የአቶ መለስ ጸጉርና የሕገ መንግሥቱ ምሰሶዎች

አቶ መለስ ሐሙስ ዕለት በተከበረው ፓርላማቸው ተገኝተው ነበር። እንደተለመደውም በሁሉም ጉዳዮች ላይ የኤክስፐርት ትንተና፣ የንጉሥ ቃል እና የጳጳስ ቡራኬ ሰጥተው ወጥተዋል። አንድ ሰዓት ከ43 ከቂቃ የፈጀው የአቶ መለስ ማብራሪያ ከፓርላማው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች የተሰጠ መልስ መስሎኛል። ንግግሩን ያየሁበት ድረ ገጽ (ዋልታ) ጥያቄዎቹን ማን እንዳቀረባቸው በዝርዝር ባይናገርም ለመገመት የማያስቸግሩ አሉበት።

መለስ 12 ደቂቃ የሚፈጅ ድንብርብሩ የወጣ መልስ የሰጡበት አንዱ ጥያቄ ሕገ መንግሥቱን የሚመለከት ነው። ጥያቄው በትክክል ምን እንደሆነ ለመስማት ባልችልም “በሕገ መንግሥቱ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮች ያሉ አይመስልዎትም ወይ?” የሚል ቃና ያለው ሊሆን እንደሚችል ከመልሱ በመነሣት መገመት ይቻላል። ጠያቂው ዝርዝር አንቀጾችን እና ጉዳዮችን ጠቅሰው ስለመጠየቃቸው ከመልሱ በመነሣት መገመት አይቻልም፤ አቶ መለስ አንድም አስተያየት የሰጡበት ዝርዝር አንቀጽ ስለሌለ። ታዲያ ጥያቄው ለምን ተነሣ? ጥያቄው እንደው በደፈናው ቀርቦ ይሆን?  እንደዚያ ሆነም አልሆነም ግን የአቶ መለስ ማብራሪያ ከግቡ አኳያ ባለሁለት ስለት ቢላ ነው። ሁለቱን ስለቶች በስተመጨረሻ አነሳቸዋለሁ።

ይህ የመለስ ማብራሪያ ክፍል ስለ ሕገ መንግሥቱ እና እርሱን ማሻሻል ወይም መለወጥ በሚፈልጉ ፓርቲዎች ላይ ያተኮረ ነው። ለየብቻ እንያቸው።

ሕገ መንግሥቱ፤ የአሸዋ ላይ ቤት?

መለስ ፖለቲካን የሚመለከቱት በጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ነው። ይህም ንግግራቸውና አስተሳሰባቸው በጽንፋዊ አቋሞች እንዲሞላ ያደርገዋል። ሰውየው ሃይማኖተኛ ቢሆኑ ኖሮ አልሻባብን የመሰሉ ሴክቶችን በቀላሉ ሊቀላቀሉ ይችሉ እንደነበር እገምታለሁ። አሁንም ሕገ መንግሥቱን ስለማሻሻል ተጠይቀው የሰጡት መልስም እንዲሁ ያለ ነው፤ ቀላሉን አክርረው፣ ከባዱን አጥቁረው፣ በመጨረሻ የተሟላ ትርጉም የማይሰጥ የተምታታ ሐተታ አቅርበዋል።  አቶ መለስ እርሳቸውና ፓርቲያቸው ሕገ መንግሥቱ “የሚሻሻል ምንም ነገር የለውም” ብለው እንደሚያምኑ፤ ነገር ግን “መለስተኛ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ቢደረግ ጽጉሬን እነጫለሁ ማለት አይደልም፤ የሚነጭ ካለ” ብለዋል። የአዲሱ ፓርላማቸው አባላትም በሳቅ አጅበዋቸዋል።

ቀጠል በማድረግ መለስ በሕገ መንግሥቱ “ምሰሶዎች” ላይ ግን ድርድር እንደሌለ ያብራራሉ። በእርግጥም ማንኛውም ሕገ መንግሥት መሠረታዊ ሊባሉ በሚችሉ መርሖች፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከታሪካዊ ምክንያቶች የሚመነጩ አገር ተኮር በሆኑ ቋሚ ስምንመቶች ላይ ጭምር የሚገነባ የስምምነት ሰነድ ነው። መለስ “ለምሳሌ” ብለው የጠቀሱዋቸው አራት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት “ምሰሶዎች” (እርሳቸው ባስቀመጡት ቅደም ተከተል) የሚከተሉት ናቸው።

