አቅም ግንባታ ሚኒስትር ፈረሰ፤ 20 የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ተመሰረቱ

በአሁኑ ሰዓት በተወካዬች ምክር ቤት እየተካሄደ ባለው ስብሰባ አዲስ መስሪያ ቤቶች እየተቋቋሙ  ይገኛሉ፡፡ ምክር ቤቱ ዛሬ ከሚያፀድቃቸው ሶስት አጀንዳዎች መሀል የፌደራል የሥራ አስፈፃሚ አደረጃጀት አዋጅን ማፅደቅ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አዲሱን ካቢኒያቸውን ከማሳወቃቸው በፊት ይህን አዋጅ ያጸድቃል።

የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑን በፍጥነት ለማስፈፀም ምን አይነት አደረጃጀት ይሻላል ከሚል መነሻ ሀሳብ የፌደራል ሚኒስትር መስሪያ ቤቶችን በአዲስ ማዋቀር እንዳስፈለገ የተገለፀ ሲሆን አቶ ተፈራ ዋልዋ ይመሩት የነበረው የአቅም ግንባት ሚኒስትር ፈርሶ በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ተተክቷል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትርም ለሁለት እንዲከፈል የተወሰነ ሲሆን ህፃናት ወጣቶችና ሴቶች ሚኒስትር በሚል በአንድ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ ስፖርት በኮሚሽን ደረጃ ተቋቁሞ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ የእለቱ አንዱ አጀንዳም ይህንኑ የስፖርት ኮሚሽንን የሚያቋቁም አዋጅን ማፅደቅ ይሆናል፡፡

የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስትርም ወደ ሁለት ሚኒስትር መስሪያ ቤትነት ተቀይሯል፡፡ የንግድ ሚኒስትርና የኢንደስትሪ ሚኒስትር በሚል፡፡ ከሚቋቋሙት ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ስምንቱ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ እነዚህም ውስጥ የውጭ ጉዳይ ፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የጤና፣ የትምህርት፣  የገንዘብ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስትር ይገኙበታል፡፡

የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ለብቻው የማዕድን ሚኒስትርም እንዲሁ ራሱን ችሎ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ የትራንስፖርትና መገናኛ ሚኒስትር ለሁለት ተከፍሎ እንዲቀጥል የተወሰነ ሲሆን ትራንስፖርት ለብቻው የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆኖ ይቋቋማል፡፡የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም እንዲሁ ራሱን ችሎ ይወጣል፡፡የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ራሱን ችሎ ቢቀጥልም ቀድሞ ይሰራቸው የነበሩ አንዳንድ ተግባራት ለፍትህ ሚኒስትር እንዲሰጡ ተወስኗል፡፡