ከአዲግራት እስከ ዛላንበሳ፤ ቁርጥራጭ ማስታወሻዎች (ክፍል ሁለት፤ የመጨረሻ)

(መሀመድ ሰልማን)

ወደ ዛላንበሳ

የአዲግራቱ ወያላ “ዛላንበሳ! ዛላንበሳ! አሀደ ሰብ ዛላንበሳ!” እያለ ጮኾ ተጣራ፡፡ ስጠጋው ጊዜ “እተው እተው…ቀልጥፍ” አለኝ፡፡ ተሳፈርኩኝ፡፡ ከአዲግራት ወደ ዛላንበሳ ለመሄድ የ10 ብር ታክሲ መያዝ በቂ ነው፡፡ ሚኒባሱ እኔ ከተቀመጥኩበት የኋላ ወንበር ስር ኩልል ያለ ድምፅ የሚያወጣ ሰፒከር ተገጥሞለታል፡፡ በስፒከሩ ኤርትራዊው አብረሃም አፈወርቂ ለብቻው ነግሶበታል፣ ኢሳያስ አፈወርቂ በአሥመራ ብቻቸውን እንደነገሡት አይነት፡፡ “ሰማይ፣ ፊቅረይ፣ ፊሺክ በሊ፣ ሚስጥር ፊቅሪ፣ ሀደራ፣ ሺኮር ….” የተሰኙትን ዜማዎች እያከታተለ ይጫወታል፡፡

በጦርነት የወደመው የዛላንበሳ ፋብሪካ

የታክሲው መጋረጃ “ይከፈት-አይከፈት” በሚለው ክርክር ውስጥ ከጎኔ ከተቀመጠው ጎልማሳ ሰው ጋር ተግባባሁ፡፡ በትግርኛ የተጀመረው ትውውቃችን እኔ ቋንቋው ላይ ባሳየሁት መደነቃቀፍ ወደ አማርኛ ተሸጋገረልኝ፡፡ ጎልማሳው ሰው ጥርት ያለ አማርኛ ይናገራል፡፡ በጥያቄ አጣደፍኩት፡፡ በግራና ቀኝ የምናልፋቸውን ተራራዎች እያመለከተ ስምና ውለታቸውን ተረከልኝ፡፡ በክፍሉ ታደሰ “ያ ትውልድ” ቅፆች ብቻ አውቀው የነበረውን የአሲምባ ተራራን በስተቀኛችን በርቀት አመላከተኝ፡፡ የአይጋ ተራራዎችንም እንዲሁ፡፡ ከኤርትራ ጋር ያደረግነውን ውጊያ አነሳሁበት፡፡
“እንደሚባለው ብዙ ሰው ሞቷል እንዴ?” ፈራ ተባ እያልኩ ጠየኩ።

ምላሹን በለበጣ ፈገግታ ብቻ ገለጸልኝ፡፡ ለተወሰነ ርቀት በዝምታ ከተጓዝን በኋላ አንዲት ኮረብታ አመላከተኝ፡፡ “እዚህች ጋ ብቻ አንድ ሻለቃ አልቃለች፡፡” ለወታደራዊ ቋንቋዎች ባእድ ስለሆንኩ አንድ ሻለቃ ስንት ወታደር እንደምትይዝ መጠየቅ አሳፍሮኝ ሐዘኔን ጭንቅላቴን በመወዝወዝ ገለጽኩለት፡፡

