የቱኒዚያዊያኑ የበቃኝ ርምጃና ተሞክሮው
በቃኝ! በቃኝ! በቃኝ! መረገጥ በቃኝ! መዘረፍ በቃኝ! መገደል በቃኝ! መታሰር በቃኝ! መዋረድ በቃኝ! ። ህዝቡን እንደ ጠላት ረግጦ ሲገዛ የቆየውን አምባገነን፣ ከስልጣን ያባረረው የቱኒዚያ ህዝብ ድምጽ!
ለሃያ ሶስት አመታት በብረት በትር ከገዛ በኋላ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣኑ የተፈነገለው እና ባለፈው አርብ ከአገሩ ሸሽቶ የወጣው የቱኒዚያው ዚን ኤል አቢዲን ቤን አሊ በሚያስገርም ሁኔታ ኢትዮጵያን በጉልበት ከሚገዛው መለስ ዜናዊ ጋር ተመሳሳይ ታሪክ አለው።
ቤን አሊ ከሱ ቀድሞ የነበረውን ገዢ በብቃት ጉድለት እና በጭካኔ ወቅሶ፤ ዴሞክራሲ እና ለውጥን ቃል ገብቶ ወደ ስልጣን የመጣው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1987 ነበር። ወደ ስልጣን ከመውጣቱ በፊት በአገሪቱ የደህንነት ተቋማት ውስጥ ለበርካታ አመታት የሰራው ግለሰብ ግን፣ በቱኒዚያ ዴሞክራሲን የማስፈን አላማ እንደሌለው ለማሳየት አንድ የምርጫ ዘመን አልፈጀበትም።
ቤን አሊ በቱኒዚያ የውትድርና እና የደህንነት መዋቅራት ውስጥ በነበረባቸው ጊዜያት በገነባው ድጋፍ ላይ ተንተርሶ በህዝቡ ውስጥ ፍርሃትን በማስፈን የሚገዛን አምባገነናዊ ስርአት ገነባ። ስልጣን በያዘ በስድስተኛ አመቱ ባካሄደው ምርጫ ተብዬ መቶ በመቶ አሸፍኩ አለ። ከአምስት አመታት በኋላ በተካሄደው ምርጫ 99.4 በመቶ፤ ባለፈው አመት በተካሄደው ደግሞ 90 በመቶ።
እንደሱ ካሉ አምባገነናዊ አገዛዞች በሚጠበቅ መልኩም፥ የሰብአዊ መብት ረገጣ በቱኒዚያ ውስጥ ሰፈነ። ህዝቡ እራሱን የመግለጽ እና የመሰባሰብ መብቱን ተነጠቀ፤ ጋዜጠኞች ታፈኑ፣ ተሰደዱ፤ በርካታ ዜጎች ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ለሰቆቃ ተዳረጉ። በአገሪቱ ውስጥ እና በውጪ ያሉ የገለልተኛ መረጃ አውታሮች ታፈኑ፤ ዜጎች በጨለማ እንዲኖሩ ተፈረደባቸው። እንዲህ አይነቱ ግፍ ለኛ አዲስ አይደለም።
የቤን አሊ አገዛዝ ከሰብአዊ መብት ረገጣና አፈና ባሻገር፤ እንደ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ሁሉ፥ በሙስና፣ በአድሎ፣ በስራ አጥነት እና በኑሮ ውድነት ቀለሞች ያጌጠ ነበር። በተለይም፥ የቤን አሊ ቤተሰቦች እና የነገዱ አባላት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በስራ አጥነት በሚሰቃይበት አገር፣ አብዛኛውን ትርፋማ የንግድ ዘርፍ ሁሉ ተቆጣጥረው ሃብት አጋበሱ። ከመለስ ዜናዊ ሚስት አዜብ መስፍን ሁኔታ ጋር እጅጉን በሚመሳሰል መልኩ፤ የአምባገነኑ ባለቤት ለኢላ ትራበልሲ ከህዝብ በተሰረቀ ሃብት አጌጠች፣ አሸበረቀች፤ በውጭ አገራት የከፈተቻቸው የባንክ ሂሳቦች ሞልተው አፈሰሱ።
ልክ እንደ አዜብ መስፍን፥ ለኢላ ትራበልሲም ዘራፊነቷን ለመደበቅ እና የህዝብ ሰው ለመምሰል የከፈተቻቸው እና የመራቻቸው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እውነተኛ ማንነቷን ሊደብቁላት አልቻሉም።