  1. የመንግሥት እና ሃይማኖት መለያየት፣
  2. የቡድን እና የግለሰብ መብት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣
  3. የብሔረሰቦችን (ብሔሮችንና ሕዝቦችን ረስተዋቸዋል ወይስ ጠፉ?) መብት በማክበር ላይ የተመሠረተ፣ የብሔረሰቦችን ዳር ድንበር መሠረት ያደረገ፣ ሰፊ የአካባቢ ነጻነት የሚሰጥ ፌዴራላዊ ሥርዓትና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እና
  4. የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ እና በዚሁ ማእቀፍ የመሬት አስተዳደር በመንግሥት እጅ እንዲሆን ማድረግ ናቸው።

መለስ እንደሚሉን “እነዚህ ምሰሶዎች ከተነኩ፣ ከተቀየሩ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዳለ ይፈረካከሳል። ስለዚህ እነዚህን ምሰሶዎች የሚነካ ነገር…አንድ አንቀጽ፣ አንድ ቃል የመቀየር ሳይሆን የሥርዓቱን ምሰሶዎች የመናድ ወይም የመጠበቅ ነው። እነዚህ ሲነኩ ከጸጉር መንጨት በላይ መሄድ ይጠይቃል።” አቶ መለስና ተከታዮቻቸው በእነዚህ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ምክንያት (ያይን ቀለም ካለማማር ጀምሮ) “ጸጉር ከመንጨት” አልፈው ማንኛውንም ነገር “እንደሚነጩ” በተግባር የምናውቀው ነው። “ጸጉር” የመንጨት መብት፣ ሥልጣንና ጉልበት እንዳላቸው ሳንዘነጋ ግን አንዳንድ ጥያቄዎችን እናንሣ። (በነገራችን ላይ የአቶ መለስ ጸጉር የተመለጠው ለካስ ሕገ መንግሥቱ ሲነካ እየነጩት ነው?! “እስኪ ጸጉር እንንጭ” አለ ካድሬ ሲተርት! በኋለኛው አገባቡ “ጸጉር እንንጭ” ማለት ተቃዋሚን እናጥፋ ወይም ሀብት እናግበስብስ ማለት ነው፤ እንደ አገባቡ። ለምሳሌ ሁለት ካድሬዎች አዲስ ንግድ መጀመር ፈልገው “ጸጉር እንንጭ” ወይም “ጸጉር አካፍል” ከተባባሉ ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚገኝበት ሙስና እናፈላልግ ወይም ከተገኘው እንካፈል ማለታቸው ሊሆን ይችላል። በተቃራኒው በሌላ አገባብ “ሕገ መንግሥቱ ተነካ፣ ጸጉራችንን እንንጭ” ካሉ የሆነ ምክንያት ተፈልጎ “የሚነጭ” ተቃዋሚ ወይም ተጠርጣሪ ግለሰብ/ድርጅት ስለተገኘ እንዝመትበት ማለታቸው ሊሆን ይችላል። እያንዳንዱ ሥርዓት የራሱ ቋንቋ አለው፤ ቋንቋውን መማር አይጎዳም። ከነጪ ይሰውረን። ወደ ጉዳያችን እንመለስ።)

የአቶ መለስ ትንተና አንድ መሠረታዊ መነሻን ታሳቢ ያደርጋል፤ ይህም አሁን እርሳቸው “ጸጉር የሚነጩለት” ሕገ መንግሥት በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሕዝብ መክሮበት፣ አብዛኛውም ተስማምቶበት የጸደቀ አስመስለው ማቅረባቸው ነው። ይህ ራስን በፈቃደኝነት ለማሳሳት ከመፍቀድ በቀር ፋይዳ የሌለው ፖለቲካዊ መነሻ ነው። በዚህ አይነት የደርግም ሕገ መንግሥት “ሕዝብ ያጸደቀው ነበር” የማይባልበት ምክንያት የለም። እንዲያ ከሆነ ደግሞ አቶ መለስ “ሥልጣን የያዙን ሕግ መንግሥታዊ ሥርዓትን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ (በጦርነት) አስወግደው፤ ይህም ሳይበቃቸው ሕገ መንግሥቱ (የደርግ) ከሚፈቅደው ውጪ ሌላ ሕገ መንግሥት በማዘጋጀት ነው” ተብለው ሊከሰሱ ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህ ክርክራቸው ከመነሻው ፖለቲካው ተቀባይነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ ነው።

