የአዲስ አበባ ወጣቶች የወያኔው አገዛዝ የከለከለውን ባንዲራ በጥምቀት በአል አውለበለቡ

በአዲስ አበባ የተከበረውን የጥምቀት በአል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር በሚል ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በቡድን የተደራጁ ወጣቶች በዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ልዩት ዕዛዝ ህዝብ በተሰበሰበባቸውና በማንኛውም ኦፊሴላዊ ቦታዎች እንዳይውለበለብ በአዋጂ ያገደውን በማሃሉ አንባሻ የሌለውን አረንጓደ ቢጫ ቀይ ቀለም የኢትዮጵያዊያን ስንደቅ አለማ በጉልበት  በማውለብለብ ማሳለፋቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ሪፖርት ገልጹአል:: ወጣቶቹ በዚሁ እለት በየአካባቢያቸው የሚገኙ የታቦት ማለፊያ መስመሮችን በራሳቸው ተነሳሽነት ማጽዳታቸውንና ቄጠማም መጎዝጎዛቸውን አክሎ ገልጹአል::

በወያኔ ድርጅታዊ መዋቅር የተደራጁ የከተማይቱ ልዩ ልዩ የወረዳ ባለሥልጣኖች በራሳቸው አነሳሽነት የተሰባሰቡትንና  የታቦቱን መሄጃ መንገዶች በማጽዳት ላይ የነበሩትን እነዚህን ወጣቶች ለማስቆም ሞክረው እንደነበረና በተለይ አገዛዙ በአገሪቱ የትኛውም ክፍል አገልግሎት ላይ እንዳይውል የከለከለውን ባንዲራ አንዳያውለበልቡ ለማስፈራራት ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱን ዘጋቢያችን በቦታው ተገኝቶ እንደተመለከተ በላከው ሪፖርት ገልጹአል። በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ የተደናገጡት የወያኔ ባለሥልጣናትና የደህንነት ሰዎች ከወጣቶቹ ጋር አታካሮ መግባት ወደ አልተጠበቀ አመጽ ሊሸጋገር ይችላል ከሚል ስጋት ዝም ብለው ከርቀት ሆነው ለመከታተል እንደተገደዱና  እነርሱ “የጥፋት ኀይሎች” የሚሉዋቸው ተቃዋሚዎች መጠቀሚያ እንዳያደርጉዋቸው በማለት በከፍተኛ አይነ ቁራኛ ሲከታተሉዋቸው እንደዋሉ ለማወቅ ተችሎአል ። በቤተክሪስቲያኖች አካባቢ ያሉ የወያኔ ታማኝ አገልጋዮች ከጽጥታ ሃይሉች ጋር በመተባበር የወጣቶቹን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ሲከታተሉ እንደነበር ፤ ተቃውሞ የሚያስነሳ ጽሁፍ ያለበት ቲ-ሸርት እንዳይለብሱ ፤ በ እጃቸውም ምንም አይነት ‹ተንኳሽ ጽሑፎች› ያለበት ነገር እንዳይይዙ ፤ ሲከታተሉ እንደነበር ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል። አንዳንድ ወጣቶች በጸጥታ ሃይሉ ሰራተኞች  ቄጤማ ከመጎዝጎዝ እና ምንጣፍ ከማንጠፍ እንዲቆጠቡ፣ ወያኔ ያወጣውን የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም መመሪያ እንዲያከብሩ ተነግሮአቸው እንደነበረ ነገር ግን ሰሚ እንዳላገኙ እንዲያውም አኛ የፈለግነውን ብናደርግ ምን ይመለከታችኋላ እስከማለት እንደደረሱ ታውቆአል።

ከዚህም ባለፈ መልኩ ለወያኔ ካደሩ የወጣቶችና ሴቶች ማህበራት በጥምቀት በአል የወያኔው አምባገነን አገዛዝ የከለከለውን ባንዲራ እናዳይጠቀሙ ማስፈራሪያና ዛቻ ለወጣቶች ቢያስተላልፉም ወጣቶቹ ይህን ዛቻ ከቁብ ሳይቆጥሩ በእምቢተኝነት የሚያምኑበትን የኢትዮጵያ ባንዲራ ማውለብለባቸውን ገልጾልናል::

ወጣቶቹ በራሳቸው ተነሳሽነት እንዴት እንዲህ አይነት ህብረት እንደፈጠሩና ለምንስ የወያኔን ባንዲራ አናውለበልብም እንዳሉ ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ወጣቶች እኛ በአምባገነኑ አገዛዝ ወኪሎች አማካኝነት ለሚቀርብ ጥሪ ሁሌም ቦታ አንሰጥም፣ እኛ የምንፈልገው በህዝብ የተመረጡ መሪዎች እንዲመሩን ነው፣ እስከዚያው ድረስ በራሳችን ተነሳሺነት የምናከናውናቸውን ተግባሮች ደስ ብሎን እናከናውናለን ብለዋል፣ ፣ ወጣቶቹ ቀጥለውም ወደፊትም ቢሆን ከወያኔው አገዛዝ የሚቀርብልንን ጥሪ በፈቃደኝነት አንቀበልም፣ ትክክለኛው ጊዜ ሲመጣና ሁኔታዎች ሲመቻቹልን ለዓለም ማንነታችንን እናሳያለን ሃገራችንንም ወደፊት እናራምዳለን በማለት መልሰዋል::