[አንድ ለቅዳሜ ] ሥልጣን እንጂ ተጠያቂነት የሌለበት “የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ”

ኢሕአዴግ የምርጫ 2002 እፍረቱን ለማረሳሳት (ሊረሳ የሚችል ከሆነ) ብዙ ሙከራዎችን ማድረግ ነበረበት። የመጀመሪያው እና ትልቁም “የእድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” ተብሎ የቀረበው ሰነድ ነው። ዕቅዱ በይዘቱም ሆነ በቅርጹ ሰፊ የሐሳብ ልውውጥን የሚጋብዝ ነው። እስካሁን በብዛት ትኩረት የተሰጠው ግን ዕቅዱ ሊሳካ የሚችል በመሆኑና ባለመሆኑ ላይ ነው። ዕቅዱ የሚሳካም ይሁን አለዚያም የማይፈጸም፣ የሰነዱ ፖለቲካዊ ፋይዳ ተገቢውን ትኩረት ያገኘ አልመሰለኝም። እንደ ሁልጊዜውም እጅ እጅ የሚለው ፕሮፓጋንዳም ብዙዎች ሰነዱን ጨርሶ ማንበብ ቀርቶ ወሬውንም ለመጥላት እንዲቸኩሉ አድርጓል። ሆኖም ዕቅዱ ወደድነውም ጠላነው የአገሪቱን ሕይወት በተለያየ መልኩ የሚነካ እንደመሆኑ መገለል ሳይሆን በጥልቀት መተቸት ይገባዋል እላለሁ።

በዚህ አጭር ጽሑፍ ልመልሳቸው እንደማልችል ባውቅም ጥቂት ጥያቄዎችን ልሰንዝር። ጥያቄዎቹ የውይይቱን ፈር ከማሳየት አልፈው ቀያጅ እንዳይሆኑ ምኞቴ ነው።

1.      ዕቅዱ 2020ን (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) እንደ መዳረሻው ታሳቢ ያደርጋል። ሰነዱ እንዲያውም ያለፉትን አምስት ዓመታትም (1997-2002) የዚሁ የረጅም ዘመን (ከ1997-2020 ያሉትን 24 ዓመታት) ዕቅድ “የመጀመሪያ አምስት ዓመት” ብሎ ይጠራል። እንዲህ ያለ የ24 ዓመት (በማጠጋጋት የሩብ ክፍለ ዘመን እንበለው) አገራዊ የልማት እቅድ እንዳለ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቃልን? ምነው እቅዱ መኖሩና መጀመሩ ሳይበሰር ሁለተኛው የአምስት ዓመት እቅድ እንዲህ ተወራለት? ኢሕአዴግ ለምን የረጅም ዘመን ዕቅድ ኖረህ ተብሎ አይወቀስም፤ ይመሰገናል እንጂ። ጥያቄው ወዲህ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት የመውጫውን ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ የመራመድ ሸክም ላለባቸው አገሮች ይህን መሰል ዕቅዶች ቢሳኩም ሆነ ቢከሽፉ ውጤታቸው ለብዙው ዜጋ የሚተርፍ ነው። ስለዚህ እንደ ቻይና የሚልዮኖችን ሕይወት ለመገበር የሚፈቅድ “አብዮተኛ”  አመራርንና አመለካከትን የሚታገስ ታሪካዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው፤ አለዚያ ደግሞ ቢያንስ ዋና ዋና ፍላጎቶችን የሚወክሉ ቡድኖች ሌላው ቢቀር በመሠረታዊ ጭብጦችና ግቦች ላይ ሊመክሩበትና ሊስማሙበት የሚችሉበትን ከባቢ መፍጠር ያስፈልጋል።

ለየዋህ ተመልካች ኢሕአዴግ ሁለቱንም ጽንፎች (የማኦንም ሆነ የአገራዊ መግባባትን መንገድ) ያልመረጠ ይመስላል። ላይ ላዩን ስለ ብሔራዊ መግባባት ቢሰብክም ይህን የ25 ዓመታት አገራዊ ዕቅድ መተግበር ሲጀምር ለስሙ እንኳን ሰፊ የውይይት መድረክ (ድርጅቱ የሌሎችን ሐሳብ ፈጽሞ የማያስተናግድ ከመሆኑ አንጻር ውይይቱን ድራማ ልንለው እንችላለን) መጥራት አላስፈለገውም። እርግጥ አሁን “የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት” በሚል የሰበሰባቸውን ካብ አይገባ ድንጋይ የሆኑ ፓርቲዎች ሰብስቦ በዕቅዱ ላይ አስተያየት ስጡ ብሎ ሲጋብዛቸው ታይቷል። እንግዲህ በቃ አገር መከረበት ማለት ነው። በተቃራኒው ግን ኢሕአዴግ የማኦን (የቻይናን) አርአያ በመከተል ቁም ነገር ያለው ተቃራኒ ሐሳብ ሊያቀርቡ የሚችሉ ግለሰቦችን፣ ብድኖችን እና ማኅበራዊ/ሲቪል ተቋማት የሚያገል፣ የሚያርቅ እና ባስ ሲልም የሚያጠፋ ስልት ቀይሶ ተግባር ላይ አውሏል።