ወደ ሕገ መንግሥቱ ይዘት ሲገባ ደግሞ በዚህ መሰል መሠረታዊ ሰነድ ውስጥ መካተት አልነበረባቸውም ከሚባሉት ጀምሮ ቢካተቱም በርትአዊ መንገድ አልተተረጎሙም የሚባሉ መርሖች ሞልተዋል። የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ የክልሎች አወቃቀር፣ የቡድኖች ስያሜና ትርጉምን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። እንደ አይሁድ ጭፍጨፋ (ሆሎካስት) ሲያስፈልግ መማጸኛ፣ ሲፈለግ ደግሞ የተለየ ሐሳብ የሚያነሱትን ለማስፈራሪያና ለማውገዣ መዋል የጀመረው የብሔረሰቦች ጥያቄ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። ሕገ መንግሥቱ መብታቸውን ያስከብርላቸዋል ከተባሉት “ብሔረሰቦች” መካከል ለግማሹ ክልል ሰርቶ ሌሎቹን አንድ ላይ ያዳበለበትን ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ራሱ አይመለስም። ታዲያ አንድ ዜጋ መርሑን ተቀብሎም ይሁን ሳይቀበል ነገር ግን ለሁሉም ርትአዊ በሆነ መንገድ አልተተረጎመም፣ ስለዚህም መሻሻል አለበት ቢል “ጸጉር ለመንጨትም” ሆነ “ከዚያ በላይ ለመሄድ” መፎከርን ምን አመጣው?

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የተምታታ ትንተና ሕገ መንግሥቱን ሊለወጡ በማይችሉ “መርሖች” የተሞላ አስመስለው ማቅረባቸው ነው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በርካታ ድንቅ አንቀጾች እንዳሉት ሁሉ ኅብረተሰብ ሲለወጥ የሚለወጡ ጉዳዮችንም ይዟል። ለምሳሌ በትራንስፎርሜሽኑ አገራችን በመቶ ዓመት ውስጥ ከበለጸጉት አገሮች ተርታ ተሰለፈች እንበል፤ አቶ መለስም በስልጣን ላይ ናቸው እንበል፤ አንድ ፓርቲ “አሁን መሬት የግል መሆን ከሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ቢል አቶ መለስ ጸጉራቸውን ሊነጩ ነው? በተቃራኒው ግን የነጻነት፣ የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ዘመን የማይለውጣቸው በመሆናቸው አተገባበራቸው እየሰፋ እንጂ መርሖቹ ራሳቸው አይቀየሩም። አቶ መለስ ግን የክልል አወቃቀርን ከሰብአዊ መብትና ከነጻነት ጋራ እኩል አድርገው ያቀርባሉ። ነጻነቱ የተከበረለት ሕዝብ የአካባቢውን አወቃቀር የመወሰን መብቱ ይጠበቃል። ጥያቄው ፌዴራል አወቃቀሩ አይደለም፤ ኢሕአዴግ መርሑን ሁሉንም እኩል በሚያስተናግድ፣ አገራዊ ጥቅምን ከግምት በሚያስገባ መንገድ አልተረጎመውም ከሚል አስተያየት የሚመነጭ ነው። ስለዚህ የሕወሀት/ኢህአዴግን አንድ አመለካከት ከሌሎቹ የበለጠ ቅዱስ አድርገን የምንቀበልበት አንዳችም ምክንያት የለም፤ ካለም ምክንያቱ ኢህአዴግ በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን መያዙ ብቻ ነው።