የመንግስትን የደህንነት እና የመከላከያ መዋቅር በመጠቀም አንገቱን በረገጡት ህዝብ ላይ የተሳለቁት እነዚህ ባል እና ሚስት፣ የቱኒዚያዎቹ ቻውሴስኮዎች ተብለው ተጠርተዋል። ኒኮላ እና ኢሌና ቻውሴስኮ ሮማንያን ለሃያ ሁለት አመታት ረግጠው የገዙ እና የዘረፉ ባልና ሚስት መሆናቸው ይታወሳል። ከሃያ አንድ አመታት በፊት አገዛዛቸው በህዝባዊ አመጽ ከተገለበጠ በኋላም፤ ሁለቱም ተረሽነው አስከሬናቸው በቴሌቪዥን ታይቷል።
የኢሌና ቻውሴስኮን እና የአዜብ መስፍንን ተመሳሳይነት ከዚህ ቀደም ዘርዝረን ነበር። ሁለቱም በባለቤቶቻቸው ላይ ተንጠላጥለው ስልጣን በስልጣን ላይ የደራረቡ፤ ከህዝብ የዘረፉትን ገንዘብ ወደ ውጭ ያሸሹ፤ ህዝብ ሲራብ በውድ ልብስና ጌጥ ያሸበረቁ፤ ሰነፍ ተማሪዎች ሆነው ሳለ የውሸት ዲግሪዎች ያሰባሰቡ፤ እውነተኛ ማንነታቸውን ለመደበቅ በጎ አድራጊ መስለው ለመታየት የሚጥሩ፤ እንዲሁም ጉቦ በመስጠት ሽልማት እና ሙገሳን ከተለያዩ ተቋማት የሚያሰባስቡ መሆናቸውን አሳይተናል።
ታዲያ፥ ቤን አሊ እና ሚስቱ እንደ ቻውሴስኮዎች እንደ ረገጡት እና እንደዘረፉት የተረዳው የቱኒዚያ ህዝብ…መጨረሻቸውንም እንደነሱው ለማድረግ ቆርጦ ሳይነሳ አልቀረም።
የቤን አሊን እና የመለስ ዜናዊን አገዛዝ ከሚያመሳስላቸው ነጥቦች ውስጥ ሌላው፣ ሁለቱም ከውጭ አገራት፣ በተለይም ከምእራባውያኑ ጋር፣ ያላቸው ግንኙነት ነው።
ቤን አሊ በተለይ ከዛሬ ዘጠኝ አመታት በፊት በአሜሪካ ላይ የደረሰውን የሽብርተኞች ጥቃት ተከትሎ እንደ ብዙ የአለማችን አምባገነኖች እራሱን “ጸረ-ሽብርተኛ” ብሎ በመሾምና ከአሜሪካኖቹ ጋር በመወገን ድጋፋቸውን ለማግኘት ችሏል። እነሱም በህዝቡ ላይ ለሚፈጽመው ግፍ ጀርባቸውን ሰጡ። እንደ ፈረንሳይ ያሉ አገራትም እንዲሁ።
ባለፈው አመት በቱኒዚያ በተደረገው ምርጫ፣ ቤን አሊ 90 በመቶ በሚሆነው ድምጽ አሸንፌያለሁ ብሎ ሲያውጅ፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አገዛዙ ለአለም አቀፍ ታዛቢዎች በሩን አለመክፈቱን አውግዞ፣ ከቱኒዚያ ፕሬዚደንት እና መንግስት ጋር ያለውን ግንኙነት ግን አጠንክሮ እንደሚቀጥልበት ገልጿል። የወያኔ አገዛዝ ባለፈው አመት ካካሄደው የምርጫ ተውኔት በኋላ ምእራባውያኑ እንዲሁ ማለታቸውን ልብ ይሏል።
ከሁሉ ባሻገር ደግሞ፥ ምእራባውያኑ በቱኒዚያ ይሰሙ የነበሩትን የለውጥ ድምጾች ይመቱ የነበረበት ክርክር ስለኛም ከሚናገሩት ጋር ተመሳሳይ ነው። “በቱኒዚያ የኢኮኖሚ እድገት እየታየ ነው፣ እሱን ካገኙ ዴሞክራሲ ምን ያረግላቸዋል።” “በቱኒዚያ ጠንካራ ተቃዋሚ ቡድን የለም፤ ቤን አሊ ቢወርድ ስልጣን ማን ይረከባል፤ ቢያንስ እሱ መረጋጋትን አስፍኗል።” እና የመሳሰሉት አስተያየቶች ይሰጡ ነበር። በዚህም ምክንያት፣ የቱኒዚያ ህዝብ ሲገደል፣ ሲታሰር፣ ሰቆቃ ሲደርስበት፣ በስራ አጥነት እና በኑሮ ውድነት ሲንገላታ ሃያላኑ አገራት ዝም አሉ።
