የዋጋ ማስተካከያው ኻያ ቀናት
ከሰሜን አፍሪካ እየተንደረደረ ቁልቁል የሚዘልቀው የአብዮት ሰደድ ሙቀቱ አዲስ አበባ ላይ መሰማቱ አልቀረም። ብዙ ሽር ጉድ የተባለለት የመሪዎቹ ጉባኤ እየተካሄደም ነዋሪዎች ለአስቸኳይ ስብሰባ የተጠሩ ልጆቻቸው እንዲመክሩ መወትወቱ አልቀረም። ኢህአዴግ የሕዝቡን የኑሮ ምሬት የሚያስታግሱ ብሎም የሚያሽሩ መፍትሄዎችን ሰጥቻለሁ ብሎ ያስባል። በአንድ ወር ውስጥ የዋጋ ተመን እና የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ እርከን ማሻሻያ ማድረጉን እንደ ዋነኛ ግብ ይቆጥረዋል፡፡ በትይዩ ደግሞ እንዲህ መልካም አድርጌለታለሁ የሚለውን ሕዝብ የደህንነት ስጋቱ ምንጨ አርጎ ያየዋል።
ትግበራዎች አንድ ትልቅ መልዕክት አላቸው፡፡ፓርቲው ቀደም ሲል በወሰዳቸው የኢኮኖሚ ጉዳይ ለውጦች ላይ እምነት አለማሳደሩን፤ አርቴፊሻል ለውጦች መኾናቸውን መቀበሉን እና የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ለውጦቹም ያልተፈለገ ግብ መምታታቸውን መረዳቱን ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግን “መረዳት” ከመጸጸት ጋር እና ማኀበረሰቡን ይቅርታ ከመጠየቅ ጋር የተዛመደ አይደለም፡፡ ለተሻለ የፖሊሲ ለውጥም ፖለቲከኞችን የሚጋብዝ ምክንያት አይደለም፡፡ ይልቁንም ስህተትን ከመሸፋፈን ጋር ብሎም ሕዝቡ መብቱን እንዳይጠይቅ ከማፈን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የበለጠ አምባገነን የመኾን ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጰያ መንግስትም ይሄንኑ እያደረገ ነው ያለው፡፡
ይህ ገመናን የመደበቅ ብልሀት ግን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ አይመስልም፡፡ ልጓሙን ስቶ ለቁጥጥር የሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ኻያ ቀናትን ያስቆጠረው የችርቻሮ ሸቀጦች ዋጋ ትመና ከመድኃኒትነቱ ይልቅ የሸማቹንና የቸርቻሪውን ኑሮ ይበልጥ እያጎመዘዘው ይገኛል፡፡ በተለይ አዲስ ነገር ኦንላይን ለሳምንት ያህል ቅኝት ባደረገችባቸው የመንደር አነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ቤቶች ላይ የዋጋ ለውጡ ከፍተኛ ኪሳራን እያስከተለ ሲኾን በዝቅተኛ የኑሮ እርከን ላይ የሚገኘው ሸማችም የተጋቦቱ ሌላው ተጠቂ እየኾነ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ አነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ቤቶች ሁለቱን የገበያ ጠባያት ማለትም የዝቅተኛውን ሸማች እንዲሁም የአትራፊ ነጋዴውን ጠባያት በአንድነት የሚይዙ ናቸው፡፡ እንደ ሸማች የቤተሰብ እለታዊ ሸመታዎች ላይ ሲሳተፉ እንደ ነጋዴው ደግሞ ከቀለብ የምትተርፈውን ሽራፊ ጥሪት መልሶ ንግድ ላይ በማዋል ተግባር ላይ ይጠመዳሉ፡፡ እንደ ብዙሃኑ አርሶ አደር ሁሉ ቢመች ለገበያ ካልኾነ ደግሞ ለቤተሰብ ቀለብ የሚሉ ናቸው፡፡ በሁለቱም የኢኮኖሚ ተዋናዮች መካከል መገኘታቸው ደግሞ በሁለቱም ጎራዎች ላይ ሊከሰት በሚችለው አሉታዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ዋነኛ ሰለባዎች እንዲኾኑ ምክንያት ነው፡፡
ባለፈው ታህሳስ የተደረገውም የዋጋ “ማስተካከያ” በሁለቱም ስለት መካከል እንዲራመዱ እያደረጋቸው ነው፡፡ እንደ ሸማች የሸቀጦች ከትላልቅ አከፋፋዮች ዘንድ አለማገኘት እንዲሁም ደግሞ እንደ ነጋዴ ቀደም ሲል በከፍተኛ ዋጋ የተገዙ ሸቀጦችን በአዲሱ ዝቅተኛ ታሪፍ እንዲሸጡ መገደድ የተጋፈጡት እውነታ ነው፡፡
ለሣምንት ያህል የተደረገው የአዲስ ነገር ኦንላይን የገበያ ቅኝት እንደሚያሳያው የችርቻሮ ነጋዴዎቹ ከዋጋ ለውጡ ቀደም ሲል የገዟቸው ሸቀጦች በአዲሱ ዋጋ ዝቅተኛ ተመን መያዛቸው ለኪሰራ ዳርጓቸዋል፡፡ ቀድሞ ይተምኑት ከነበረው ዋጋ እስከ 30 በመቶ ያህል ቅናሽ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡ ቀድሞውንም ቢኾን ከችርቻሮ ንግድ የሚገኝ ትርፍ ለቤተሰብ ቀለብ እና ለቀጣዩ ግብዓት መግዣ የሚካፈል ነው፡፡ ትርፍ የለም ማለት ቀለብ ይጎላል፤ ዋነኛ የመተዳደሪ ምንጭ የኾነው ችርቻሮ ይቋረጣል ማለት ነው፡፡ ለአነስተኛ ብድር እንኳ በኢሕአዴግ አንዱ ክንፍ መደራጀትን መጠየቁም የችርቻሮ ነጋዴዎችን የዛሬ እና የነገ ሕይወት ለፈተና ዳርጎታል፡፡