ምሰሶ መንጨት፤ ጸጉር መትከል

ኢሕአዴግ ፓርቲያዊ አምላክ መሆን እንደሚፈልግ ካረጋገጠ ሰንብቷል፤ ለዚያውም ጨቋኝና ጨካኝ ‘አምላክ።’ ዓለም ከፈጣሪ ‘መዳፍ’ ለሰከንዶች ብትወጣ ትጠፋለች እንደሚባለው ሁሉ ኢትዮጵያም ከህወሓት/ኢሕአዴግ መዳፍ መውጣት ቀርቶ የኢሕአዴግ ሕልምና ቅዠት ካልተፈጸመ ኢትዮጵያ ምን እንደምትሆን በተደጋጋሚ ተነግሮናል። ትፈራርሳለች፤ ትጠፋለች፤ ትናዳለች፤ ትበታተናለች፤ ትሰምጣለች። ፈጣሪ ‘ኢሕአዴግ’ ደግሞ ተራውን መልአኩ መለስን ልኮ ኢትዮጵያን እየጠበቃት ነው። ተረት ይመስላል? ሰዎቹ ግን እንዲህ ሳያስቡ አይቀሩም። አንዱ ሃይማኖተኛ ሚኒስትር በቅርቡ “መለስ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የላካቸው መሪ” እንደሆኑ ተናግረዋል። እንግዲህ እኚህ ሚኒስትር እግዜሩ ከሾመላቸው አለቃቸው ጋራ እንዴት ሲሰሩ እንደከረሙ ገምቱ።

አቶ መለስ በፓርላማ ማብራሪያቸው ስለ ሕገ መንግሥቱ ያነሡት ነጥብ ተቃዋሚዎችን የሚመለከት ነው። በቅድሚያ “በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሠረታዊ ምሰሶዎች ላይ የጋራ እምነት በሌለበት ሁኔታ የተረጋጋና የዳበረ ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም” የሚል ማንም ሰው የማይቃወመው መንደርደሪያ ይሰጣሉ። አስከትለው የጀርመንን ታሪክ ከጠቀሱ በኋላ “የሕገ መንግሥቱን ምሰሶዎች የማይቀበል ፓርቲ ሰላማዊ መንገድ ነው የምከተለው ቢል እስኪደላው ድረስ ብቻ ነው…አቅሙን ሲያገኝ፣ ሁኔታው ሲመቻችለት ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓቱን ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ወደመቀየር እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም” ብለዋል። ለዚህ ማስረጃ ለማቅረብም ወደ ሒትለር መሄድ ሳያስፈልግ የደርግን ቀይ ሽብር እና ነገደ ጎበዜን (ምርጫ 97 ማለታቸው ነው) ማየት እንደሚበቃ ይነግሩናል።

በስተመጨረሻ ደግሞ ታዲያ “የሕገ መንግሥቱን ምሰሶዎች የማይቀበሉ  ፓርቲዎች እውቅናና ድጋፍ ለምን ይሰጣቸዋል?” በማለት ራሳቸውን  ይጠይቃሉ። ለመልሱም የአሜርካንን “ተሞክሮ” በትምህርታዊነቱ ጠቅሰው ዋናውን ማስፈራሪያ አከል ወሬ ይቀጥላሉ። የአሜሪካ ሕገ መንግሥት የናዚ ፓርቲን የመሳሰሉ ፓረቲዎችን የሚታገሰው “ሕዝቡ ያለው አማራጭ እንዲሰፋለትና እንዲመርጥ፤ ቡድኖቹም ተጨባጭና ወቅታዊ አደጋ (clear and present danger) እስካልሆኑ ድረስ” መሆኑን በመንደርደሪያነት ይጠቅሳሉ። “…በእኛም ሁኔታ የሕገ መንግሥቱን መሠረታዊ መርሖች የማይቀበሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ በሰለማዊ መንገድ እንሠራልን የሚሉ እንዳሉ እናውቃለን። በተለይም የብሔሮችን መብት በማክበር ዙሪያ የተፈጠረውን ፌዴራላዊ ሥርዓት የማይቀበሉ አሉ። እነዚህ ሰዎች ስልጣን ቢይዙ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እንደሚፈጠር ጥርጥር የለውም። እነዚህ ኀይሎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የተሰለፉ ናቸው ብንል እውነታውን ነው የምንናገረው። ነገር ግን ተጨባጭና ወቅታዊ አደጋ እስካልሆኑ ድረስ የእነዚህን ግለሰቦችና ቡድኖች ሕገ መንግሥታዊ መብት ማክበር አስፈላጊ ነው።” ብለዋል።