የቱኒዚያ የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ደግሞ የባሰውኑ በህዝባዊ አመጹ ምክንያት የተነሳውን አለመረጋጋት በቁጥጥር ስር ለማዋል ቤን አሊን እንደምትረዳ አመላከተች። አመጹ ተስፋፍቶ ቤን አሊ እስኪፈረጥጥ ድረስም ዝም አለች።
እንግዲህ አምባገነኖች የፈለጉትን ያህል ቢጠነክሩ፤ ህዝብ የሚረዳው ሃያል አገር ቢያጣ፤ አይሆንልህም፤ እራስህን በራስህ ማስተዳደር አትችልም፤ ልዩ መሪ ያስፈልግሃል፤ ያንን ደግሞ ስለሌለህ ላለህ አምባገነን አጎንብሰህ ለዘላለም ተገዛ ተብሎ ቢፈረድበትም፤ በቃኝ ብሎ የፈነዳ ለታ ሊያቆመው የሚችል ሃይል እንደሌለ የአለማችን ታሪክ አሳይቶናል። በቱኒዚያ የሆነውም ይኸው ነው።
ሙሃመድ አል ቦዚዚ የሃያ ስድስት አመት ቱኒዚያዊ ወጣት ነበር። የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ቢኖረውም፤ በቤን አሊ የተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እና አገሪቱ ከተዘፈቀችበት ሙስና እና ዘረፋ የተነሳ እንደ ብዙ ቱኒዚያውያን ወጣቶች ስራ አልነበረውም።
ታዲያ፥ ታታሪዎቹ የኢትዮጵያ ወጣቶች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እራሱን እና ቤተሰቡን ለመርዳት ቆርጦ የተነሳው ወጣት፣ ሲዲ ቦዚድ በተባለችው ከተማው ጎዳናዎች ዳርቻ ላይ ፍራፍሬ እና አትክልት በመሸጥ ድህነቱን መዋጋቱን ተያያዘው። ይሄ ግን፥ ቀድሞውን የልጁን እጣ ፈንታ ለሰረቁት፣ ኑሮውን የድህነት መቀመቅ ውስጥ ለከተቱት የአምባገነናዊው አገዛዝ ቅጥረኞች ተቀባይነት አልነበረውም። የንግድ ፍቃድ የለውም በሚል ሰበብ ፖሊሶች ምርቱን ቀሙት፤ መደቡንም አፈረሱበት።
ከአንድ ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ መገናኛ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሆነውም ይኸው ነው። እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ከረሃብ ለማዳን እመንገድ ላይ ሸቀጣሸቀጥ በመሸጥ ትርፍ ለማግኘት የሞከሩ ወጣቶች፣ የጠላት ወታደሮች እንደሚያደርጉት በዘረኛው አገዛዝ ፌዴራል ፖሊስ ተከበው እቃቸውን ተቀምተዋል፤ በእንባ እየተራጩም ተስፋ ወደጠፋባቸው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተበታትነዋል።
ሙሃመድ አል ቦዚዚ ግን አልቅሶ ወይም ተናዶ ዝም አላለም። የሱ ቁጣ እና ተስፋ መቁረጥ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ነበር። የሃያ ስድስት አመቱ ወጣት ታህሳስ 9 ቀን 2003 አመተ ምህረት ከአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ቆሞ በራሱ ላይ እሳት አቀጣጠለ።
የሙሃመድ አል ቦዚዚ እርምጃም፣ እንደ ክብሪት ሆና የቱኒዚያን ህዝብ ቁጣ ጫረች….