የችርቻሮ ነጋዴዎቹ ኪሳራ ግን በቀላሉ ወደ ብዙኃኑ ማህበረሰብ ለመጋባት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ ነጋዴዎቹ ኪሳራቸውን ለማሳናስ ሲሉ ከወሰዷቸው እርምጃዎች አንዱ ለሽያጭ ያዘጋጇቸውን ሸቀጦች ለቤተሰብ ፍጆታ ማዋልን ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱም እንደ ሸማች ሸቀጦቹን ተጠቃሚዎች እንደመኾናቸው ቀላሉ መፍትሄ ኪሳራን በፍጆታ መካካስ ይኾናል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሹኑ ለገበያ አለማቅረብን ሌላው መፍትሄያቸው አድርገዋል፡፡ ይህም በመኾኑ በኑሮው ዝቅተኛነት የተነሳ የችርቻሮ ነጋዴዎች ላይ ሸመታውን ጥገኛ ያደረገው ብዙሃኑ ነዋሪ ለይምሰል በተሰነዘረው የዋጋ ማስተካከያ ይበልጡኑ ተጎድቷል፡፡
ለወትሮው እንደሚታየው ቢኾን ኖሮ የችርቻሮ ነጋዴው እና ዝቅተኛ እርከን ላይ ያለው ሸማች በማህበራዊ ጉዳዮች የተሳሰሩ እንደመኾናቸው በዋጋ እና የሚዛን መጠን ላይ የመደረደር፣ ትርፍና ኪሳራን በግልጽ የመነጋገር እንዲሁም “አንተ ትብስ” የመባባል ጠባያቸውን በገለጹ ነበር፡፡ ይኹንና አሁን ባለው የገበያ ሥርዓት እና የገበያ ዋጋ ተመን ሂደት ሁለቱ የገበያ ተዋናዮች እንዳይተማመኑ ኾነዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የመንደር ቸርቻሪዎች መንግስት ከተመነው ከፍ ባለ ነገር ግን ዝቅተኛ በሚባል ዋጋ ለመሸጥ ቢከጅሉም ሙሉ ለሙሉ ገበያው ላይ እጁን ያሳረፈውን አካል በመፍራት አንጻራዊ የተሻለ ከሚባል መፍትሄያቸው ታቅበዋል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ማለት ግን በመንግስት እርምጃ “የበጎነት ምትሃት” ውስጥ የታሰሩ የሉም ማለት አይደለም፡፡ በእርግጥ ኢኮኖሚው አሁን እያሳየ ያለውን ጠባይ ባለመገንዘብም ይሁን በቀጣይ የሚከሰተውን ባለመገመት በደፈናው የመንግስትን እርምጃ በጎ እንደኾነ የሚናገሩ አሉ፡፡ ይህ “ምትሃት” የግንባሩን ሐሳቦች ሁሉ በጭፍን በሚደግፉት አባላት ላይ የሚታይ ቢኾንም ለአገልግሎት እስከ 20 ብር መክፈላቸውን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ለአንድ ኪሎ ሥጋ 53 ብር በመክፈላቸው የሚፈነጥዙ ሸማቾች ላይም የሚስተዋል ነው፡፡ እንዲህ ያለው የ“ምትሃት” ስሜት በሸማቾች ዘንድ መፈጠር የገበያውን ሥርዓት የማናጋት ሚና ይኖረዋል፡፡ መውጫ ቀዳዳ ለሚፈልጉ “ብለጣ ብልጥ ነጋዴዎች” ያልተፈለገ የዋጋ ተመን ሥርዓት እንዲፈጥሩ መንገዱን ያመቻችላቸዋል፡፡
ያለፉት ኻያ ቀናት እንደ ባለፉት ኻያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዓመታት ሁሉ የተዋጣላቸው አልነበሩም፡፡ በሁሉም ጊዜያት ደግሞ ስማቸው ብዙም በመገናኛ ብዙሃን የማይነሳው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ንዋየ ገብረ ኣብ አሁንም ከቢሯቸው አሉ፡፡ ለአመታት የመሩት ቢሮም ኾነ እርሳቸው በስማቸው የሚጠቀስ የኢኮኖሚ ጥናት እና ምርምር ወይም ደግሞ የአገሪቷን የኢኮኖሚ ጉዞ የሚያሳይ ዘገባ አቅርበው አያውቁም፡፡ የአሁኑንም የሸቀጦች ዋጋ ማስተካከያ ከየትኛው የጥናት ውጤታቸው ተነስተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንደመከሩ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመከሩ ነው? የሚለውም የውስጥ ገመና ነው፡፡ ክፋቱ ግን የሕዝቡ ኑሮ የውስጥ ገመና አይደለም፡፡ ከላይ ቢሸፍኑት እግር ራቁቱን ይቀራል፤ ይህ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው፡፡