃኝና ነው?” ብትል የሚሰማ የለህም ብቻ ሣይሆን ፀረ ልማት ነህ፤ እናም ምስህን ታገኛለህ። በትንሹ የትም እንዳትሠራ ተደርገህ እንደባራክ ኦባማ አባት ጊዜህን ለማሳለፍ በተንሻፈፈ ጫማ ባቡር መንገድ ለባቡር መንገድ ልትንገላወድ ትችላለህ።
በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት እየተካሄደ ያለው አረመኔያዊ ተግባር (Absolute Barbarism) በየትኛውም ዘመንና በማንም ሰብዓዊ ፍጡር አልተካሄደም። ሲገርፉህ አትግረፉኝ ብሎ መናገር ወንጀል የሆነባት፣ ሲያስርቡህ አታስርቡኝ ማለት የሚያሳስርባት፣ በግልጽ ሲያዳሉብህ እኔም ዜጋችሁ ነኝ ከወንድም እህቶቼ አትለዩኝ ባልህ የምትወነጀልባት፣ ሲበሉ ብታይ ሌላ ጊዜ እንዳታይ ዐይንህ የሚጠፋባት፣ በቁጭት ጣትህን ወደሰማይ እንኳን ብትዘረጋ በሰላ መራጃ ጣትህን የምትቆረጥባት፣ ለጋራ ዕድገት ብለህ ብትራመድ እግርህ የሚቆረጥባት፣ወደፈጣሪ እግዚኦ ብትል መዓት ጠሪ ተብለህ የምትፈረጅና የምትከለከልባት… ምናልባትም የዓለም ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። የሚያሳዝኑ መሪዎች ከሚያሳዝኑ ተመሪዎች ጋር ሁለቱም በተለያዬ ዐውዳዊ አገባብ እያለቀሱ እሚኖሩባት ሀገር ሆናለች – ኢትዮጵያችን። ዕንባና ደም ማረጋቸውን ግን አላቆሙም – ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር። የወጣ ይመለሳል። ያለቀሰ ይስቃል፤ ያስለቀሰ ያነባል። የገደለ ይገደላል፤ የተራበ ሲጠግብ የጠገበ ይራባል። የሱን ፍርድ በትዕግሰት እንጠብቃለን። …
የወያኔውን መንግሥት ከሌሎች መንግሥታት የሚለዩትን እጅግ ብዙ ነገሮች መናገር ይቻላል። በነገራችን ላይ ይሄ ዴሞክራሲ የሚሉት ፈሊጥ ብዙም አይገባኝም። ቀድሞ የመቀመጫየን ነው ያለችው ዝንጀሮዋ። ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው። 99.56 እና 99 ከመቶ እያገኙ ዴሞክራቶቸ ነን እሚሉትን የአፍሪካና አንዳንድ አስመሳይ የሌሎች አህጉራት መሪዎችን የቁጩ ሥራ እንተወውና በአውሮፓና አሜሪካም ይህ ዴሞክራሲ እሚሉት ፋሽን ብዙውን ጊዜ ከፋሽንነት ወጥቶ እውናዊ ጠቀሜታ ሲሰጥ አላየንም። ለዚህም ነው ለምሳሌ ”ሺም ታለበ መቶ ያው በገሌ” ከሚል አቋም በመነሳት ብዙው የአሜሪካ ሕዝብ ለምርጫዎች ደንታ ቢስ የሆነው። ሀብታሞች በገንዘባቸው እንደፈለጉ በሚጠመዝዙት የፖለቲካ ቁማርና የጨረባ ተዝካር ጊዜን ላለማጥፋት ብዙው ሰው – ሰለጠነ በሚባለው ሀገር ማለቴ ነው – በፖለቲካ ሲሳተፍ አይታይም። ያውቁታል።
ኦባማም ሄደ – ሮኒም መጣ – የሀብታሞችና የ”ምሥጢራውያኑ” አሰለጦች ሕግ እንደሆነ አይለወጥም፤ እንደነበረ ይቀትላል – በቀጥታም ሆነ በዕጅ አዙር። መፈክሩ ”የተጻፈው የፈለገውን ይሁን፤ ነገር ግን ፖለቲካው መሽከርከር ያለበት በኛው ሰው፣ ለኛው ጥቅምና ፍላጎት መሆኑ እስከወዲያኛው መቀጠል አለበት” የሚል ነው። አንግባባም አልልም። ይቺ የዓለም ጣጣ – ይቺ የገንዘብ፣ የሥልጣንና የሀብት ነገር እንደሀሽሽ ሱስ ናት። መላ ሰውነትን ታናውጣለች። ኀሊናን ትሠውራለች። የይሉኝታን ገመድ በጣጥሳ ትጥላለች። እንዲህ ነበር፤ አሁንም እንዲሁ ነው፤ ወደፊትም – ቢያንስ እኛ በምናውቀው ”ወደፊት”ም እንዲሁ ይቀጥላል። ሌላ ”ወደፊት” ወደፊት ከመጣ ያ ወደፊት ወደፊት እስኪመጣ ድረስ የምናውቃቸው አካሄዶች በእስካሁኑ እንደሚቀጥሉ እናምናለን።