ወጣቱ እራሱን ካቃጠለ በኋላ የፈነዳው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ እየዘለለ ምድሪቱን አጥለቀለቃት። የቤን አሊ መንግስት የአገሪቱን መከላከያ ሃላፊ ህዝቡን እንዲያጠቃ አዘዘ፤ ሃላፊው እምቢ አለ፤ ከስልጣኑም ተወገደ። በኢትዮጵያችን ቁልፍ የመከላከያ የስልጣን መቀመጫዎች በሙሉ በዘረኞች በመያዛቸው፤ እንደዚህ ግለሰብ ወቃሽ ህሊና ይኖራቸዋል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል።
እናም አምባገነኑ ቤን አሊ ወታደሮቹን እና ፖሊሶቹን በህዝቡ ላይ አዘመተ። በአስርት የሚቆጠሩ ተገደሉ፤ መቶዎች ቆሰሉ፤ በርካቶች ታሰሩ። ጋዜጠኞች እና የኢንተርኔት ላይ ጸሃፊዎች ከያሉበት ተለቀሙ። ከ1997 ምርጫ በኋላ መለስ ዜናዊ በህዝብ ላይ ያካሄደው ጥቃት አይነት በቱኒዚያም ተከሰተ።
ህዝቡ ግን አልቆም አለ። “ቤን አሊ ውጣ ውጣ!” “ቤን አሊ ዘመንህ አልቋል!” እያለም ጮኸ። የደህንነት ሰራተኞቹ እና ወታደሮቹ የአፈና ሙከራቸውን አፋፋሙት። ሰልፈኞቹን በየቦታው በማገት እና በማጥቃት ለማስቆም ሞከሩ። ይሁን እንጂ፥ ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች በራሳቸው በመሰባሰብ በተናጠል ሰልፍ ማድረግ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ሁኔታው ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነው የአገዛዙ ቅጥረኞች፤ ሰዓት እላፊ ለመጣል ሞከሩ። ለጊዜውም ፋታ ያገኙ መሰለ…ይሁን እንጂ ያልተበገሩ ጥቂቶች ትእዛዝ እየጣሱ በመውጣት ህዝቡን ያነሳሱት ነበር።
ይህ፥ የአንድ ሰዓት እላፊ ትእዛዝ ሰባሪ ቱኒዚያዊ ድምጽ ነው…
“ቱኒዚያ ለዘላለም ትኑር! የቱኒዚያ ህዝብ ዛሬ ነጻ ነው! የቱኒዚያ ህዝብ ሆይ ተነስ! አትፍራ! የቱኒዚያ ህዝብ አይፈራም! አምባገነኑ ሸሽቷል! ዛሬ ነጻ ህዝብ ነን! የቱኒዚያ ህዝብ አይፈራም! የቱኒዚያ ህዝብ ሆይ እራስህን ከፍ ከፍ አድርግ! እንስሳው ቤን አሊ ፈርጥጧል! በዚህ ምሽት ነጻ ወጥተሃል! ነፃነት ለዘላለም ትኑር!”
አዎን፥ ያልተበገሩት ጥቂቶች…ነገሮች ጋብ ያሉ ሲመስሉ፤ ዝም ያሉ ሲመስሉ፤ ክፍተቱን በድፍረታቸው ይሞላሉ!
የቱኒዚያው ህዝባዊ አመጽ ዋና ከተማው ደረሰ። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ጎዳናዎቹን አጥለቀለቁ። ቤን አሊ ከስልጣን እንዲወገድ ጥሪ ቀረበ።
ገድሎ፣ ደብድቦ እና አስሮ አልሆንለት ያለው አምባገነን፤ አሁን በተስፋ መቁረጥ ብዙም ያላሰበባቸውን እርምጃዎች መውሰድ ጀምሯል። ህዝቡን ሲያስገድል የቆየው እሱ መሆኑን ለመሸፈን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ወንጅሎ ከስልጣን አባሮታል። ህዝብ ግን አልታለለም።
ቤን አሊ በጥድፊያ ቃል መግባት ጀመረ። “ቃል እገባለሁ…በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ስራዎችን እፈጥራለሁ። የኑሮ ውድነቱን በቁጥጥር ስር አውላለሁ። ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ። ከአራት አመታት በኋላ የስልጣን ዘመኔ ሲያልቅ እወርዳለሁ።” እና የመሳሰሉትን ተናገረ። ህዝብ አልሰማ አለ። ቀጥሎ ደግሞ “እሺ በስድስት ወራት ውስጥ አዲስ ምርጫ አካሄዳለሁ አለ።”
አምባገነኖች አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ የማይናገሩት የለም፤ ይህን እኛም እናውቀዋለን። መለስ ዜናዊ ከአመት አመት የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ሲል የማይገባው ቃል፣ የማይዋሸው ውሸት እንደሌለ እናውቃለን። ወደፊትም የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ፤ ከዚህም የባሰ ውሸት እንደሚዋሽ እና ቃል በቃል ላይ እንደሚያዥጎደጉድ ይጠበቃል። ሰሞኑን የኑሮ ውድነትን እቆጣጠራለሁ ብሎ መፎከሩም ከዚሁ የሚመደብ ነው። ታዲያ የቱኒዚያ ህዝብ በቤን አሊ የቃላት ውዥንብር አልተታለለም። ከአመት አመት የአምባገነኑን ውሸት መስማት በቅቶት ስለነበር!
