የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት “በማህበር ከተደራጁ ወጣቶች” ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ ተወያየ
(ሙሉ ገ.)
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶችንእና እናቶችን በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታዎች ላይ ለሁለት ቀናት አወያየ፡፡
በአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት የሚገኙ ምንጮች ለሪፖርተራችን እንደገለጹት ሰሞኑን በቱኒዚያ እና በግብፅ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመጽ ኢህአዴግን በእጅጉ አስቦታል፡፡
ቅዳሜ ጥር 21 ቀን 2003 ዓ.ም ከቀኑ በ3፡00 ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት አመራር አባላት በከተማዋ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ በተለያዩ ማህበራት፣ የወጣት ሊግ እና በአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራት የተዋቀሩ ወጣቶችን በተለያዩ ትምህርት ቤት አዳራሾች አነጋግርዋል።
በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ከተሰበሰቡ ወጣቶች መካከል ለሪፖርተራችን አስተያየቱን የሰጠ አንድ ወጣት እንደተናገረው ይህ የምክክር ስብሰባ ሳይሆን” የ1997 የሕዝብ ተቃውሞን ከአሁን በኋላ ዳግም እንዲከሰት አንፈቅድም” የሚል ማስፈራሪያና “ወጣቱን በተስፋ በማማለል ከኢህአዴግ ጋር እንዲሰለፍ የማድረግ ስትራቴጂክ አካሄድ ነው” ብሏል፡፡
ስብሳቢዎቹ “ አሁን ያለውን የሀገሪቱን የልማት ሂደት ለማስቀጠልና በአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት ወጣቱን በመላ ተሳታፊ ለማድረግ የጸጥታና የሀገር ደህንነት ጉዳይ ተቀዳሚው የመንግሥት ትኩረት መሆኑን” ለወጣቶቹ በመግለጽ “የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንደ ቱኒዚያና ግብጽ አይደለም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እሁድ ጥር 22 ቀን 2003 ዓ.ም ደግሞ ወላጆችን በተለይም በተለያዩ የሴቶች እና በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የተደራጁ እናቶችን የሰበሰበው የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤትና ፌዴራል ፖሊስ ለተሰበሰቡት እናቶች “ልጆቻችሁን ከአልባሌ ቦታ ተቆጣጠሩ፣ በኢትዮጵያ ላይ ልዩ ልዩ የሽብር ተግባራትን የሚያካሂዱ ቡድኖች ስላሉ ሳያውቁት ከእነርሱ ጋር እንዳይሰለፉ ተቆጣጠሩ፤ መንግሥት ሁሉንም ነገር በንቃት እየተከታተለ ይገኛል” በማለት አጭር መልዕክት ለተሰብሳቢው አስተላልፈዋል፡፡