የባላንጣዎች ደርግ
Doris Kearns Goodwin የጻፈቺውን Team of Rivals የሚለውን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ሰሞኑን እያነበብኩት ነበር፡፡ መጽሐፉ ስለ ታላቁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ስለ አብርሃም ሊንከን የተጻፈ ነው፡፡ በአሜሪካ ታሪክ እንደ አይከን ከሚታዩ መሪዎች አንዱ ነው አብርሃም ሊንከን፡፡
አብርሃም ሊንከን ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደር እጅግ የሚንቁት እና ብቃቱን የሚጠ ራጠሩት ተቀናቃኞች ገጥመውት ነበር፡፡ ከራሱ ከሪፐብሊካን ፓርቲም ሆነ ከዴሞክራቲክ ፓርቲ በሞያም፣ በልምድም፣ በታዋቂነትም እንልቃለን ብለው ከሚያስቡ ተቀናቃኞች ጋር ነበር የተፎካከረው፡፡
በወቅቱ የነበሩ ሚዲያዎች የአብርሃም ሊንከንን መመረጥ ዕድለኛ ስለሆነ ነው ነበር ያሉት፡፡ ምክንያቱም ተፎካካሪዎቹ ከእርሱ የተሻሉ ናቸው ተብለው ይታሰቡ ስለነበር ነው፡፡ አንድ በጥብቅና ሞያው እጅግም ያልታወቀ፣ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አንድ ዙር ብቻ ያገለገለ፣ ለሁለት ጊዜያት ያህል ለሴናተርነት ተወዳድሮ ያልተሳካለት ሰው ፕሬዚዳንት ሲሆን ሚዲያዎች ምን ያድርጉ፡፡
ሊንከን የተመረጠበት ዘመን በአሜሪካ ታሪክ እጅግ ወሳኝ ከተባሉት ዘመናት አንዱ ነው፡፡ በሰሜነኞቹ እና በደቡቦቹ መካከል ሀገሪቱን ለሁለት የሚከፍል መለያየት መጥቶ ነበር፡፡ በባርያ አሳዳሪዎች እና ባርነት ለአሜሪካ ርግማን ነው በሚሉት ተራማጆች መካከል የነበረው ክርክር እየተጧጧፈ መጥቶ ወደ ባላንጣነት እየተቀየረ ነበር፡፡
አብርሃም ሊንከን የፕሬዚዳንትነቱን ሥፍራ እንደ ያዘ ያደረገው ነገር ነበር መላውን አሜሪካ ያስገረመው፡፡ ካቢኔውን ያቋቋመው በእነዚያ ባላንጣዎቹ በነበሩት ተፎካካሪዎች ነበር፡፡ ዋና ዎቹ የሪፐብሊካን ተቀናቃኞች የነበሩትን የኒውዮርኩን ዊልያም ሴዋርድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኑ፣ ሪፐብሊካኑ የኦሐዮ ገዥ ሳልማን ቼዥ የገንዘብ ሚኒስትር ሆኑ፣ ሪፐብሊካኑ የሚዞሪ ግዛት ታዋቂ ፖለቲከኛ ኤድዋርድ ቤትስ ዋና ዐቃቤ ሕግ ሆነው ተሾሙ፡፡