በዚህ ወቅት ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ እንዲህ የሚል ንግግር አደረጉ፦
“ወንድሞቼ እና እህቶቼ፦ ቤን አሊ ውሸታም ነው። ልናምነው አንችልም። በሙስና ለተዘፈቀው አገዛዙ ተጨማሪ ጊዜን ለመግዛት እየሞከረ ነው። ከዚህ ቀደም ዴሞክራሲያን እንደሚያስፈን ቃል ገብቶልን ነበር፤ የሰጠን ግን እስር ቤቶችን እና ሰቆቃን ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በቤን አሊ ትእዛዝ ከ90 በላይ ዜጎች ተገድለዋል። ይህ ሰው ሊወገድ ይገባዋል። ከስልጣን ሊወርድ ይገባዋል። ለፈጸመው ወንጀል እና ሙስና እንዲጠየቅም ፍርድ ፊት መቅረብ አለበት። ወንድሞቼ እና እህቶቼ፦ አሁን ልናቆም እና እጃችንን ልንሰጥ አንችልም! በዚህ ዘራፊ አገዛዝ ላይ ጫናችንን ልናጠናክር ይገባናል። ቤን አሊን ከስልጣን እስክናስወግድ እና ዴሞክራሲያዊ፣ እንዲሁም ህግ እና ሰብአዊ መብት አክባሪ የሆነን ስርአት እስክንገነባ ድረስ አንድ ሆነን መቀጠል አለብን። እንበርታ፤ ድላችን ቅርብ ናት!”
ይህ ንግግር የህዝቡን ስሜት የገለጸ ሆነ። ቱኒዚያውያን የቤን አሊን “የላም አለኝ በሰማይ” ቃላት አልሰማ አሉ። “ቤን አሊ ውሸታም ነው”፤ “ቤን አሊ ዘመንህ አልቋል”፤ “ጫወታው አልቋል”፤ “ቤን አሊ ውጣ” የሚሉ መፈክሮች ተሰሙ።
ህዝቡ ሰልፉን በድፍረት ቀጠለ። በብዛቱም ፖሊሶቹን እና ወታደሮቹን ዋጣቸው። የወታደሮቹ አዛዦች ቤን አሊ ፈርጥጦ ሲሄድ ምን እንደሚውጣቸው በማሰብ በፍርሃት ተወጠሩ። በስተመጨረሻም፣ ፖሊሶቹም፣ ወታደሮቹም፣ ውሸቱም ሊያድነው እንደማይችል የተረዳው አምባገነን አገሩን ጥሎ አንበሳ እንዳየች ውሻ ጅራቱን በሁለት እግሮቹ መካከል ሸጉጦ ፈረጠጠ። በግል አውሮፕላኑ ላይ ወጥቶ ከአገር አገር ሲንከራተት ከቆየ በኋላ በስተመጨረሻ ሳውዲ አረቢያ ጥገኝነት ማግኘቱ ታወቀ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሰልፈኞቹ የአምባገነኑን ሚስት የለኢላ ትራበልሲን ቤተሰብ ንብረቶች መዝረፍ እንደጀመሩ ሪፖርቶች ተሰሙ። ቤተሰቦቿም አገር ጥለው ወደ ፈረንሳይ ሸሹ።
ቤን አሊ መውደቁን ያስተዋሉት የቀድሞ ምእራባውያን ጓዶቹ በአንድ ጊዜ ከዱት፤ ዞር ብለውም የቱኒዚያን ህዝብ እንደሚደግፉ አስታወቁ። ከበርካታ ወራት በፊት እንዲሁ በህዝባዊ አመጽ የተባረረው የኪርጊስታኑ አምባገነን መሸሹን ሲሰሙም ምእራባውያን እንዴት ፈጥነው እንደከዱት ይታወሳል። እስከ መጨረሻው ጸጥ ብላ የቆየችው ፈረንሳይ ቤን አሊን እንደማትቀበል አስታወቀች፤ ጥቂት ቆይታም ዘመዶቹ በአገሯ ባንኮች ያከማቹትን ገንዘብ ከመንቀሳቀስ ማገዷን ገለጸች።
መቸም መለስ ዜናዊ እና አዜብ ይሄንን ሲሰሙ ከኢትዮጵያ ህዝብ እየዘረፉ በአውሮፓ ባንኮች ያከማቹትን ገንዘብ ወደ ሌላ አገራት የማዛወሩን ጉዳይ ሳይመክሩበት አይቀሩም። የኛውን ዘረኛ አምባገነን እና ሚስቱን ከሚያስጠብባቸው ጉዳይ ውስጥ ትልቁ ከስልጣን የተባረርን ለታ ማን ያስጠጋናል የሚለው ጉዳይ ነው። መለስ ዜናዊ እንደሆን ከአረቦቹ ጋር ጠላት ነው። ምእራባውያን እጁ ደም ያለበትን አምባገነን አያስጠጉም። ቻይና እንደሆነች ለንግዷ ስትል ቀጥሎ ከሚመጣው መንግስት ጋር ግንኙነት ትፈልጋለች። ሌሎች የአፍሪካ አገሮች እሱን ከማስጠጋት ጋር ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን የፖለቲካ ጫና ለመጋፈጥ አይፈልጉም። መለስ ዜናዊ በፈጸማቸው የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎች ምክንያት ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሌዎች እና የሌሎችም አገር ዜጎች በአለም ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሊያቆሙት አሰፍስፈው የሚጠብቁት ሰው ነው። “ምን ይውጠኝ ይሆን?” የሚለው ጥያቄ አእምሮውን ጠዋት ማታ ሳያስጠብበው አይቀርም። ለዚህም ነው በጨነቀው ቁጥር ትግራይን አስገንጥሎ አዲስ አገር የመፍጠሩን ጉዳይ ለጓዶቹ የሚያስታውሳቸው።
