በኢንቨስትሜንት ስም የሚካሄደው የደን ጭፍጨፋ እጂግ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱ ተዘገበ

በተፈጥሮ ደን ክምችታቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚታወቁትና በኢንቨስትመንት ስም ለባለሃብቶች የተቸበቸቡት ሰፋፊ ቦታዎች፣ በባለሃብቶቹ እየተጨፈጨፉና ከሰል ለማምረትም እየተቃጠሉ እንደሆነ የቤሻንጉል ጉምዝ ክልል ምንጮቹን በመጥቀስ የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ገለጸ።

በክልሉ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የደን ቃጠሎ እንደሚካሄድ፣ ለእርሻ ስራ ብለው የሄዱ ባለሀብቶችም ደኑን በማቃጠልና ከሰል በማክሰል ወደ ውጭ እንደሚልኩ፣ የመንግስት ባለስልጣናትም በጥቅም እየተደለሉ አገሩን እያወደሙ መሆኑን የአካባቢው ሰዎች ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ መናገራቸውን ዘጋቢያችን ከስፍራው ያገኛቸውን ምንጮች በመጥቀስ ገልጹአል።

 ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለግብርና ልማት መሬት የወሰዱ ኢንቨስተሮች የሚያካሂዱትን መጠነ ሰፊ የደን ምንጣሮና ቃጠሎ አቁመው መሬቱን በአግባቡ እንዲይዙ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትዕዛዝ መስጠቱን ሪፖርተር የተባለው አፍቃሪ ህወሃት ጋዜጣን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘግቡአል።

የዘረኛውና አምባገነኑ መለስ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚሊየኖች የሚቆጠር የሃገሪቱን ለም መሬት በነጻ ሊባል በሚችል ደረጃ ለውጪ ሃገር ባለሃብቶች በማደል ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። የአገራችንን ለም መሬት ለባዕዳን ተቀራማቾች አሳልፎ በመስጠት የወያኔ ጸረ አገር ፖሊሲ ውስጥ እጅግ የሚገርመውና የሚደንቀው በመሬት ጥበት ለዘመናት ተጨናንቆ እና ተጣቦ በሚኖረው የአማራ ክልል ከመንዝ ህዝብ ተነጥቆ ለውጪ ባለሃብት ተሰጠ የሚባለው መሬት ጉዳይ ነው። በጋምቤላ፤ በቤነሻንጉል እና በኦሮሚያ አስከቅርብ ጊዜ የተቸበቸበው መሬት ሰው ያልሰፈረበት ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩ የነበሩ ለወያኔ ያደሩ ባንዳዎች ፤ ከመሬቱ ጥበት የተነሳ በተራራ ላይ ተንጠልጥሎ ከሚኖረው የመንዝ ህዝብ ላይ ስለተቀማው ሰፊ ቦታ ልማትን በክልሉ ለማስፋፋት ነው የሚል ሽፋን እየሰጡት እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል። ካራቱሬ እየተበለ የሚጠራው የህንድ ኩባንያ ዋና ሥራአስኪያጅ ስለመሬት ቅርምት ዶክሜንታሪ ፊልም ላዘጋጀ የውጪ ጋዜጠኛ፤ ኩባንያው እራሱ ማመን እስኪያቅተው ድረስ እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ “ኑና ውሰዱ ተብሎ በለጋስነት የተሰጠን ቦታ ነው ” በማለት በደስታ እየፈነደቀ ምስክርነት ሲሰጥ ተዘግቦ ለአለም ተሰራጭቶአል።

የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢንቨስትመንት ስም የውጭ አገር ባለሀብቶች የእርሻ መሬት ለመቀራመት ወደ ኢትዮጵያ እንዲጎርፉ ማድረጉን ተከትሎ የአገሪቱ የደን ሀብት በከፍተኛ ደረጃ መራቆቱ በርካታ ብርቅየ የዱር እንስሳትም ሊተኩ በማይችሉበት ሁኔታ እየወደሙ አካባቢውም ወደ ምድረ በዳነት እየተቀየረ መሆኑን በርካታ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች እያሳሰቡ መሆኑ በስፋት ይታወቃል።