ስለዚህ የኛይቱ ምርጫ ተብዬ መቼም ቢሆን ወስፋቴን እንደማታንጫጫ መግለጽ እፈልጋለሁ። ከዚያ ይልቅ አምባገነንም ሆኖ ፤ በሕዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያልተመረጠም ሆኖ ቢያንስ የጨካኝ አባትን ያህል እንኳን ሊንከባከበኝና የምለውን ሊያደምጠኝ የሚገባ መሪ እንዲኖረኝ ግን እፈልጋለሁ። በላም አለኝ በሰማይ ላምንና በዚያ የማይጨበጥ እሳቤ ልሰክር እንደማይገባኝ በተለይ አሁን አሁን ራሴን እያሳመንኩ መጥቻለሁ።
የኢትዮጵያን በዓይነቱ ለየትና ረቀቅ ያለ ጉዳይ ስናይ ደግሞ ሁኔታው አስቸጋሪ ባሕርይ እንዳለው እንገነዘባለን። መሪያችን ማን ነው? የችግሮቻችን ዋነኛ መባቀያ የት ነው? ከዚህ መውጣት የምንችለው እንዴት ነው? እኛ ተጨቋኞችስ በምን ሁኔታ ላይ ነው የምንገኘው? ሀገራችን ወዴት እያመራች ነው? የሕዝቡ ዕለታዊ ችግር ምን ያህል ሥር እየሰደደ ነው? … ብዙ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይቻላል። መልሱ ግን ከየት ይመጣል? ”መደበቅ” አይጠቅምም – በሁለቱም አቅጣጫ።
ባጭሩ ሁነኛና የኛን የብዙኃኑን ጥቅም በአግባቡ እሚያስጠብቅ መንግሥት የለንም ማለት እንችላለን። መንግሥት የሚባል ነገር ካለንም በመንግሥቱ መዋቅር ውስጥ በዘመድ አዝማድና በዘር ቅኝት እየተጠራሩ የሚሰገሰጉ በአመዛኙ የአንድ ዘውግ አባላትን ልዩ ጥቅም የሚያስከብር፣ ሌሎች የሀገሪቱ ዜጎችን በግልጽና በሥውር (በዓይነ ቁራኛና በጠመንጃ) የሚጠብቁ ወታደሮችንና ጆሮ ጠቢዎችን (አንድ ለአምስት) ደመወዝ በገፍ የሚከፍል(ያለችንን ጥቂት ጥሪት ለወንበሩ ጥበቃ እያሟጠጠ ያለ)፣ አድርባይ ተሽቆጥቋጮችን በጥቅም እየገዛ በወንድሞቻቸው አናት ላይ የሚያሰለጥን፣ የሀገሪቱን ጓዳ ጎድጓዳ ብልቅጥቅጥ አድርጎ ለጠላት በማሳየት ክፉ ቀን ቢመጣና ሲመጣ ሀገሪቱን ለማንም አጋሚዶ ሰጥቶ ለመኮብለል የተዘጋጀ፣ በሥልጣን ላይ እስካለ ግን በብድር፣ በዕርዳታና ባለው ውስን የሀገር ሀብት አንዳንድ ዐይነ ግቡ የልማት ሥራዎችን የሚሠራ(It’s just (fair) to give the devil its due)፣ በማይማንና ደናቁርት የእከክልኝ ልከክልህ ሕገ-ሙስና (ሕገ-ጥፋት) የተሰባሰቡ አውሬዎች መናኸሪያ የሆነ መንግሥት አለን – አለን ከተባለ አሁንም።
ይህ የደንቆሮዎች ስብስብ የሕዝቡን በድናዊ የሬሣ ዝምታ እንደስምምነት በመቁጠር ይሁን ሰዎቹ በሠፈረባቸው አጋንንት የማንአለብኝነት ወረርሽኝ እየተመሩ በየጊዜው የሚጭኑብን ሸክም ከአቅማችን በላይ ነው። በቫት ሰበብ ኑሮው ተሰቀለ። በቀረጡና ግብሩ መጨመር ሰበብ ኑሮው ተሰቀለ። በነዳጁና በዶላሩ ምንዛሬ ማሻቀብ ሰበብ ኑሮው ተሰቀለ። በማዳበሪያ ዋጋ፣ በትራንስፖርት፣ በዕቃዎች ዋጋ፣ … መናር ምክንያት ኑሮው ተሰቀለ። በአልጠግባይ ስግብግብ ነጋዴና የባለሥልጣን መመሣጠር ምክንያት ኑሮው ተሰቀለ። በየጊዜው በሚጣልብን መዋጮ ምክንያት ኑሮው ተሰቀለ። … ኑሮው ያልተሰቀለበት ሰበብ አይገኝም።