ከኑሮ ውድነት እና ከስራ አጥነት ጋር የተያያዙ የተቃውሞ ሰልፎች በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በፍጥነት እየተንሰራፉ ነው። ህዝቡ በሙስና በተዘፈቁ እና ከህዝብ በዘረፉት ሃብት ኪሳቸውን በሞሉ አምባገናዊ መሪዎች መገዛቱ በቃኝ እያለ ነው። በበርካታ አገራት ህዝባዊ አመጽ ተቀስቅሷል፤ የአገዛዞቹ ቁንጮዎችም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተዋል። ብዙዎቹ በቱኒዚያ የደረሰው እንዳይደርስባቸው ከወዲሁ የችኮላ እርምጃዎች እየወሰዱ ነው፤ በአንዳንድ ምርቶች ላይም የዋጋ ተመን አድርገዋል። መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ለማድረግ እየሞከረ ያለውም ይኸው ነው።
ዘረኛውን አምባገነን እና የወንጀል እና የዘረፋ ጓዶቹን ፍርሃት ሰቅዞ ይዟቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ከነዚህ የሰሜን አፍሪካ አገራት እጅጉን በባሰ ሁኔታ በአገዛዙ ከፍተኛ ጥቃት እና ግፍ ሲፈጸምበት ቆይቷል። ታዲያ የኛው አምባገነን የስጋን ዋጋ ከ70 ብር ወደ 52 ዝቅ አድርጎ እና የራሱን ጥፋት በነጋዴዎች ላይ አላኮ ህዝብ የሚያታልል መስሎታል። እንደለመደው የውሸት ቃል አዥጎድጉዶ፤ ለሃያ አመታት እንዳልገዛ ሁሉ፤ እድገት የሚመጣው ከአምስት አመታት በኋላ ነው እያለ እና የሃሰት ተስፋ እየመገበ ጊዜ መግዛት የሚችል መስሎታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ብዙ ጥያቄዎች አሉት። እነዚህ ጥያቄዎችም ቁጣውን እያፈሉት ነው።
አዎን፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ጥያቄዎች አሉት፦
- ለመሆኑ፥ የአገራችን ችግር የሁላችንም ነው ከተባለ፣ ድሆቹ እኛ ብቻ የሆንበት ምክንያት ምንድን ነው? ለምንድን ነው መለስና አዜብ በሃብት ላይ ሃብት እየጨመሩ ሲሄዱ፣ እኛ ግን እየደኸየን ያለነው?
- ለምንድን ነው የባለስልጣናቱ ልጆች በአስር ሺህ ዶላሮች የልደት ስጦታ ሲሰጣቸው እኛ ግን በባዶ ሆድ የምናድረው?
- ለምንድን ነው ለባለስልጣናቱ ልጆች እስከ ውጭ አገር ድረስ በዶላር እየተከፈለ ጠባቂ ሲመደብላቸው እኛ ሽሮ እና ዘይት መግዣ ገንዘብ የሌለን? ለምንድን ነው? ይላል የኢትዮጵያ ህዝብ።
ህዝቡ እየጠየቀ ነው…
- ለመሆኑ እንዴት ነው የውጭ አገር የግብርና ኩባንያዎች ከለም መሬታችን ላይ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ እያገኙ፤ እኛ ግን አገራችን የተደጋጋሚ ድርቅ ሰለባ ስለሆነች ረሃቡን ቻሉት የምንባለው?
- እንዴት ነው መለስ፣ አዜብ፣ ስብሃት እና ሳሞራ ከህዝብ የዘረፉትን ገንዘብ ወደ ውጭ አገር ባንኮች እያሸሹ፤ እኛ ተርበንም ቢሆን በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ስም ለወጣው እቅድ ገንዘብ አዋጡ ተብለን የምንገደደው?
- እድገት ፈጠራቸው የምንባለው ችግሮች ባለስልጣናቱን ሳይሆን እኛን ብቻ የሚጎዱት ለምን ይሆን?