የዕቅዱ ስኬት አንድም በጉልበት በመፈጸሙ ከሚያስከፍለው ፈርጀ ብዙ ዋጋ፣ አለዚያም ወሳኝ ፍላጎቶችን የሚያስማማ መሠረት በማጣቱ/በማግኘቱ ከሚከተለው ውጤት ጋራ መያያዙ የግድ ነው። ዕቅዱ የማን ነው? የኢሕአዴግ፣ የመንግሥት፣ የአገር/የሕዝብ…? በ1997 ምርጫ ማግስት ይህን የሩብ ምዕተ ዓመት ዕቅድ አጽድቀው መተግበር መጀመራቸውን እየነገሩን ነው። እንዴት ያለ ድንቅ የጊዜ አመራረጥ ነው? በተለይ ብሔራዊ መግባባት ለሚያሻው ይህን መሰል ዕቅድ! በድጋሚ ዕቅዱ የማን ነው?

ይህን መሰል አገራዊ እቅዶች ተራ የቁጥር ግብ በማስቀመጥ የሚጠናቀቁ አይደሉም። ከዚያ በፊት ልንፈጥረው የምንፈልገው ማኅበረሰብ ምንነት/ማንነት ከታሪኩና ከተጨባጭ ሁኔታው በመነሳት መተንተኑን ይጠይቃል። ትምህርት ማስፋፋት አንድ ጥሩ ጉዳይ ነው፤ ግን የትምህርቱን ይዘትና ግብ መወሰን በመጨረሻ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑ ባይካሄድም የካድሬ ጨዋታም አይደለም። ለምሳሌ ስለ ትምህርት ጥራት ብዙ ይባላል። አሁን ደግሞ 70/30 የሚለው ሐሳብን መጥቷል። ለመሆኑ ይህ ሁሉ ሐሳብ ትምህርታችን አገራዊ ስር የለውም፤ ወደ ስሩ መመለስ አለበት የሚለውን ጥያቄ ተመልክቶታል? እንግዲህ የረጅም ዘመን አገራዊ ዕቅድ ሲነደፍ እንዲህ አይነት መሠረታዊ ጥያቄዎች ባይመለሱ እንኳን መነሣት አለባቸው ለማለት ነው። በድጋሚ ዕቅዱ የማን ነው?

2.     የዕቅዱ ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? ይህ “ዕቅዱ ሊሳካ ይችላል አይችልም?” ከሚለው ጠባብ ጥያቄ በመሠረቱ የተለየና የበለጠም አስፈላጊ ይመስለኛል። ዕቅዱ በወሳኝ መልኩ (ከ70 በመቶ ባላነሰ) ተሳካ እንበል። ይህ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ሕይወት ምን ማለት ነው? በተቃራኒው ዕቅዱ ሳይሳካ ቢቀርስ ምን አገራዊ ጣጣ ያመጣል? ጣጣው ወዴት ሊወስደን ይችላል?

3.     ዕቅዱ የሩብ ምዕተ ዓመት የመሆኑን ያህል የአገሪቱን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚያካትት አይደለም። እርግጥ ይህ በኢኮኖሚ ልማቱ ላይ ያተኮረ ሆኖ ሌሎች አጠቃላዩን ስእል የተሟላ የሚያደርጉ ተጓዳኝ እቅዶች አሉ ወይም በዝርዝር ይመጣሉ ከተባለ ጥያቄው ሌላ ይሆናል። 167 ገጾች ያሉትን ይህን ሰነድ ሳነብ የታዘብኩት አንድ ቁም ነገር ጸሐፊዎቹ ርእይ (ቪዥንን) ከዕቅድ (ፕላን) ጋራ የማምታታት ችግር እንደተጠናወታቸው ነው። ሰነዱ በአመዛኙ በቁሳዊ ልማት ላይ ያተኮረ ነው። ዕቅዱ በውጤቱም ሆነ በአፈጻጸም ሒደቱ በአገሪቱ “መንፈሳዊ/ባህላዊ” ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ምንድን ሊሆን ይችላል?