ሌሎች ኃያላንን ደግሞ ከዴሞክራቲክ ፓርቲው አመጣ፡፡ እነዚህም ቢሆኑ የሊንከን የውስጠ ፓርቲ ተቀናቃኞች ነበሩ፡፡ ጌዲዮን ዌልስ የባሕር ኃይል ሚኒስትር ሆነ፤ ሞንት ጎመሪ ብሌይር ፖስት ማስተር ጄኔራል ተብለው ተሾሙ፡፡ ኤዲዊን ኤም ስታንተን የጦር ሚኒስትር ተደረጉ፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላል በዕውቀትም ሆነ በልምድ ከአብርሃም ሊንከን እጅግ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ሹመቱን የሰሙ ሁሉ እነዚህ ስመ ገናና ሰዎች ፕሬዚዳንቱን ይውጡታል ብለው ፈርተውለት ነበር፡፡ ከዚያም በላይ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሊንከን ጋር የማይስማማ ሰዎች በአንድ ካቢኔ መገኘት ያንን ካቢኔ የባላንጣዎች ደርግ (ደርግ ማለት የግእዝ ቃል ሲሆን ኮሚቴ ማለት ነው) አሰኘው፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደካማ እና ልምድ የሌለው፣ አሜሪካንንም ከችግር ሊያወጣ የማይችል እያሉ ይወቅሱት የነበረውን ሊንከንን ማመስገን እና ማድነቅ የጀመሩት ዋነኛ ባላንጣዎቹ ነበሩ፡፡ «ብቃት የሌለው አስተዳዳሪ» እያለ ይወቅሰው የነበረው ሪፐብሊካኑ ኤድዊን ስታንተን «ፍጹም ለመሆን የተቃረበ» ሲል ሊንከንን አደነቀው፡፡ ሴዋርድ አብርሃም ሊንከንን ከማድነቅ አልፎ የሊንከን የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪና የቀርብ ወዳጁ ሆነ፡፡
በመጀመርያዎቹ ጊዜያት ስለ ሊንከን ሲያስብ «አሜሪካ በአጋጣሚ ያገኘችው ደካማ መሪ» ይል የነበረው ኤድዊን ሳንተን የአሜሪካውን ጠቅላይ የጦር አዛዥ ሊንከንን አድናቂ ሆነ፡፡ እንዲያውም ሊንከን ከሞተ በኋላ ለብዙ ሳምንታት ዕንባውን መቆጣጠር እየተሳነው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያለቀስ ነበር፡፡ ከሊንከን የተሻለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመመረጥ ባለመታከት ይለፋ የነበረው ኤቨን ቼዝ በመጨረሻ ላይ ሊንከን ከእርሱ እጅግ የሚበልጥ መሪ መሆኑን ራሱ መሰከረ፡፡
በዚህ ሁኔታ ነበር አብርሃም ሊንከን አሜሪካን ከእርስ በርስ ጦርነት እና ከባርነት መርገም ያወጣት፡፡ በ1876 እኤአ ታዋቂው ተናጋሪ ፍሬዴሬክ ዳግላስ አፍሪካ አሜሪካውያን ለአብርሃም ሊንከን ያሠሩትን የመታሰቢያ ሐውልት ሲመርቅ «ማንኛውም ሰው ስለ አብርሃም ሊንከን እውነተኛ ነገር ሊናገር ይችል ይሆናል፤ አዲስ ነገር ግን መናገር አይችልም» በማለት እንደተናገረው አብርሃም ሊንከን ትውልደ ትውልድ አሜሪካውያን ሁሉ የሚያውቁት እና የሚያደንቁት፤ ታሪኩን እንደ ሕዝብ መዝሙር በቃላቸው የሚሸመድዱት፣ በየንግግራቸው የሚጠቅሱት እና የሚያሞግሱት መሪ ለመሆን ቻለ፡፡
