የመጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር እንዲዘጋ ተደረገ

(ፍኖተ-ነጻነት) — የኦሮሞ መጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር የቦርድ አባላት አቶ ለገሰ ገ/ሥላሴ፣ አቶ ሙለጌታ ሪቂቱ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 3ኛ ዓመት ተማሪ የነበረው ሲሳይ ሰርቤሳ ነሐሴ 16 ቀን 2003 ዓ.ም የሚከበረውን የእሬቻን በዓል ለማክበር ወደ ቤተሰቦቻቸው ግንደበረት ከተማ ሄደው ነሐሴ 17 ቀን 2003 ዓ.ም ሲመለሱ ጊንጪ ከተማ ተይዘው መታሰራቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት በሄዱበት አካባቢ ለኦነግ ቅስቀሳ አድርጋችኋል በሚል እንዲታሰሩና አቃቤ ህግም በሽብር ተግባር ጠርጥሮ እንደከሰሳቸው ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተጠርጣሪዎችም በዓሉን በትውልድ አካባቢያቸው እንዲያከብሩ በደብዳቤ ጥሪ ተደርጐላቸው እንደሄዱ የተጠቆመ ሲሆን ያለፈው ሳምንት መጋቢት 3 ቀን 2004 ዓ.ም በ8 ሰዓት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 3ኛ ወንጀል ልደታ ምድብ ችሎት የአቃቤ ህግ የምስክሮች ቃል በነሱ ላይ መደመጡ ተጀምሯል፡፡ መጋቢት 4 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ደግሞ ቀሪ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል እንደሚሰማ ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡

የፌደራል ማኅበራት ማደራጃ ኤጀንሲም የማህበሩን አባላት ፈቃድ አልጠየቃችሁም በሚል በደብዳቤ እንዲዘጋ መወሰኑን የማህበሩ አባላት በተለይም ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡ የማህበሩ አባላት በበኩላቸው ማህበሩ ዕውቅና የተሰጠውና ነባር እንደሆነ በመግለፅ ለዚህም አስፈላጊው ማረጋገጫ ሰነዶች በእጃቸው እንዳለ አስታውቀዋል፡፡