በአማራ ክልል የሚገኙ ገበሬዎች የማዳበሪያ ዋጋ ስለተወደደባቸው ላለመግዛት መማማላቸው ታወቀ

የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን በተደጋጋሚ እንደዘገበው በአማራ ክልል የሚገኙ አርሶ አደሮች አምና በ900 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ማዳባሪያ በአንድ ጊዜ አንድ ሺ 200 ብር በመግባቱ ዋጋው እስካልተስተካከለ ድረስ ምንም አይነት ማዳበሪያ ላለመግዛት መወሰናቸውንና ይህንን ውሳኔ የሚጥስ እንዳይኖር በየቤተክርስቲያኑ መማማላቸው ታውቋል። ከእሳት ዘጋባ መረዳት እንደተቻለዉ አርሶ አደሮቹ ይህንን እርምጃ ለመዉሰድ የበቁት በማዳበሪያዉ ዋጋ መናር ብቻ ሳይሆን በየአመቱ ለምርት የሚጠቀሙበት የምርጥ ዘር ዋጋ በአንዴ በማሻቀብ የአንድ ኩንታል ምርጥ ዘር ዋጋ ከ2 ሺ 500 ብር በላይ በማሻቀቡ ነዉ።

ኢትዮጵያ ወስጥ በየግዜዉ እያዘቀዘቀ በመጣዉ የኑሮ ውድነት ክፉኛ ከተጎዱት የህብረተሰብ ክፍሎች አንዱ ገበሬዉ ሲሆን ይህ አሁን የታየው የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር ዋጋ ንረት በመጪው የግብርና ምርት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽኖ ከመፍጠሩ ሌላ ገበሬዉንም ሆነ ሌላዉን ሸምቶ አዳሪ ህዝብ ከፍተኛ ችግር ዉስጥ እንደሚከተዉ ብዙዎች በአጽንዖት ይናገራሉ። እነዚህ በዋጋ ንረት የተማረሩት ገበሬዎች ወያኔ በአስቸኳይ ልዩ ድጎማ አድርጎ የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ዋጋን ካላረጋጋ፣ የጀመሩትን አድማ እንደማያቆሙ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ዉስጥ ማዳበሪያ በማስመጣትና በማከፋፋል ስራ ላይ የተሰማራው አምባሰል የተባለው የወያኔ ኩባንያ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት የሂሳብ ምርመራ የማያውቀው ድርጅት እንደሆነና አስከዛሬ ሂሳቡን ኦዲት አስደርጎ እንደማያውቅ ይታወቃል።

ከዚሁ ከዋጋ ጋር በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ቃሊቲ ዉስጥ የሚገኘው እስር ቤት ከዋጋ ጭማሪ ከቫትና ከካሽ ሪጀስትር ጋር በተያያዘ በሚታሰሩ ነጋዴዎች በመጨናነቁ ቁጥራቸዉ በዛ ያለ ነጋዴዎች ወደ ሸዋ ሮቢት እስር ቤት በግዴታ እየተዛወሩ መሆናቸው ታውቆአል።የኢሳት ዘጋቢ የእስር ቤቶችን ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው ቫት አጭበርብራችሁዋል በሚል የሚታሰሩ ነጋዴዎች ቁጥር መጨመር በአገሪቱ ውስጥ የእቃዎችን እጥረትና የዋጋ ውድነቱን አባብሶታል ተብሎአል።

በቅርቡ የዋጋ ግሽበትን እንቆጣጠራለን በሚል ሰበብ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ያወጀዉ የዋጋ ቁጥጥር ዘይትና ሌሎችም መሠረታዊ ሸቀጦች አገሪቱ ሙሉ እንዲጠፉ ምክንያት በመሆኑ ወያኔ እንደቀድሞው የመንግሥቱ ሃይለማሪያም ዘመን በቀበሌ አማካይነት በየወሩ አንድ አንድ ሊትር ዘይት በነፍስ ወከፍ ማከፋፋል ጀምሯል። በወር አንድ ሊትር ዘይት እንኳን አራትና አምስት ልጅ ያለበትን ቤተሰብ ወንደላጤዉንም ሳምንት እንደማያቆየዉ እየታወቀ ይህ ወያኔ የጀመረዉ የዘይት ቸርቻሮ ዘመቻ ስህተትን በስህተት ለማረም የሚደርግ አጉል ሩጫ እንጂ ሸማቹን ህብረተሰብ እንደማይጠቅም ህዝቡ ካወቀዉ ቆይቷል። ከአዲስ አበባና ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደሚሰማዉ አገሪቱ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ መውጣቷ በገሀድ ይታያል። “ህዝቡ ምን በልቼ ልደር በሚል ሀሳብ በመጠመዱ ምንም ነገር ለማሰብና ለማሰላሰል ተስኖታል” ሲሉ ህዝቡ ያለበትን የኑሮ ሁኔታ ገልጸዋል።