የመጀመርያው አፍሪካ አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት ሆኖ የተመረጠው ባራክ ኦባማ እንኳን የፕሬዚዳንትነቱን ቃለ መሐላ ሲፈጽም በዚሁ ተፈቃሪ ፕሬዚዳንት በአብርሃም ሊንከን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር የማለው፡፡
አገር ከአጣብቂኝ ወጥታ አብዛኛውን ሕዝብ ወደሚያግባባ እና ወደሚያስተባብር ጎዳና እንድትሻገር፣ ክርክሩ ለጠብ እና ለመለያየት መሆኑ ቀርቶ እንደ ቢላዋ ስለት ተፋጭቶ አንድ ነገር ለመቁረጥ እንዲውል ለማድረግ ከተፈለገ ሀገር በባላንጣዎች ደርግ መመራት አለባት፡፡
አንድ ዓይነት ከበሮ ሲመታላቸው ተመሳሳይ እስክስታ የሚወርዱ፣ ለምን? እንዴት? የት? ማን? ሌላስ? ብለው መጠየቅ የማይፈልጉ ሰዎች ተባብረው የሚመሩት ሀገርም ሆነ ተቋም እንደ ረግረግ ጭቃ ችግሩን እዚያው ላይ ሲወ ቅጥ ይኖራል እንጂ ከችግሩ መውጣት አይችልም፡፡
ብዙዎቻችን በሃሳብ እና በአመለካከት ከሚመስሉን፣ ሃሳባችንን ከሚደግፉ እና ያልነውን ሁሉ ይሁን ይደረግልን ብለው ከሚቀበሉ ሰዎች ጋር ለመሥራት ዝግጁዎች እና ፈቃደኞች ነን፡፡ ከማይደግፉን እና ከሚቃወሙን፣ ከኛ የተለየ ሃሳብ ካላቸው እና ከማይስማሙን ሰዎች ጋር መሥራት ግን ይከብደናል፡፡
ሊንከን ይቃወሙት የነበሩትን ባላንጣዎቹን ወደ ካቢኔው ሲያመጣ ለተወሰነ ጊዜ ችግር እንደ ሚገጥመው አጥቶት አልነ በረም፡፡ ግን በራሱ የሚተማመን ሰው ነበረ፡፡ እነዚያ ባላንጣዎቹ መቃወም ብቻ ሳይሆን በዕውቀት እና በልምድ ከእርሱ የተሻሉ መሆናቸውን እያወቀ ነው ያመጣቸው፡፡ በራሱ ይተማመን ስለነበር ግን ስማቸው ከእኔ በላይ ይገናል፣ እኔን ይረቱኛል፣ ይንቁኝ ይሆናል፣ የሚሉ ስሜቶች አልነበሩትም፡፡ የእነርሱን ብርታት የሚያውቀውን ያህል የራሱንም በርታት ያውቀዋል፡፡
ጀግና መሪ ማለት ከእርሱ ከሚበልጡም ሆነ ከእርሱ ከሚያንሱ፣ ብሎም ከእርሱ ከሚስተካከሉ ሰዎች ጋር መሥራት የሚችል መሪ ነው፡፡ ጀግና መሪ ማለት እንዳልከው ይሁንልን ከሚሉት ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ያልከውን አልተቀበ ልነውም፣ እኛ ደግሞ በዚህ እና በዚያ መንገድ አይተነዋል ከሚሉት ተቀናቃኞቹ ጋር መሥራት የሚችል ነው፡፡
ሊንከን እነዚህን ሰዎች ወደ ካቢኔው ሲያመጣ የሰዎችን ተቃውሞ አይደለም ያየው፡፡ እነዚህ ሰዎች ልዩ ልዩ አሜሪካ ውያንን ይወክላሉ፡፡ የእነርሱ ብቻ ሳይሆኑ የብዙዎቹም አፎች ናቸው፡፡ ይህ የእነርሱ ሃሳብ ያዋጣል ብለው የሚያስቡ አያሌ አሜሪካውያን ነበሩ፡፡ ስለዚሀም ለእነዚህ ሃሳቦች ዕድል መስጠት ፈለገ፡፡ እነዚህ ሃሳቦች ብቻቸውን ብቁ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ከሌሎች ሃሳቦች እና አመለካከቶች ጋር ሲፋለሙ እና ሲዋሸዱ ግን ለሁሉም አሜሪካዊ የሚጠቅም የተሻለ ሃሳብ ይፈልቃል፡፡ ስለዚህም የወዳጅ የቀናቃኞች ካቢኔ አቋቋመ፡፡