“ያችን ደግሞ አየሃት? ሻእቢያ ብዙ ሕይወት ከፍሎባታል፤ ያችን ደግሞ እያት ትንቅንቅ ነበር፤ ፈንጅ ቀብረውብን ነበር፡፡ ይችን አየሃት? ‘ፋፂ ከተማ’ ትባላለች፡፡ ይህ የምታየው ተራራ ደግሞ ‘አምባህይወት’ ይባላል፡፡ ሲተረጎም ‘ታደጋቸው’ እንደማለት ነው፡፡ ይህ ተራራ ባይኖር ኖሮ በዚህች ከተማ አንድም ሰው አይተርፍም ነበር፡፡ ሻእቢያ በተደጋጋሚ በአየር ሲደበድባት ተራራው ከለላ ሆኖ ነው ሕዝቡ የተረፈው፡፡ …ያችን ደግሞ..እያት …ወዲያ ማዶ….ይችን ኖ…ኖ ይችኛዋ ኮረብታ…. አየሃት አይደል…እዛ በአንድ ሌሊት ያለቀው….ደግሞ….።”

ጎልማሳው ሰው ከታክሲው በስተግራና በስተቀኝ እንደ ፔንዱለም እየወዘዘወዘ ተራሮቹን አስቃኘኝ፡፡ የሁሉም ተራራች ገድል ጦርነት ነው፡፡ ሞት ነው፤ እልቂት ነው፡፡ አብረሃም አፈወርቂ “ተአዲለ” የሚለውን ዜማ በሚስረቀረቅ ድምፁ ያዜማል፡፡ ድምፁ ይስረቅረቅ እንጂ የሚያዜመው ዜማ የጦርነት ነው፡፡

ጎልማሳው ሰው ከፋፂ ከተማ ትንሽ ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን “እኔ መውረጃዬ ደርሷል፣ ደህና ሁን” ብሎ ተሰናበተኝ፡፡ ምስጋናዬን ሳልጨርስ ሰውየው በሚገርም ቅልጥፍና ከታክሲው ዱብ ብሎ ወረደ፡፡ ምድረ በዳ ላይ፡፡ በመስኮት አሻግሬ አየሁት፡፡ ጥቂት ወታደሮች በተጠንቀቅ ሰላምታ ሲሰጡት ተመለከትኩ…በ..ር…ቀ…ት፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ

ኦሮማይ!

ዛላንበሳ ደርሻለሁ፡፡ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ቤት ጓሮ ቆሜያለሁ፤ ኤርትራን በቅርብ ርቀት እያየኋት ነው፡፡ ከድንጋይ ርብራብ የተሠሩ የኤርትራ ቤቶች ቁልጭ ብለው ይታዩኛል፡፡ አንድ የኤርትራ ቤተክርስቲያንም ጉልላቷ ይታየኛል፡፡ እንደ እረኛ “ስማእንዶ!” እያልኩ ጮኸ ብዬ ብጣራ እንኳ አቤት! ሊሉኝ የሚችሉ ኤርትራውያን አይጠፉም፡፡ አሁን በአንድ ኢትዮጵያዊ ቤት ጓሮ ቆሜ በቅርብ የማያት ሆኖም የማልረግጣት የኤርትራ ደቡባዊ የገጠር ከተማ “አምበስተገለባ” ትባላለች፡፡ እኔ ከቆምኩበት በስተሰሜን በ24 ኪሌ ሜትር ርቀት ደግሞ “ሰንአፌ” ትገኛለች፤ ከእኔ በ140 ኪሌ ሜትር ርቀት ደግሞ አሥመራ፡፡

ዛላንበሳ ፈርሳ የተገነባች ከተማ ናት፤ ለዚያውም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እርዳታ፡፡ በጦርነቱ ሻእቢያ ያፈራረሳቸው ቤቶች አሁንም ፍርስራሻቸው ተከምሮ ይታያል፡፡ የተወሰኑ አዳዲስ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ለአንድ የፈረሰ ቤት 60 ሺህ ብርና ከዚያ በታች እርዳታ ተደርጎ ነው ከተማዋ ነፍስ የዘራችው፡፡ በከተማዋ አንድዬ አስፋልት ላይ ታች ሲሉ የሚታዩት የመከላከያ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች ናቸው፡፡ የከተማዋ ውብ መኪናዎች ደግሞ የወታደር “ኦራል”ሎች ናቸው፡፡ የከተማዋ ሊስትሮዎች የሚጠርጉት ረዥሙን የወታደር ከስክስ ጫማ ነው፡፡ ከተማዋ አሁንም ከ10 ዓመት በኋላ ከጦርነቱ መንፈስ የተላቀቀች አትመስልም፡፡