- እኛ ከስራዎቻችን እየተባረርን ከባለስልጣናቱ ዘር የወጡ ምርጦች ግን እየተቀጠሩ ያሉት እንዴት ነው?
- እኛ ስራ አጥተን ስንቸገር ለነሱ አዳዲስ ስራዎችን የሚፈጥረው ተአምራዊ የመንግስት ፖሊሲስ ከየት ፈልቆ ይሆን?
- ለመሆኑ እኛ የኤሌክትሪክ ሃይል አጥሮን ስንቸገር እነሱ ገለልተኛ ቴሌቪዥን እና ሬድዮኖችን የሚያፍኑበትን ሃይል የሚያገኙት ከየት ነው?
የህዝቡ ጥያቄ በዚህም አያቆምም…
- መሬት በህገወጥ መንገድ በመሸጥ እና በማስተላለፍ ተከሰው የትናንሽ ከተሞች አስተዳዳሪዎች ሲታሰሩ፤ ከተማ የሚያካክሉ መሬቶች በዚሁ አኳኋን ከየቦታው የነጠቀችው አዜብ በነጻ የምትመላለሰው ለምንድን ነው?
- በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ግብር ባለመክፈል ስም እየተከሰሱ እስር ቤት ሲገቡ፤ የወያኔ ባለስልጣናት ንብረት የሆነው ኤፈርት እና ባለስልጣናቱ ግብር የማይከፍሉት ወይም ባለመክፈላቸው ፍርድ ፊት የማይቀርቡት ለምንድን ነው?
- ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ዜጎች ትናንሽ ወንጀሎችን በመፈጸማቸው በየቀኑ እየታሰሩ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን በጠራራ ጸሃይ ያስጨፈጨፉት ቤተ መንግስት ውስጥ የሚቀመጡት እንዴት ነው?
- ጥቂት ዘረኞች የአገሪቱን ገንዘብ እየመዘበሩ፣ እኛ ግብር የምንከፍለው ለምንድን ነው?
- በየአመቱ ከአገሪቱ በጀት ውስጥ የሚጠፋው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የት እየሄደ ነው?
- ከወርቅ ማእድኖቻችን እየተጠቀመ ያለው ማነው?
- ለባእዳን ነጋዴዎች መሬት በማከፋፈል እየተጠቀመ ያለው ማነው?
- እኛ እንዲህ እየደኸየን የወያኔ ባለስልጣናት ባለሃብቶች የሆኑት እንዴት ነው? ለመሆኑ ሃብታቸው ከየት መጣ?
- ዝርፊያቸውን ካከናወኑ በኋላ ሃብታቸውን የሚያስመዘግቡት፤ እንዲሁም ሃብታቸውን በማስመዝገባቸው ተከታትሎ የሚቀጣቸው ሰው ያለ ለማስመሰል የሚሞክሩት ማንን ለማታለል ነው?
አዎን፥ ህዝቡ ይጠይቃል…
- ለመሆኑ ዴሞክራሲ አለ እየተባልን፣ ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ግን በኛ ያልተመረጡበት ምክንያት ምንድን ነው?
- ሃሳባችሁን በነጻነት ግለጹ እየተባለ፣ ያንኑ ስናደርግ ግን የምንታሰረው፣ የምንደበደበው፣ የምንሰደደው፤ ለምንድን ነው?
- ንጹሃን ለሰቆቃ የሚዳረጉት ለምንድን ነው?
- እኩልነት አለ እየተባልን ከአንድ ዘር የተውጣጡ ምርጦች የፖለቲካን ስልጣን እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲቆጣጠሩ እየተደረገ ያለው ለምንድን ነው?
