በሰበታ ከተማ ከመሬት ሽያጭ ሙስና የተመዘበረው ገንዘብ ለፖለቲካ ሲባል እየተደበሰበሰ ነው

(ሙሉ ገ.)
• አንድ ሹመኛ በከተማው ያሠሩት ሕንጻ “ሰርቆ ማሳያ” ተብሏል
• ግለሰቡ ከክልሉና ከኦሕዴድ ባለሥልጣናት ጋራ የሪልስቴቶች ባለቤት ሆነዋል
• መሐንዲሱ የ4 ሚልዮን ብር ቤት ሲገነቡ
በኦሮሚያ ክልል የሰበታ- ሐዋስ ከተማ ከመሬት ሽያጭ ሙስና ጋር በተያያዘ በአስተዳደር ሥራ ላይ የነበሩ ከፍተኛ የኦህዴድ- ኢህአዴግ አመራር አባላት ከገቢና ፋይናንስ ቢሮና ከደላሎች ጋር በመተባበር “ከ15 ሚልዮን ብር በላይ ገቢ ወደ ኪሳቸው ማስገባታቸውን አዲሱ አመራር ባደረገው ጥናት አረጋገጠጥኩ” አለ። ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ግን “ተጣራ የተባለው የገንዘብ መጠን ከትክክለኛው ጋራ ሲተያይ እዚህ ገባ የማይባል ነው” ብለዋል።

ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ነዋሪዎች ግን “አዲሱ አስተዳደር አረጋገጥኩት” ያለው የገንዘብ መጠን “የአንድ እና የሁለት የአስተዳደር ሰራተኞች የዝርፊያ ድርሻ ብቻ ነው” ሲሉ ተረጋገጠ የተባለውን የተመዘበረ የገንዘብ መጠን አነስተኛነት ይናገራሉ። “አዲሱ አስተዳደር ፖለቲካዊ ገጽታው እንዳይበላሽ መጠንቀቁን ትቶ የመሬት ምዝበራውን በደንብ ቢያጣራ ትክክለኛውን የዝርፊያ አሃዝ ይደርስበት ነበር” ብለዋል፡፡
ከመሬት ካርታ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ሙስና ከወራት በፊት በድንገት በደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስራ አምስት በላይ የሰበታ፣ ዓለም ገና እና ወለቴ አካባቢዎች የአስተዳደር ሠራተኞችና መሃንዲሶች አሁንም በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሲሆን በመሬት ድለላ የአስተዳደር ሠራተኞችን ሲያገለግሉ የነበሩ ደላሎች ግን ሰሞኑን መለቀቃቸውን የአካባቢው እማኞች ገልጸውልናል፡፡
በወለቴ፣ ዓለምገና እና ሰበታ ከተሞች ከ1997 ምርጫ ዋዜማ ጀምሮ መሬት በዘመድ አዝማድ፣ በጎሳ፣ በፖለቲካ አጋርነትና በገንዘብ ጭምር በግልጽ ይቸበቸብ ነበር። “የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃ ሳይወስዱ ፖለቲካዊ ጥቅም ብቻ ሲያተርፉበት ከርመዋል” ብለውናል፡፡
የቀድሞው የሰበታ ከተማ ማኅበራዊ ጉዳይ ሐላፊና የኦህዴድ ኢህአዴግ ከፍተኛ ካድሬ የነበሩት ግለሰብ እና የሰበታ ከተማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ ገዛኸኝ ጎቤ ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የመስተዳድሩ አባላት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ እኝሁ ግለሰብ ምንም ያልነበራቸው የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩ ሲሆን በቅርቡ ያስገነቡት በዓለም ገና ከተማ የሚገኝ ባለስድስት ፎቅ ህንፃ በከተማው ነዋሪ ”ሰርቆ ማሳያ‘ ተብሎ ይጠራል ይላሉ የአካባቢው ምንጮች።
አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ሌላ ሰራተኛ ደግሞ በ1999ዓ.ም ከሌመን ወደ ሰበታ ተዘዋውረው ሲመጡ “ተራ መሃንዲስ የነበሩ ሲሆኑ በአሁኑ ጊዜ በሰበታ ከተማ በ400 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት ቪላ ቤት እና በውስጡም ዘመናዊ ጅምናዚየም፣ የካሜራ መቆጣጠሪያ እና ውድ አውሮፓ ሰራሽ እቃዎች ይገኙበታል” ይላሉ።
ነዋሪዎቹ የቀድሞው የከተማው ማኅበራዊ ጉዳይ ሐላፊ ከበርካታ የኦህዴድ እና የኦሮሚያ ባላሥልጣናት ጋራ በሽርክና በሰበታ፣ በገላን ከተማ እና በደብረዘይት ከተማ ሪል ስቴቶችን ማቋቋቸውን ይናገራሉ። በቅርቡ “በሙስና እና ብልሹ አሠራር ምክንያት” ከሐላፊነታቸው የተነሱት የሰበታ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽመልስ ሀሰኖ “በሕግ ከመጠየቅ ይልቅ የኦሮሚያ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኃላፊ ተደርገው ተሹመዋል” ሲሉ የዜና ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሪፖርተራችን አስተያየቱን የሰጠ አንድ የከተማው ነዋሪ እንደተናገረው “የከተማው እና የአካባቢው ባለሥልጣናት በሙሉ አብረው በፎርጅድ ካርኒ ሸጠው ብር ካካበቱ እና ለራሳቸውም በፎርጅድ ካርኒ ካርታ አሰርተው ቪላ ቤት ከሰሩ በኋላ ጉዳዩን ሕዝብ አውቆት መነጋገሪያ ሲሆን ተጠያቂነቱን ወደ መሃንዲሶቹ ብቻ ማምጣታቸው ተገቢ አይደለም፤ ይህ የሥርዓቱ አጠቃላይ ችግር ነው” ብሏል፡፡