አፈወርቅ ተክሌ በአዲግራት ካቶሊክ ካቴድራል የሠሩት ስዕል

“ኢትዮጵያ ሆቴል” ጎራ አልኩኝ፤ የከተማዋ ትልቁ ሆቴል ነው፡፡ ነጭ ጋውን የለበሱ ሙሉ ፀጉራቸው ከለበሱት ነጭ ጋውን ጋር ፍጹም “ማች” የሚያደርግ ሰው “ታይ ክእዘዝ” አሉኝ፡፡ የሆቴሉ ባለቤት ናቸው፡፡ ተስተናጋጅ ስለሌለ አስተናጋጅ መቅጠር አልፈለጉም፡፡ ራሳቸው ታዘው፣ ራሳቸው ሠርተው፣ ራሳቸው ያመጡታል፡፡ አቶ ጣእመ ለምለም እንደሚባሉ ግድግዳ ላይ በስማቸው ከሰቀሉት የትግርኛ ጥቅስ ተረዳሁ፡፡ “ሲመክሩት እምቢ ያለ መከራ ይመክረዋል” አይቶ ጣእመ ለምለም ትላለች ጥቅሷ፡፡ ያዘዘኩትን ለመሥራት ተፍ ተፍ እያሉ ወሬ ማውራት ጀመሩ፡፡ እያወሩ መሥራት ይችላሉ፡፡ የሚያወሩት ሰው የናፈቁም ይመስላሉ፡፡ በቤቱ ያለኔ ማንም እየተስተናገደ አልነበረም፡፡

“አቦይ! እዚህ ያለ ዲሽ የኤርትራ ቲቪን ማየት ይቻላል የሚባለው እውነት ነው?” አልኳቸው፡፡ መልስ ሳይሰጡኝ እጃቸውን በፎጣ ጠራርገው የቲቪውን የርቀት መቆጣጠርያ ነኩት፡፡ የኤርትራ ቲቪ አንዳንድ የልማት ዜናዎችን በጭፈራ አጅቦ እያቀረበ ነበር፡፡ “ዙርያውን የምታየው እኮ ኤርትራ ነው፣ የመጣህበት ታክሲም ኤርትራ የእኔ የምትለውን መሬት ረግጦ ነው ያለፈው፤ ወደከተማዋ ለመግባት ስለማይመች ነው የኛ ወታደሮች የሚቆጣጠሩት” አሉኝ፡፡
ቆየት ብለው የቲቪውን ድምፅ አጠፉና ከጎኑ የተደቀነውን ሬዲዮ ነካኩት፡፡ የትግርኛ ዜማዎች መዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ የኤርትራ ኤፍ ኤም ነበር፡፡ ከአሥመራ የሚተላለፈው “95.00 ኤፍ ኤም አሥመራ” ዛላንበሳ ካረፍኩበት ሆቴል ኩልል ባለ ድምፅ ይሰማል፡፡

“38th Parallel”

የዛላንበሳ ዋናው አስፋልቱ ሳያልቅ ኢትዮጵያ ታልቃለች፡፡ ሁለት ወታደሮች በመሀላቸው ቀጭን ሽቦ ዘርግተው በሽቦው ዳርና ዳር ቁጭ ብለው የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ድንበር መጨረሻ ያውጃሉ፡፡ ቀጭኗን ሽቦ የኢትዮጵያ 38th Parallel ብለን ልንጠራት እንችላለን፡፡ አንድ ሕዝቦች የነበሩትን ሰሜንና የደቡብ ኮሪያን ይህች ቀጭን መስመር ለያይታቸዋለች፡፡ አንድ ሕዝቦች የነበሩትን ኤርትራንና ኢትዮጵያን ይህች ቀጭን ሽቦ ሁለት እንደሆኑ ታውጃለች፡፡