ለሀገር የማይጠቅም ሃሳብ የለም፡፡ ግን ብቻውን ለሀገር የሚጠቅምም ሃሳብ የለም፡፡ ማንኛውም ሃሳብ የሰዎች ሃሳብ ነው፡፡ የሰዎች ሃሳብ ደግሞ ውሱንነት አለበት፡፡ በዚህ ዓለም አንድ እና ብቸኛ መፍትሔ የለም፡፡ ከሌሎች የተሻለ መፍትሔ ግን ሊኖር ይችላል፡፡ ያ መፍትሔ ከሌሎች የተሻለ ነው ማለት ግን ብቻውን ፍጹም ነው ማለት አይደለም፡፡ የሕክምና ሰዎች የተሻለ መድኃኒት የሚሉት የተሻለ የማዳን ኃይል ያለውን እና አነስተኛ ተጎንዮች ጉዳት የሚያመ ጣውን ነው፡፡ ምንም የጎንዮች ችግር የማያመጣም ሆነ መቶ በመቶ ፍቱን የሆነ መድኃኒት ግን የለም፡፡
ከታችኛው ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግሥት መዋቅራዊ አካል፤ መንግሥታዊ ባልሆኑ ሌሎች ተቋማት እና ማኅበራት ውስጥም ቢሆን አለቆች እና መሪዎች በዙርያቸው ሊሰበስቧቸው የሚያስፈልጓቸው ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት የሚሉትን ብቻ ከሆነ ራሳቸውን በራሳቸው ለመግደል ተዘጋጅተዋል ማለት ነው፡፡ የሚቃወሙን፣ የሚሞግቱን፣ ስሕተታችንን የሚያሳዩን፣ የተሻለ ሃሳብ የሚያመጡልን፣ እኛንም ጭምር የሚያስንቁን ሰዎችም በዙርያችን ያስፈልጋሉ፡፡
አንድ ካቢኔ፣ ምክር ቤት፣ ቡድን፣ ኮሚቴ፣ ማኅበር፣ ተቋም፣ ቦርድ፣ ኅብረት፣ ወዘተ ሲቋቋም የተለያዩ ሃሳቦች እና አመለካከቶች ውክልና ያላቸው፣ ክርከሩን እና ውይይቱን የሚያሞቁ፣ የተለየ መንገድ የሚያዩ፣ በድፍረት ሊገዳደሩ የሚችሉ፣ ግን በመጨረሻ ለአንድ ዓላማ የሚሠሩ ሰዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
ሰው ሲፈጠር መጀመርያ የተቋቋመው ተቋም ቤተሰብ ነው፡፡ የመጀመርያው ቤተሰብ የተመሠረተው በአዳም እና በሔዋን መካከል ነው፡፡ የእነዚህን የሁለቱን አፈጣጠር፣ ሥነ ልቡና፣ ፍላጎት፣ ዐቅም፣ ጠባይ፣ ከተመለከትን አብረው መኖር አይገባቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን የተፈጠሩት አብረው እንዲኖሩ ነው፡፡
ያ ብቻም አልነበረም፡፡ የሀገራችን ሊቃውንት ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያብራሩ ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ተፈጠረ ይላሉ፡፡ አራቱም እርስ በርሳቸው የሚቀዋወሙ ናቸው፡፡ እሳት እና ውኃ፣ አፈር እና ነፋስ፡፡ እሳትን ነፋስ ያቀጣጥለዋል፣ እሳትን ውኃ ያሞቀዋል፣ እሳትን ውኃ ያጠፋዋል፣ አፈርን ውኃ ይወስደዋል፣ አፈርን ነፋስ ያጉዘዋል፣ ነፋስን የአፈር አቀማመጥ (የመልከዐ ምድር ሁኔታ) ይገታዋል፡፡ ሁለቱ ረቂቅ ናቸው፤ ነፋስ እና እሳት፡፡ ሁለቱ ግዙፍ ናቸው፣ አፈር እና ውኃ፡፡ አንዱ ቋሚ ነው፣ አፈር፣ አንዱ ረቂቅ ቋሚ ነው፣ እሳት፤ አንዱ ፈሳሽ ሯጭ ነው፣ ውኃ፣ አንዱ ፈጣን ሯጭ ነው፣ ነፋስ፡፡
