የዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ራእየ ዮሐንስ – የዓለም መጨረሻ” መጽሐፍ ተመረቀ(አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤)
የዲ/ን ዳንኤል ክብረት “ራእየ ዮሐንስ – የዓለም መጨረሻ” መጽሐፍ ተመረቀ
(አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤)
18ኛ መጽሐፉ ነው ተብሏል
ከመጽሐፍ ቅዱስ(ዐሥራው) መጻሕፍት ሁሉ በስፋት ያልተተረጎመው የዮሐንስ ራእይ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ራእዩ በምሳሌዎች፣ ምልክቶች እና ትንቢቶች በመሞላቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከአንድምታ ትርጓሜው ባሻገር የዮሐንስ ራእይ ከክብደቱ አኳያ ተጨማሪ ማብራሪያዎች እና መረጃዎች እንደሚያስፈልጉ የነገረ ቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያስረዳል፡፡ በዚህ ረገድ የተሻለ መረጃ ለአንባብያን በማቅረብ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ”ራእየ ዮሐንስ – የዓለም መጨረሻ” በሚል ርእስ ያዘጋጀውን መጽሐፍ ባለፈው የካቲት 2 ቀን 2004 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ በሚገኘው ትሪያንግል ሆቴል አስመርቋል፡፡
በመጽሐፉ ዝግጅት ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ምንጮች የተገኙ 78 መጻሕፍት በቀጥታ ማጣቀሻነት ጥቅም ላይ መዋላቸው ተመልክቷል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ኀያላን ሴቶች እየተባሉ ከሚጠሩት አንዷ የሆኑት የጎንደሯ እቴጌ ምንትዋብ አጽፈውና ዐሥለው ለጎንደር ቁስቋም ማርያም ካበረከቱትና ከራሳቸው ጋ ለዐፄ ኢያሱ ሁለተኛ (1730 – 1755) መታሰቢያ ከሆነው ራእየ ዮሐንስ መጽሐፍ(ብራና) ቅጅ እንዲሁም ደጃዝማች ውቤ አጽፈውና ዐሥለው ለደረስጌ ማርያም ከሰጧቸው ቅጅዎች ላይ የተወሰዱ ሥዕሎችም በአስረጅነት ተካተውበታል፡፡
ለመጽሐፉ ዝግጅት አራት ዓመታትን መውሰዱን ዲያቆን ዳንኤል በምረቃው መርሐ ግብር መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡ በአራቱ ዓመታት ውስጥ 5000 የብራና ማይክሮፊልም መጻሕፍት በሚገኙበት አሜሪካ – ሚኒሶታ ቅዱስ ዮሐንስ ኮሌጅ፣ በጎንደር(ቁስቋም ማርያም፣ ደረስጌ ማርያም፣ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት)፣ በመንበረ ፓትርያሪክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ የብራና መጻሕፍትን ለመመልከት ተሞክሯል፤ የአርመን፣ ሶርያ፣ ግሪክ እና ግብጽ-ኮፕት ምንጮችን ለመዳሰስ ጥረት ተደርጓል፤ ቅዱስ ዮሐንስ ራእዩን ባየባትና ጥንት በታናሽ እስያ ዛሬ በቱርክ ምዕራባዊ ጠረፍ በኤጅያን ባሕር የምትገኘውን የፍጥሞ(ፓትሞስ) ደሴት ለስድስት ሰዓት በመርከብ ተጓጉዞ በማቋረጥ በአቡቀለምሲስ ዮሐንስ ገዳም ከስምንተኛው መ/ክ/ዘ አንሥቶ በዋሻው ውስጥ የሚገኙ ሥዕሎችና የቃል አስረጅዎች ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል ተብሏል፡፡ በምረቃው ሥነ ስርዓት ላይ ‹‹The Holy Patmos›› በሚል ርእስ የተዘጋጀውና በደሴቲቱ የሚገኙ 365 አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስቃኘው የ30 ደቂቃ ፊልም ለተመልካች ቀርቧል፡፡
በ”ራእየ ዮሐንስ – የዓለም መጨረሻ” መጽሐፍ ምረቃ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” መጽሐፍ አዘጋጅና የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር ጉባኤ አባል ዲያቆን ዓባይነህ ካሴ፤ “የመጽሐፉ አዘጋጅ ከራሱ ሐሳብ ተቆጥቦ በርካታ የዐሥራው መጻሕፍትን ትርጓሜ ከተለያዩ ድርሳናት ጋ በማመሳከር፣ የቅዱሳት ሥዕላትን ሐሳብ ሳይቀር በአስተርጓሚነት (አስረጅነት) በመጠቀም በብዙዎች ዘንድ ያልተሞከረውን የደፈረ፤ ከባዱንና ረቂቁን ራእየ ዮሐንስን ለመምህራን፣ ጸሐፊያንና አንባብያን በአንድ ደረጃ ያቃረበ ነው፤ አዘገጃጀቱም ለመሰል ጸሐፊዎች ትምህርት የሚሰጥና ደረጃውን ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ዲያቆን ዓባይነህ በቀጣይ የአዘጋጁ ሥራዎች ከወቅቱ አኳያ መታየትና የበለጠ መብራራት ይገባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦችም አመልክተዋል፡፡ ከእኒህም መካከል ቅዱስ ዮሐንስ ራእዩን ላሳየው መልአክ ስላቀረበው ስግደት(ዮሐ. 19 እና 22)፣ የቁጥሮችን ሐሳብ በተለይም ሺሕ ዓመትን እና 144 ሺሕን በተመለከተ ስላለው የአተረጓጎም ልዩነት፣ ከሌሎች የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ራእዩ የተጻፈበት ዘመን ቅድምና፣ ከቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእዚናንዙ ጽሑፍ አንጻር፣ የዮሐንስ ራእይ ቀኖናዊነት ጉዳይ፣ አዘጋጁ በተደጋጋሚ ለምስክርነት የተጠቀሙበት የቪክቶርያነስ ትርጓሜ፣ የተርጓሚው ማንነት የሚሉትና ሌሎችም ነጥቦች ይገኙባቸዋል፡፡
የዲያቆን ዳንኤል ክብረት 18ኛ መጽሐፍ እንደሆነ የተገለጸው “ራእየ ዮሐንስ – የዓለም መጨረሻ” በአግዮስ የኅትመት እና ጠቅላላ ንግድ ሓላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የታተመ ሲሆን በ221 ገጾች የተካተቱና በአምስት ክፍሎች የተከፋፈሉ ማብራሪያዎችን፣ መረጃዎችንና ሥዕላዊ መግለጫዎችን የያዘው መፅሃፉ፤ ዋጋው 80 ብር ነው፡፡