አባዱላ ገመዳ ባለአራት ፎቅ ቤቱን ተነጠቀ

አገራችንን በማፍረስ ተልዕኮ እና በሃብት ምዝበራው ወንጀል የተጠመደው ዘረኛው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች በትናንሽ ጥቅማ ጥቅሞች እና መደለያ በዙሪያው ያሰባሰባቸውን አንዳንድ ግለሰቦች በተለያየ ውንጀላ የማስወገድ ተግባሩን እየገፋበት እንደሆነ በዚህም ምክንያት አባዱላ ገመዳ የወቅቱ ተረኛ እንደሆነ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቁ።

ለረጅም ጊዜ የኦሮሚያ ክልልና የኦህዴድ ፕሬዝዳንት በመሆን በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የአጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሲያስተገብር የቆየው አባ ዱላ ገመዳ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ከመለስ ዜናዊ ጋር በገባበት አለመግባባት ግልጽና ስውር ተጽዕኖዎች እየደረሰበት እንደሚገኝ ለግለሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አረጋግጠዋል።

እንደ የኦሮሚያ አካባቢ ምንጮች መረጃ በአባዱላና በመለስ ዜናዊ መካከል የነበረውን አለመግባባት የተባባሰው ሸክ አላሙዲን በኦሮሚያ ክልሉ በስሙ ይዞት የነበረውን ሰፊ የልማት ቦታ ለረጅም ጊዜ ምንም የግንባታ ሥራ አልሰራበትም በማለት እንዲወረስ ካስደረገና በኦህዲድ ሥር የሚተዳደረው የድንሾ ንግድ ድርጅት በጫት ንግድ ገቢያ የነበረውን ድርሻ የመለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ለመቆጣጠር ጣልቃ ስትገባ ለማስቆም ከተፍጨረጨረ ቦኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመለስ ዜናዊ በቀጥታ የሚተላለፈው ቀጭን ትዕዛዝ ክልላችንን ይጎዳል በማለት ቅሬታ ያሰሙ ከከፍተኛ አስከ ተራ የኦህዲድ አባላት ያሉ ግለሰቦች በሙስናና በኦነግ አባልነት ተወንጅለው ከርቼሌ እንደወረዱ በተለያየ ሚዲያ መዘገቡ ይታወሳል ። አባዱላ ገመዳ በትርፍነት ከተመራው የከተማ ቦታ አንዱን በቅርቡ ለድርጅቱ ኦህዲድ አውርሶ እንደነበረ የሚያስታውሱ ምንጮቻችን በተጨማሪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ቦሌ ወሎ ሰፈር አካባቢ ያስገነባውን ባለ አራት ፎቅ መኖሪያ ቤቱን በሙስና ሰበብ መነጠቁን ገልጸዋል። የአባዱላ ጣጣ በዚህ ሳያበቃ ተጨማሪ ክስ በጸረሙስና ኮሚሽን በኩል ሊመሰረትበት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

አባዱላ ገመዳ በቅርቡ ለህክምና ሰበብ ወደ ጀርመን መጥቶ እንደነበርና ከመለስ ዜናዊ የሚደርስበትን ውርደት ለመሸሽ ጥገኝነት የመጠየቅ ሃሳብ እንደነበረው ነገር ግን በስደት ህይወት ውስጥ ያለውን ውጣ ውረድ የመቋቋም ፍርሃት ገብቶት ሃሳቡን እንደቀየረና በመጣበት እግሩ እንደተመለሰ ተያይዞ የደረሰን መረጃ አረጋግጦአል።

ለመለስ ዜናዊ ባላቸው ታማኝነት ብቻ ዕውቀት እና ችሎታቸው በማይመጥናቸው የስልጣን ማማ ላይ ከተፈናጠጡት የጄሌ ድርጅቶች መሪዎች መካከል ከመለስ ዜናዊ የሚደርስባቸውን ውርደት ለማስቆም የምቾት ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ብዙ አይደሉም። የቤንሻንጉል እና ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት የነበረው ያረጋል አይሸሹም ከሁለት አመት በፊት በስደት ካናዳ ከደረሰ ቦኋላ ወዲያው ተጸጽቶ ይቅርታ በመጠየቅ ለመለስ ዜናዊ መልሶ እጁን እንደሰጠ ይታወሳል።