ማዶ ለማዶ የሚተያዩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች ሕዝቦቻቸው መስመሯን እንዳያልፉ ይከላከላሉ፡፡ ርቀታቸው በሜትሮች የሚለካ ነው፡፡ ዘወትር ምሽት የኤርትራ ወታደሮች በክራር ሲያዜሙ ይሰማል፡፡ ክራሩ ብቻ አይደለም የሚሰማው፡፡ ምሽት አልፎ አልፎ የተኩስ ለውውጥም ይካሄዳል፡፡ ለክፉ የማያደርስ የተኩስ ልውውጥ፣ ሚዲያዎች የማይዘግቡት የተኩስ ልውውጥ፡፡ ወዳጃዊ የተኩስ ልውውጥ፡፡

ነጯ መኪና

ኤርትራዊያን ቀጭኗን የሽቦ መስመር ለማለፍ ጨለማን ተገን አድርገው አብዝተው ይተጋሉ፡፡ ብዙዎቹ ይሳካላቸዋል፡፡ ጥቂቶቹ ይረሸናሉ፡፡ እድለኛ ከሆኑ ደግሞ ወደማጎሪያ ይላካሉ፡፡ የኤርትራውያኑን ጥረት ለመደገፍ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሽፋን ተኩስ ያደርጋሉ፡፡ ጉቦ የተቀበሉ የኤርትራ ወታደሮችም የውሸት ተኩስ ይከፍታሉ ይባላል፤ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ፡፡ ልክ ጎህ ሲቀድ በኢትዮጵያ መሬት ጥቂት ኤርትራውያን “በቅለው” ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቀጭኗን መስመር ለማለፍ የተሳካላቸው ብቻ ናቸው፡፡ በአጭር የሚቀሩም ሬሳቸው ይለቀማል፤ ጠዋት ጠዋት፡፡ በሕይወት የኢትዮጵያን አፈር የረገጡትን የኤርትራ ልጆች የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰብስበው ያስቀምጧቿል፤ “ሐርድ ቶፕ” የምትባለው ነጯ መኪና እስክትመጣ፡፡

ዛላንበሳ በመልሶ ግንባታ ላይ

ነጯን መኪና በዛላንበሳ የማያውቃት የለም፡፡ የእጅ ሰዓት ለማያስሩ ነዋሪዎች የሰአት መቁጠርያ ሆና ታገለግላለች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ታርጋ የለጠፈችው ይህች ነጭ መኪና ዘወትር ማለዳ ወደ ቀጭኗ ሽቦ ተጠግታ ወደ ኢትዮጵያ የተሻገሩ ኤርትራዊያንን ታጭቃለች፡፡ እየከነፈች መጥታ እየከነፈች ትሄዳለች፤ ወደ ሽመልባ እና ሌሎች የስደተኛ ካምፖች፡፡ የዛላንበሳ ነዋሪዎች እንደነገሩኝ ነጯ መኪና እረፍት የላትም፡፡ በየእለቱ ያለማቋረጥ ወደ ኢትዮጵያ የሚያቋርጡ የስደተኞችን ብዛት ለሚያይ ኤርትራ ከኢሳያስ በስተቀር ሰው የቀረ አይመስለውም፡፡

