በወያኔ አገዛዝ ዘመንና በቀደምቶቹ 2 መንግሥታት መካከል ስላለው የመሬት ፖሊሲ ልዩነት እንዲብራራለት አስተማሪውን በመጠየቁ ለእስር የበቃው ተማሪ አስቻለው ቢራቱ በከፍተኛ ስቃይ ላይ መሆኑ ተዘገበ
በቀደሙት ሁለት መንግሥታትና አሁን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ የመሬት ፖሊሲ መካከል ያለው ልዩነት እንዲገለጽለት የምጣኔ ሐብት አስተማሪዉን በትምህረት ክፍለ ጊዜ የጠየቀው ተማሪ ተማሪዎችን ለአመጽ የሚያነሳሳ የፖለቲካ ጥያቄ ጠይቀሃል ተብሎ ለእስር የተዳረገው ተማሪ አስቻለው ቢራቱ በታሰረበት እስር ቤት ውስጥ ለከፍተኛ የምግብ ችግር መዳረጉን ኢሳት ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
በአሁኑ ሰዓት በቡታጀራ እስር ቤት ውስጥ የሚገኘው ተማሪ አስቻለው ከላይ የተገለጸውን ጥያቄ በመጠየቁ ብቻ ወንጀለኛ ተደርጎ ፍርድ ቤት ከቀረበ ቦኋላ የአንድ አመት ጽኑ አስራት እንደተፈረደበትና ወላጆቹ ውሳነውን ተቃውመዉ ይግባኝ ቢጠይቅም ፍርዱ እንጸናበት ቀደም ሲል መዘገቡ ይታወሳል።
በዘንድሮው አመት የ12ኛ ክፍል መሰናዶ ተማሪ የነበረው ተማሪ አስቻለው በሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ላይ እንደሚደረገው በሃሰት በተቀነባበሩ 7 ክሶች የተከሰሰ ሲሆን ክሶቹም ተማሪውን ለአመጽ ለማነሳሳት፤ የመማር የማስተማር ሂደቱን ለማወክ፤ የጸረ ሰላም ሃይሎች መሳሪያ በመሆን ሰላምና እድገት ለማደፍረስ ወዘተ የሚሉ በተቃዋሚዎች ላይ በተከታታይ የሚቀርቡ ተራ የዉንጀላ ክሶች ናቸዉ።
ተማሪ አስቻለው ፈጽመሀል በተባለው ጥፋት ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአንድ አመት እስራት እንዲቀጣ የወሰነበት በመሆኑ የዘንድሮውን ማትሪክ ፈተና መውሰድ እንደማይችል የታወቀ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ቤተሰቦቹ ከሚገኙበት ከቡታ ጅራ ርቆ ሆሳእና ዉስጥ በሚገኘው ማረሚያ ቤት እንዲታሰር በመደረጉ ተማሪው ከፍተኛ የምግብና የአልባሳት ችግር ገጥሞት እንደነበር የሆሳእና ማረሚያ ቤት በቁጥር ደኢማ 13/1926/ 03 የጻፈው ደብዳቤ ማመልከቱን ኢሳት ዘግቧል።
ተማሪ አስቻለው በትምህርቱ ጎበዝ ከመሆኑም በላይ ለተማሪዎች መብት የሚሟገት በመሆኑ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች በጣም እንደሚወዱትና እንደሚያከብሩት ኢሳት የዘገበ ሲሆን ተማሪው በአካባቢው ያለው አስተዳዳር መበላሸት፣ መንግስት ትምህርት ቤቱን የፖለቲካ መናሀሪያ ማድረጉንና በመምህራን ላይ የሚደርሰውን ጭቆና ሳይቀር አጥብቆ በመቃወም የሚታወቅ ከእድሜው በላይ በሳልና ደፋር ነው ተብሏል።