አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፤ ስምንቱ ሚኒስትሮች አዲስ ናቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  ዛሬ በመሠረቱት አዲስ ካቢኔ አቶ ይለማርያም ደሳለኝ ትልቁን ስልጣን ተቆናጠዋል፡፡ ለረዥም አመት አቶ ስዩም መስፍን ይዘዉት የቆዩትን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ጋር ደርበው እንዲሠሩ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና የደኢህዴግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ይለማርያም ተመርጠዋል፡፡

አቶ መለስ ካቢኒያቸውን ሲመሰርቱ መመዘኛ ያደረጉት እድገትና ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት ህብረተሰቡን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ቁርጠኛ የፖለቲካ አመራር ብቃት አላቸው ብለው ያሰቧቸውን እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ 23 የካቢኔ አባላትን መርጠዋል፡፡

በአመዛኙ ለውጥ ያልታየበት የሚኒስትሮች ሹመት አንድ የፓርቲ አባል ያልሆኑ ግለሰብን የሚኒስትርነት ስልጣን ለመጀመርያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን እንዲመሩ የተመረጡት ግለሰብ አቶ መኮንን ማንያዘዋል ይባላሉ፡፡ የፓርቲ አባል ባይሆኑም ከጀማሪ ኢኮኖሚስትነት ተነስተው የፕላንና ኢኮኖሚ ምክትል ሐላፊ እንዲሁም የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ለንግድ ሚኒስትርነት የተመረጡት የሶዴፓ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ አብዱርማን ሼህ ማሀመድ ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በሶማሌ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡ አቶ ጁነዲን ሳዶ ይዘዉት የቆዩት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ለአቶ ደሴ ዳልኬ ተስጥቷል፡፡ አቶ ደሴ የሲዳማ  ዞን አስተዳዳሪ እና የደኢህዴን ስራ አስፈፃሚ ነበሩ፡፡

የህወሀት ታጋይ የነበሩት አቶ ደብረፅዮን  ገብረሚካኤል አዲሱን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲይዙ ተመርጠዋል፡፡

ሚኒስትር ሳይሆኑ የካቢኔ አባል አድርገው ጠቅላይ ሚኒስትር የሾሟቸው አቶ በረከት ስምኦን፣ወይዘሮ አስቴር ማሞን እና አቶ መላኩ ፋንታን ነው፡፡ አቶ በረከት ስምዖን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮችን እንዲይዙ፣ ወ/ሮ አስቴር የፓርላማ የኢህአዴግ ተጠሪ እንዲሆኑ እንዲሁም አቶ መላኩ ፋንታ የገቢና ጉምሩክን እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሳዶ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነት ተነስተው የአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የመከላከያ ሚኒስትር፣አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚኒስትር፣ ዶክተር ሽፈራው ተ/ማርያም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ አቶ ብርሀነ ሀይሉ የፍትህ ሚኒስትር፣ አቶ ሱፍያን አህመድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር፣ አቶ ተፈራ ደርበው የግብርና ሚኒስትር፣ አቶ ድሪባ ኩማ የትራንስፖርት ሚኒስትር፣ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኀኖም ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ባሉበት እንዲቀጥሉ ተመርጠዋል፡፡

ወይዘሮ ስንቅነሽ እጅጉ የማእድን ሚኒስትር ሆነዋል፡፡ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ መኩሪያ ሀይሌ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነዋል፡፡  አቶ አሚን አብዱልቃድር ከአፋር ክልል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነዋል፡፡ አቶ አብዱልፈታህ ሀሰን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