ድንበር አልባው ቡና

የዛላንበሳ አባወራዎች የኤርትራ ሴቶች ለሚስትነት መልካም ናቸው በሚል ከብዙዎች ጋር ተጋብተው ወልደው ከብደዋል፡፡ ማዶ የሚገኙት የአምበሰተገለባ የኤርትራ ቀበሌ ነዋሪዎች ደግሞ የዛላንበሳ ሴቶች ብርቱ ናቸው በሚል ከኢትዮጵያውያን ጋር ተጋብተው ወልደው ከብደዋል፡፡ ድንገት ጦርነት የሁለት አገር ሰዎች አደረጋቸው፡፡ አሁን ለቡና መጠራራት አይችሉም፡፡ ነገር ግን ቡና አፍልተው ከወታደሮች ጋር ጥሩ ተግባቦት ባላቸው እረኞች በኩል ኤርትራ ላሉ ዘመዶቻቸው ይልካሉ፡፡ ለአማቾቻቸው ጥህሎና ቡና ያሾልካሉ፡፡ ወታደሮቹን ተለማምጠው ገብተው ቶናና በረካ ጠጥተው የሚወጡም አሉ፡፡ ቡናና ጌሾ በእረኞች በኩል ለኤርትራ ዘመዶች መላክ የተለመደ ነው ብለውኛል፡፡

ኩርፊያ፣ ጦርነት፣ ድንበር፣ ቂም የማይገባቸው ከብቶች ድንበር እየተሻገሩ ያስቸግራሉ፡፡ ወታደሮች ሰብሰብ አድርገው ድንበር አካባቢ ያቆዩዋቸውና ባለቤቶቻቸው ሲመጡ ይመልሱላቸዋል፡፡ ይህ ሰላማዊ ድንበር ዘለል የከብቶች ልውውጥ ግን ሁልጊዜ ሰላማዊ እንዳልሆነ ተመልክቻለሁ፡፡ ዛላንበሳ ከመግባቴ ከቀናት በፊት የሆነውን ላውጋችሁ፡፡

ጥቂት ኢትዮጵያዊ ከብቶች የኤርትራን ድንበር ተሻግረው ይሄዳሉ፡፡ ሆኖም ኤርትራዊያኑ ከብቶቹን ለመመለስ አልፈቀዱም፡፡ ዐይናቸውን በጨው አጥበው አላየንም አሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ቁጥራቸው ላቅ ያሉ ኤርትራዊ ከብቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲሻገሩ ኢትዮጵያውያን ይዘው “የእኛን ካልመለሳችሁ የእናንተን አንመልስም” የሚል አቋም ይይዛሉ፡፡ በዚህ አቋማቸውም ለመጽናት ይወስናሉ፡፡ ሁኔታው ያሳሰባቸው የአጎራባቿ አምበሰተገለባ ቀበሌ ነዋሪዎች ሽማግሌዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ድርድር ይጀምራሉ፡፡ ድርድሩ ፍሬ አፍርቶ ኤርትራውያኑ አላየንም ያሏቸውን ከብቶች በሙሉ ለመመለስ ፍቃደኛ ሆነው የእነርሱን ከብቶች እየነዱ መሄድ ችለዋል፡፡ አልጀርስ የማያስኬድ ድርድር፤ አብዱልአዚዝ ቡቶፍሊካ የማያውቁት ስምምነት፤ የመለስና ኢሳይያስ ፊርማ የማያስፈልገው ስምምነት፡፡
ባሳለፍነው መስቀል ደግሞ እንዲህ ሆነ፡፡ በዚህች ደቡባዊ የኤርትራ ቀበሌ አቅራቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊት ልጃቸው እና ጥቂት ቤተሰቦቻቸው ለመስቀል በዓል ሊጠይቋቸው ከአዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ አገር አማን ባሉበት ድንገት የኤርትራ ወታደሮች አምስት የቤተሰቦቻቸውን አባላት አፍነው ይወስዳሉ፡፡ እናት ክፉኛ በሐዝን ተዋጡ፡፡ ምንም ማድረግ አልተቻለም፡፡ በስንተኛው ቀን በኤርትራ ቲቪ ታዩ ተባለ፡፡ ከኢትዮጵያ ጠፍተን መጥተን ነው…እያስባሉ ያናዝዟቸዋል፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ ድንበሩ አካባቢ በፀጉረ ልውጦች ላይ ጠበቅ ያለ ክትትል ይካሄድ ጀምሯል፡፡