የቅርብ ጊዜው ፋሽን ደግሞ የአባይ ግድብ ነው። አባይ መገደቡ እሰዬው ነው። ተገድቦ በሚገኘው ንዋይ የሀገርን ልማት መደጎሙ ጥሩ ነው። ነገር ግን የተቀደሰም ይሁን ያልተቀደሰ ሰበብ አስባብ እየፈለጉ ይህን በድህነት የሚማቅቅ ሕዝብ እንደባብ አናት አናቱን መቀጥቀጥ ጥሩ አይደለም። የሚያዋጣ በፍቃዱ ያዋጣ። ደግሞም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን አቶ መለስን ጨምሮ ስንትና ስንት ባለሥልጣኖችና አላሙዲንን የመሳሰሉ ገንዘብን የት እንጣል የሚሉ ቱጃር ቢሊየነር ነጋዴዎች ባሉባት ሀገር ለዚህች ትንሽ ግድብ ድሃውን እስትንፋስ ማሳጣት በሃይማኖትም በምድር ሕግም ያስኮንናል፤ ያስወነጅላልም። ”በፍርድ ከተነዳች በቅሎየ አለፍርድ የተዘገነች ቆሎየ (ትጸጽተኛለች?)” እንዲሉ ደመወዝን ያህል አለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መነካት የሌለበት ነገር ማንም ባቃዠው ቁጥር የሚሸረከት ከሆነ ዜጎች እንደዜጎች ሀገርና መንግሥት አለን ብለው እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? አንድ ግለሰብ ወፈፍ ባደረገው ቁጥር ደመወዝ የሚቆረጥ ከሆነ የኑሮ ዋስትናው ምንድነው? ይህ የዕብደት ሥራስ መቼ ነው እሚያቆመው? ሰውዬውስ ከሽፍቶች የጎበዝ አለቃነት እንዴት ይለያል? ለነዚህ ጥያቄዎች ከአቶ መለስ መልስ እፈልጋለሁ – ምኞት ስለማይከለከል።
እጅግ በጣም ትልቅ ነውር ነው። ሲፈልግ መቶ ሺህ ግድብና መቶ ሺህ ድልድይ ይሠራ። ነገር ግን የራሱ መንግሥታዊ በጀት ሊኖረው ይገባል እንጂ በለመደባቸው ከቅጣትና ከዕርዳታ በታሳቢነት የሀገርን የበጀት ዕቅድ እንደሚነድፉት ሁሉ ከኔ ከምሥኪኑ ደመወዝ እየቆረጡ ለሀገራዊ በጀት እንዲመድቡ የጉልበትና የአምባገነንነት ካልሆነ በስተቀር አንዳችም ሕጋዊ መደላድል የላቸውም። በበኩሌ ይቺን የሚቆርጡብኝን ገንዘብ ከልጅ ልጆቻቸውም ቢሆን በሕግ አግባብ እንዲጠይቁና እንዲያስመልሱ ለልጆቼ ”አደራ በሰማይ አደራ በምድር” ብዬ እናዘዛለሁ። ወንጀል እኮ ነው ወንድሞቼና እህቶቼ! እኛ ፈርተን ዝም ብንልስ እንዴት ደመወዝ በጉልበት ይቆረጣል? ምን ዓይነት ሀገር ሆነች? እነሱ ተመችቷቸውና ተንደላቅቀው እንደሚኖሩት እኛም እንደነሱ የሆንን መስሏቸው ይሆን? አንጎላቸው ከምን ይሆን የተሠራው? መመርመር አለባቸው! ከምኔው ወደ ”መንግሥቱ ማረን” ገባን? ”የበላችው ያስገሳታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል”አሉ? ለነገሩ ይበለን። ጥፋቱ የኛው ነው። ለባቢሎናውያን ከዚህም የባሰ ቅጣት ቢመጣ ቀጭውን አያስፈርድበትም። ደግሞም በጥቅምም ይሁን በዓላማ የተከፋፈለ ሕዝብና መንግሥት እርባና እንደሌለው ቀድሞም የታወቀ ነው። ለጭካኔያዊ አገዛዝ ተመቻችተን የተገኘን እኛ። እነሱ ምን አጠፉ? በየከፈትንላቸው ቀዳዳዎች፣ እነሱም በሚፈጥሩብን ቀዳዳዎች በየጉያችን ከፋፋይ ሽብልቅ እየሰነቀሩ ይሄውና ማንም ዝምባቸውን እሽ ሳይል ሃያ አንድ ዓመት ዘለቁ። በዚህ መንገድ ከተጓዝን ቁጥር ሊገልጸው የማይችል ረጂም ዘመን ይኖራሉ። ልጆቻቸውን በ”መተካካት” ቻይናዊ ብልሃት እየተኩ ይደቁሱናል። ሳስበው ጨነቀኝ።እስኪ ለማኝኛውም አንድዬ ልብ ይስጠን።