ሁለቱ ቀሊል ናቸው፣ እሳት እና ነፋስ፡፡ ሁለቱ ከቢድ ናቸው፣ አፈር እና ውኃ፡፡ ሁለቱ ቀሊል ሆነው ወደላይ ሲንጠለጠሉ፣ ሁለቱ ከቢድ ሆነው ወደታች ይመዝናሉ፡፡ ሁለቱ ከቢድ ሆነው ወደታች ስበው እንጦሮጦስ እንዳይከቱ፣ ሁለቱ ቀሊል ሆነው ወደ ላይ ይስባሉ፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልን ስናይ ሰው ራሱ «የባላንጣዎች ደርግ» ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የባላንጣዎች ደርግ የሚያስፈልጋቸው የመግባቢያ ሰነድ ነው፡፡ ይህቺ ሀገር ምን እንድትሆን እንፈልጋለን? የት እንድ ትደርስ እንፈልጋለን? ዓላማችን ምንድን ነው? ግባችን የት ነው? እዚህ ላይ ከተስማማን መንገድ ልዩ ልዩ ነው፡፡ ሃሳብ ልዩ ልዩ ነው፤ መፍትሔ ልዩ ልዩ ነው፣ አማራጭ ልዩ ልዩ ነው፡፡ ሞያ ልዩ ልዩ ነው፣ ችሎታም ልዩ ልዩ ነው፣ ስልትም ልዩ ልዩ ነው፡፡
እንደ ሊንከን ዓይነት በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ከሚበልጧቸው እና ከሚቀናቀኗቸውም ጋር ለመሥራት ዐቅሙ ያላቸው፤ የራሳቸውን ክብር ሳይሆን የሀገርን ጥቅም የሚያዩ ሰዎች እንደ ጅራታም ኮከብ ከዘመናት አንዴ ብቅ ሲሉ ነው የሚታዩት፡፡ ብዙ ጊዜ የሚገኙት እንደ እኒህ ቀጣሪ ዓይነት ናቸው፡፡
ሰውዬው ለኩባንያቸው የሂሳብ ባለሞያ መቅጠር ፈልገው ማስታወቂያ አወጡ፡፡ በማስታወቂያው መሠረትም አራት ሰዎች ለቀለ መጠይቅ ቀረቡ፡፡ ጠያቂው ሰውዬው ነበሩ፡፡ የመጀመርያው ተወዳዳሪ ገባ፡፡ «ቀላል ጥያቄ ነው የምጠይቅህ» አሉት ሰውዬው፡፡
«ሁለት እና ሁለት ስንት ነው»
ተወዳዳሪው ገርሞት እየሳቀ «አራት» አላቸው፡፡
«አላለፍክም» ብለው አሰናበቱት፡፡
ሁለተኛው ገባ፡፡ የመጀመርያው የሆነውን ነግሮት ነበር፡፡
«ሁለት እና ሁለት ስንት ነው?» አሉት
«ሦስት» አላቸው፡፡
«አላለፍክም» ብለው ይሄንንም አሰናበቱት፡፡
ሦስተኛው ገባ
«ሁለት እና ሁለት ስንት ነው ትላለህ?» አሉት ቀጣሪው
«አምስት» አላቸው፡፡
«አልመለስከውም» እርሱም ተሰናበተ፡፡
በመጨረሻ አራተኛው ገባ፡፡
«ሁለት እና ሁለት ስንት ነው?» ተመሳሳይ ነበር ጥያቄው፡፡
«እርስዎ ስንት ቢሆን ይፈልጋሉ´ አላቸው፡፡ ተደንቀው ዓይን ዓይኑን አዩትና «የምፈልገው እንዳንተ ዓይነት ባለሞያ ነው» ብለው ቀጠሩት ይባላል፡፡