4.     የዚህ “አገራዊ ዕቅድ” ሰነድ አደገኛ ድክመት አንዳችም የተጠያቂነት መርህ የሚያነሳ አለመሆኑ ነው። በአንድ በኩል ዕቅዱ ቁልፍ ባለጉዳዮች ተሳትፈውበት የተቀረጸ ባለመሆኑ “አገራዊ” ለመባል ያለው እድል የተመናመነ ነው። ይህም ዕቅዱን የኢሕአዴግ ብቻ ያደርገዋል። አስቂኙ ነገር ሰነዱም ሆነ የሰነዱ ባለቤት የሆነው ኢሕአዴግ በአገሪቱን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊፈጥር የሚችለውን ይህን ዕቅድ ለመፈጸም ያስችላል ያለውን ሥልጣን እና ሀብት ሁሉ እንደተፈቀደ ሲቆጥር አንድም የተጠያቂነት ልጓም አያበጅም።

ለመሆኑ ይህ ዕቅድ ባይሳካ ተጠያቂ የሚሆነው ማነው? ለምሳሌ ኢሕአዴግ በሥልጣን ላይ ያለው በምርጫ አሸንፎ ነው እንበል። አሁን ያቀረበልንን ዕቅድ ማሳካት ቢሳነው ለባከነው ጊዜ፣ ሀብት ወዘተ ተጠያቂ ይሆናል? ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር አለ? ወይስ እስከዛሬ እንደሚደረገው ምን እንዳልተፈጠረ ተቆጥሮ ስለተገኘው ድል ብቻ እየተዘመረ ሌላ ዕቅድ ይቀርባል?

ሰነዱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር እና የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተለመደ ግምገማቸውን እንደሚሠሩ ከማተት በቀር የዕቅዱን አፈጻጸም የሚገመግም ገለልተኛ አካል እንደሚኖር አይጠቁምም። ይህ ማለት ኢሕአዴግ ራሱ ያወጣውን ፈተና፣ ራሱ መልሶ፣ ራሱ ነጥብ ሰጥቶ፣ ራሱን ይሸልማል እንደማለት ነው።

5.     በመጨረሻ አንድ የዋሕ ጥያቄ፤ የሰነዱ ደራሲ(ዎች) (እነ)ማን ናቸው? ይህን ማወቅ ስለሰነዱ ብዙ የሚነግረን ነገር ይኖራል። ሰነዱ ምን አይነት ውይይት እንደሚመጥነውም በቀላሉ ለመወሰን ያግዛል። ከጅምሩ የአዘጋጆቹ ማንነት እንደ አገር ምሥጢር የተያዘለት ዕቅድ አፈጻጸሙ ግልጽነት እና ተጠያቂነትን ይላበሳል ብሎ ማመን እንዴት መታደል ነው?!

በነገራችን ላይ

ቢቢሲ ለረሃብተኞች የተሰበሰበ ገንዘብ “ለመሣሪያ መግዣ ውሏል” በማለት ባቀረበው ዘገባ የተሳሳተ ትርጉም/ስሜት በሚሰጥ መልኩ ስሙ ተነስቷል ያለውን ባንድ ኤድ እና መስራቹን ቦብ ግለዶፍን ይቅርታ ጠይቋል። ታዲያ ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥትም እኔም ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ ሲል መግለጫ አውጥቷል። አልፎም ቢቢሲ ብቻ ሳይሆን ሒዩማን ራይትስ ዎችን (ኤች.አር.ደብሊው) የመሳሰሉ ስሙን በክፉ የሚያነሱ ሁሉ ይቅርታ እንዲጠይቁት ተማጽኗል፣ አሳስቧል።

ዓመቱ መንግሥት ይቅርታ እየተጠየቀ እርሱም ይቅርታ እየሰጠ የሚያልፍበት ሊሆን ነው ማለት ነው። ግን የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ አንድ ነገር በአባሪነት አያይዞ መላክ ነበረበት፤ ይቅርታ ጠያቂዎቹ ቢቢሲ እና ኤች.አር.ደብሊው የሚፈርሙበትን የይቅርታ ደብዳቤ አርቅቆ መላክ ነበረበት።

የቢቢሲው የአፍሪካ ኤዲተር ማርቲን ፕላውት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሐላፊዎች/ሪፖርት ጸሐፊዎች የሚፈርሙት የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ ምን እንደሚል መገመት መቼም ቀላል ነው። ይቅር ባዩ መንግሥታችን! ዓለም ሁሉ አጥፊ እና ይቅርታ ጠያቂ፤ አንተ ደግሞ ጻድቅ እና ይቅርታ ሰጪ ነህ።