አነጋገሩ ግልጽ መሰለኝ። የአሜሪካዋ ታሪክ እንዲያው ማምታቻ ነገር ነች፤ ከኢትዮጵያ ጋራ የሚነጻጸርም አይደለም። ቁም ነገሩ “ሰላማዊ ትግል” አደርጋለሁ በማለት ብቻ ከመነጨት መዳን እንደማይቻል መገለጹ ነው። “መርሑን”ና ከአሜሪካ ተቀሰመ የተባለውን ትምህርት ይሁን ብለን እንቀበለው። ለመሆኑ አንድ ፓርቲ “ተጨባጭና ወቅታዊ አደጋ” መሆኑን የሚፈርደው ማነው? ሌላ ማን ሊሆን ይችላል፤ ራሳቸው አቶ መለስና ጓዶቻቸው ናቸው። አይ የሕገ መንግሥት ምሰሶ፤ አይ ዴሞክራሲያ ሥርዓት! የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ምሰሶ መንጨት፣ ጸጉር መትከል ሆኖ ቀረ?!

በመጨረሻ አቶ መለስ ይህን ተንኳሽ መልእክት በዚህ ወቅት ማስተላለፍ የፈለጉበትን ምክንያት መጠየቅ ያስፈልጋል። ዋናውና አስቸኳዩ የአቶ መለስ ግብ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ይሁኑ ከዚያ ውጭ ያሉ ተቺዎቻቸው ነክሰው የሚጮኹበትን አዲስ አጥንት/አጀንዳ መስጠት ነው። ይህም በአገሪቱ የሰፈነውን አፈናና የኢኮኖሚ ችግር በመጠኑም ቢሆን ያስረሳ ይሆናል ብለው አስልተው ይሆናል። ሁለተኛው የማብራሪያው ግብ “የአውራ ፓርቲ” ትምህርትን በመከለስ እርሳቸውና ፓርቲያቸው የማይፈልጉት፣ “በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ” የሚል ፓርቲ እንኳን ቢሆን የሚኖረው በእርሳቸውና በሥርዓታቸው ቸርነትና ሆደ ሰፊነት እንጂ ሕጋዊ መሠረት ኖሮት እንዳልሆነ በድጋሚ ለማረጋገጥ ነው። ይህም ቢሆን የዋህ ተቃዋሚዎችን ለማነጫንጭና ‘ለማስቆጣት’ በቂ ይሆናል።

መለስ ነገደ ጎበዜን ያነሡበት ምክንያት ለሰሚው ግራ ሊመስል ይችላል። በ1997 ምርጫ ወቅት በረከት ስምኦንም በተመሳሳይ አቶ ነገደን (መጽሐፋቸውን) ድንገት አንስተውት በኋላ ለተመሠረተው ክስ መነሻ እስከመሆን መድረሱ ይታወሳል። አሁን ለምን ተነሡ ብሎ መጠየቅ የዋህነት አይደለም። በ1997 የአቶ በረከትን ክርክር ተከትሎ የነገደ ጎበዜን መጽሐፍ በተመለከተ አንድ ጽሑፍ ጽፌ ነበር። በዚያ ጽሑፍ የኢሕአዴግ ሰዎች ከተራ ውግዘትና ፉከራ አልፎ ነገደ ጎበዜ በመጽሐፋቸው ስለ ሕገ መንግሥቱ ያነሷቸውን ሐልዮታዊ (theoretical) እና ተግባራዊ ጥያቄዎች እንዳልመለሱ፣ መልስ ካላቸውም በጨዋነት አቅርበው እንድንመዝነው ጠይቄ ነበር። እስከዛሬም መልሱ አልተሰማም። አሁንም አቶ መለስ መልስ አላቀረቡም። አንዳንድ ጊዜ እነመለስ ሰውየውን ይፈሯቸው ይሆን ወይስ ሁሉንም ጥፋት የሚያላክኩበት “ሰይጣን” ሊያደርጓቸው ይፈልጋሉ ብዬ እጠይቃለሁ።

በአጠቃላይ ይዘቱ የአቶ መለስ ንግግር አዲስ ቁም ነገር የለበትም፤ አዲስ የማደናበሪያ ትንተና እንጂ። ለመሆኑ መለስ ስለ ቱኒዚያና ስለ ግብጽ ተጠይቀው ነበር? በሚቀጥለው ወር አጠቃላይ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ የተለመደ ሁለገብ ትንተናቸውን እንደሚያቀርቡልን ይጠበቃል። እስከዚያ ጸጉር ንጩ!