ለመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ከዋጋ ንረቱ ጋር አብሮ ባለማደጉ በቂ አይደለም ተብሏል

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ህዝባዊ አመጽ በመፍራት እየወሰዳቸው ካሉት እርምጃዎች ውስጥ አንዱ፥ ለኢትዮጵያ መንግስት ሰራተኞች እዚህ ግባ የማይባል የደሞዝ ጭማሪ መስጠት እንደሆነ ይታወቃል። ይሁን እንጂ፥ ከሰሞኑ ሪፖርተራችንን ያናገሩ መንግስት ሰራተኞች፥ የተደረገው ጭማሪ ከመዘግየቱም በላይ እጅግ ትንሽ ነው ሲሉ አማረዋል።

ሪፖርተራችን ያናገራቸው አንድ የኢኮኖሚክስ ተማሪ፥ በሌሎች አገራት የዋጋ ንረት ሲከሰት የሰራተኞች ደሞዝም ያንን መቋቋም እንዲችል በሚል በየጊዜው ይጨምራል ይላሉ። በኢትዮጵያ ግን የሰራተኞች ደሞዝ አንድ ቦታ ቆሞ የዋጋ ንረቱ እጥፍ ድርብ ሲጨምር ቆይቷል፤ ይህም መንግስት ሰራተኛውን በቁጣ ሞልቶታትል ሲሉ አስረድተዋል። አሁንም ቢሆን የተጨመረው መጠን በአሁኑ ሰዓት ያለውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አያስችልም ብለዋል።

አገዛዙ ከአሁን በኋላ ዝቅተኛው የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝ ከ333 ብር ወደ 444 ከፍ ብሏል ማለቱን በሚመለከት፤ ይህ ማለት ባለፈው ሳምንት በአንድ ወር ደሞዙ ስድስት ኪሎ ከግማሽ ስጋ መግዛት ይችል የነበረው ሰራተኛ አሁን ወደ ስምንት ኪሎ ከግማሽ መግዛት ይችላል ማለት ነው ሲሉ በምጸት ተናግረዋል። እሳቸው በሚኖሩበት አገር የአንድ ኪሎ ስጋ ዋጋ በዝቅተኛው ደሞዝ የሚተዳደር ሰራተኛ በአንድ ሰዓት ውስጥ ከሚያገኘው ገንዘብ ያነሰ ነው ሲሉም አነጻጽረዋል።