ዘሪሁን ሙላቱ በእስራት እና በገንዘብ ተቀጣ


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 14/2010፤ ጥቅምት 4/2003 ዓ.ም):- ‹‹የሐውልቱ ሥር ቁማርተኞች›› ጽሑፍ በወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና በጋሻው ደሳለኝ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ የቀረበበት ሊቀ ትጉሃን ዘሪሁን ሙላቱ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር እስራት እና በ2000 ብር እንዲቀጣ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ወሰነ፡፡ ዛሬ ጥቅምት አራት ቀን 2003 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ዘሪሁን ሙላቱ ራሱን ሆነ ብሎ ለመጥፎ ሥራ በማነሣሣት የግል ተበዳዮችን ሰብእና አጸያፊ እና አሠቃቂ በሆነ መልኩ በማዋረዱ፣ ይህም የግል ተበዳዮች በሚመሯቸው የሃይማኖት ሰዎች ዘንድ ተአማኒነት እንዳይኖራቸው የተደረገ ሤራ በመሆኑ የአንድ ዓመት ከሦስት ወራት፤ በተለያዩ የስልክ ቁጥሮች እየደወለ በማስፈራራት ከግል ተበዳዮች ገንዘብ በመጠየቁ የአምስት ወራት በአጠቃላይ የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት እስራት እና የ2000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኖበታል፡፡ የግራ ቀኙ ይግባኝ የመጠየቅ መብት የተጠበቀ ነው ያሉት ዳኛው ፖሊስ ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ታሳቢ በሚሆን መልኩ ቅጣቱን እንዲያስፈጽም በማዘዝ ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት ተመላሽ አድርገዋል፡፡ ዘሪሁን ሙላቱ በተላለፈበት ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ከቅርብ ወዳጆቹ የተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