ኢትዮ-ኤርትራዊው የትራክተሩ ሾፌር

ይህ ታሪክ የተፈጸመው በ2000 ዓ.ም ነው፡፡ ጥቂት የውጭ ሚዲያዎችም ዘግበውታል፡፡ የኤርትራ መንግሥት አንድ ትራክተር ከነሾፌሩ ድንበር አካባቢ ያለውን ጋሻ መሬት እንዲያርስ ይልከዋል፡፡ ሾፌሩ ባጋጣሚ ወደ ኤርትራ ከመሰደዱ በፊት የአዲግራት ልጅ ነበር፤ ካቻማሊ፡፡ በአዲግራት ቤተሰብ አፍርቷል፡፡ ድንበር አካባቢ መሬቱን እያረሰ ሳለ ኢትዮጵያዊ ቤተሰቦቹ ናፈቁት፡፡ ትራክተሯን ቀስ እያለ ወደ ፊት ነዳት፤ ድንበር የሚያርስ መስሎ ማርሽ ቀየረ፡፡ እያከነፈ ወደ ኢትዮጵያ መሬት ገባ፡፡ የኤርትራ ወታደሮች በተኩስ እሩምታ አጣደፉት፡፡ የትራክተሩን ግዙፍ ጎማ እንጂ ሾፌሩን አላገኙትም፡፡ ሾፌሩ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ደግሞ የሽፋን ተኩስ ሰጡት፡፡ ሾፌሩ ኢትዮጵያ ቢገባም የተኩስ ልውውጡ ግን ሊበርድ አልቻለም፡፡ የትራክተሩ ድራማ 37 የኤርትራ ወታደሮችና ሁለት የኢትዮጵያ ወታደሮችን ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነ፡፡

ደቡብ ኤርትራ ከሰሜን የኢትዮጵያ ጫፍ እንዳየኋት

የአሥመራ ናፍቆት

የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም፤ ከአሥመራ በቀር፡፡ ይህችን ሕልም የመሰለች ከተማ ሳስብ ክፉኛ የእኔነት ስሜት ይወረኛል፡፡ ሁሌም እንደማውቃት እንጂ እንደማላውቃት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ የእኔ እንጂ “የእነርሱ” ሆና አይሰማኝም፡፡ ደግሞም የእኔ ነበረች፣ የእኔም ትሆን ይሆናል፤ ማን ያውቃል? ሃምሳ ዓመት…መቶ ዓመት…150 ዓመታት?

የ“ኦሮማዩ” ጸጋዬ “የባህር እንቁ” የሚላትን ከባህር ጠለል በላይ በ7500 ጫማ ከፍታ የምትገኘዋን አሥመራን አውቃታለሁ፤ የዘንባባ ጫካዎቿን፣ እንደ “ገዛ ባንዳ”፣ “ሰንበል ጉዳይፍ”፣ “ገጀራት ማይ ወላጮ”፣ “እዳጋ ሐሙስ”፣ “ማይ ተመናይ”…ያሉ ውብ ሰፈሮቿን በበዓሉ ግርማ ጽሑፍ አሳምሬ አውቃቸዋለሁ፡፡ ጸጋዬ አሥመራ ውስጥ ያልወሰደኝ ቡና ቤት አለ እንዴ? አሥመራን አታውቃትም አትበሉኝ፡፡

ለካንስ ወደ ድንበር መሄድ ናፍቆት ያፋፍማል እንጂ አያበርድም፡፡ ከድንበር አንጋጥቼ ያየሁሽ ናይ ሰሜናዊ ፅብቅቲ አሥመሪና! ኻብ አንቲ ንግሥቲ ይበልጽ መልክኪ…

ዛላንበሳ ጠረፍ ላይ ሆኜ የበዓሉ ግርማ ፍቅር- ፊያሜታ ስትስቅብኝ ተሰማኝ፡፡ “አባቴ ይሙት ደደብ ነህ!” እያለች፡፡