ወያኔ ህዝባዊ አመጽ ሊቀሰቅሱብኝ ነው የሚላቸውን ማሰር ቀጥሎአል። በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በርካታ ተማሪዎች ታስረዋል

ከዛሬ ነገ መጡብኝ በሚል ፍርሀት የተዋጠዉ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ንጹህ ዜጎችን ማሰር ስልጣኑን የሚያራዝምለት ይመስል በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የሆነ የእስር ዘመቻ መጀመሩን መድረክ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ከሰሞኑ ከወደ አዲስ አበባ ባሰራጨው ዜና ገለጸ። መድረክ ባሰራጨዉ በዚሁ ዜና አያይዞ እንደገለጸዉ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ ስርአት በየቀኑ እየወሰደ ባለዉ የቀቢፀ ተስፋ እርምጃ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የኦሮሞ ተወላጆች በጅምላ እየታሰሩ መሆኑን ገልጿል።

ሰዎችን በሰብእናቸዉ ሳይሆን ከተወለዱበት ብሔረሰብ አኳያ ብቻ የሚመለከተዉ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ እሱና ጓደኞቹ ለፈጠሩት የአንድ ጎሳ የበላይነት ስርአት አስጊ ናቸዉ ብሎ የጠረጠራቸዉን ሁሉ እስር ቤት እየወረወረ ከፍተኛ የሆነ የአካልና የህሊና ሰቆቃ እያደረሰባቸዉ መሆኑን መድረክ አክሎ ገልጿል። ከፍተኛ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ዶ|ር መራራ ጉዲና ይህንን አስመልክቶ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰጡት ቃለመጠይቅ “የኦነግ አባላት ናቸው” እየተባለ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ የመመረቂያ ግዜያቸዉን በጉጉት ይጠባበቁ ብዛት ያላቸዉ የኦሮሞ ተማሪዎች እየታፈኑ ወደ እስር ቤት እንደሚወሰዱና፤ በየእስርቤቱ ከፍተኛ ድብደባና ስቆቃ ይፈጸምባቸዋል ሲሉ ዶ/ር መረራ በምሬት ተናግረዋል።

የወያኔ ስርአት ይህንን የመሰለ መጠነ ሰፊ የእስር ዘመቻ የከፈተዉ ሰሜን አፍሪካ ዉስጥ አምባገነኖችን ለብልቦ መድረሻ ያሳጣዉን የአብዮት ሰደድ እሳት ኢትዮጵያም ውስጥ ለማቀጣጠል ተግተው የሚሠሩ ሃይሎች አሉ በሚል ሰበብ ሲሆን የጥቃት ኢላማዉ በተናጠል በኦሮሞ ተወላጆች ለምን አንዳነጣጠረ ግን ለጊዜው በዉል የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም አንዳንድ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚናገሩት በኦሮሚያ ውስጥ ለረጂም ግዜ ኦነግን ትደግፋላችሁ በሚል ሰበብ ብቻ በህዝቡ ላይ የሚፈፀመዉ ሂሊናን የሚሰቀጥጥ በደል ወጣቱን ክፍል እጅግ እያስቆጣ ስለመጣ በአገራችን ውስጥ በዬትኛውም ጊዜና ቦታ ሊፈነዳ ይችላል ተብሎ የሚጠበቀዉን ህዝባዊ አብዮት ኦሮሚያ ዉስጥ ሊጀምር ይችላል የሚል ስጋት ወያኔን ስላስጨነቀዉ እንደሆነ በግልፅ ይነገራል።

 ፍትህ እኩልነትና ዲሞክራሲን አገራችን ዉስጥ ማስፈን የሚቻለው የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ ለራሱ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ ሲል የገነባዉን የዘር ግድገዳ አራርሶ የህብረት ትግል ሲጀምር መሆኑ የገባቸዉ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ተሰባስበዉ በጋራ መታገል መጀመራቸዉ ወያኔን ክፉኛ እንዳሰደነገጠዉ ብዙ ተአማኒነት ያላቸዉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። የኢትዮጵያዉያን ህብረት ወያኔን እርቃኑን አስቀርቶታል የሚሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የወያኔ የድህንነት ሃላፊ፤ ህዝቡ በጋራ ‘ሆ ‘ ብሎ ወደጎዳና ከወጣና የወያኔን ጥቃት ተቋቁሞ እንደ ግብፅና ቱኒዝያ ህዝብ በጽናት ከቆመ እጃቸዉ በደም ከተነከረዉ ከመለስና በረከት ስምዖን በስተቀር ሁሉም የኢህዴግ አባላት የህዝቡን ትግል ከመቀላቀል ወደኋላ እንደማይሉ በእርግጠኛነት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መለስ ዜናዊ ኦህዴድ የኦነግ ታናሽ ወንድም ነዉ በሚል ሰበብ በኦህዴድ አባላትና በኦሮሞ ህዝብ ላይ የጀመረው የእስር ዘመቻ በሰላም አገር ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ወደሚገኙ የኦሮሞ ድርጅቶች ዘልቆ በመግባት ባለፈዉ ሳምንት የኤፌዴን ምክትል ዋና ጸሀፊ የሆኑት የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ መምህር አቶ ብርሀኑ እምሩን ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ዉጭ አስሮ ቃሊቲ መወርወሩን ተያይዞ የደረሰን ዜና ያመለክታል።