ለምንድን ነው፣ ለምንድን ነው፣ ለምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ህዝብ፥ እነዚህን እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እየጠየቀ ነው። መለስ ዜናዊ ግን እውነቱን ሊናገር እና ሊመልሳቸው አይችልም። ችግሩ ውሸታምነቱ ብቻ ሳይሆን፤ እውነቱን መናገር የሚወነጅለው እራሱኑ መሆኑ ነው።
የመለስ ዜናዊ እና የቤን አሊ አገዛዞች ብዙ ተመሳሳይነት አላቸው…ሁለቱም ዴሞክራሲን በማስፈን እና ለውጥን በማምጣት ስም ስልጣን ያዙ፤ ነገር ግን አፈናን፣ ፍርሃትን፣ ዘረፋን፣ ሙስናን፣ አድሎን፣ የኑሮ ውድነት ለየህዝቦቻቸው ሰጡ። ሁለቱም ይዋሻሉ፤ ላልተወሰነ ጊዜ ስልጣን ጨብጠው ለመቆየት ይሻሉ።
ቤን አሊ የመንግስትን ስልጣን ተገን በማድረግ ለመጣበት ነገድ አባላት እና ለቤተሰብ ዘመዶቹ ሃብት አጋበሰ። መለስ ዜናዊም በዘር ለተሳሰሩት ምርጦች ኢኮኖሚውን እና የፖለቲካን ስልጣን ሰጥቷል። የቤን አሊ ሚስት ላይላ ትራቤልሲ ከህዝብ በሰረቀችው ገንዘብ ሃብታም ሆነች፤ አዜብ መስፍንም እንዲሁ። ላይላ ትራቤልሲ ዘራፊነቷን ለመደበቅ እራሷን እንደ በጎ አድራጊ ለመቅረጽ ትሞክራለች፤ አዜብ መስፍንም እንዲሁ።
ይህ ሁሉ ሃብት ማግበስበስ፤ ይህ ሁሉ በዘር መደራጀት ግን ህዝብ ተቆጥቶ የተነሳ ለታ አያድናቸውም። ምእራባውያን አገራትም መንገዳገዳቸውን ሲያዩ ጥለዋቸው ይሮጣሉ።
ብዙዎች ስለ ቱኒዚያ የወደፊት ሁኔታ ከወዲሁ ጥያቄ እያነሱ ነው። የጀመሩት ለውጥ ከዳር ይደርስላቸው ይሆን? ሌላ አምባገነን ይነግስባቸው ይሆን? ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ያመሩ ይሆን? እና የመሳሰሉት…
ማን ያውቃል? የቱኒዚያ ህዝብ በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያልፍ ይሆናል። ነገር ግን ቢሳሳት እንኳ፤ እንደማንኛውም ህዝብ ከስህተቱ ሊማር ይችላል። ዴሞክራሲ ማለት ህዝብ ፈጽሞ የማይሳሳትበት ስርአት ማለት አይደለም። ዴሞክራሲ ማለት ህዝብ በፈቃዱ የሚገዛበት እና ስህተት ሲፈጽምም፤ ከስህተቱ የሚማርበት፤ በራሱ ፍጥነት የሚጓዝበት እና የሚያድግበት ስርአት ማለት ነው። “በእኔ አውቅላችኋለሁ” መርህ የሚገዙን አምባገነኖች የሚቀሙንም ይህን ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ ከራሳችን ስህተት የመማር መብት!
ያም ሆነ ይህ፤ የቱኒዚያ ህዝብ ድምጹን አሰምቷል! ምን እንደሚፈልግ ተናግሯል! ጉልበቱንም አሳይቷል! ይህ፥ ወደፊት ለሚመጡትም ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው።
መለስ ዜናዊ ህዝብ በቁጣ መነሳቱ የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እንጂ የማይቀር እንደሆነ ያውቃል። ለዛች ቀንም ሁልጊዜም ቢሆን ይዘጋጃል። ታስረው እንደሰለጠኑ ውሾች ለሱ ብቻ የሚታዘዙ ወታደሮችን ከማሰልጠን አንስቶ፤ በዘር እየከፋፈለ ህዝብ በማጋጨት አይኖችን ከራሱ ላይ የማስነሳት ስራውን በየአቅጣጫው ተሰራጭተው የሚሰሩለትን ቅጥረኞች በማስቀመት ሁሌም እንደተዘጋጀ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ህዝቡን በሃይማኖት መከፋፈልን እንደ ጭንቅ ቀን መውጫው በመቁጠር የመሰረት ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
አዎን፥ የተጠበቡ አምባገነኖች፣ እነሱ ሲሄዱ ሰላም እንዳይኖር ለማድረግ እና ህዝቡ እነሱን በማስወገዱ እንዲጸጸት ብዙ ተንኮል ይሸርባሉ። ይሁን እንጂ፥ ደግመው ደጋግመው እንዳፈሩ የአለማችን ታሪክ አሳይቷል።
መለስ ዜናዊ ከስልጣን ይባረራል። ኢትዮጵያም እንደሱ ምኞት ወደ እርስ በርስ ግጭት እና ደም መፋሰስ አትገባም! ለዘላለም ትኖራለች፤ ድንበሯ ይሰፋል፤ ታብባለች፤ ልጆቿም በሰላም ይኖራሉ!
ለዘረኛው አምባገነን ምእራባውያን ደጋፊዎች አንድ መልክት አለን። አንድ የመካከለኛው ምስራቅ አገር ጸሃፊ ከጻፉት ጽሁፍ የተወሰደ ቅንጫቢ እነሆ፦
“‘ጠብቀን የሚሆነውን እንይ’ የሚለው የዩናይትድ ስቴትስ አካሄድ ከዚህ በኋላ በቂ አይደለም።…አሁን ህዝቡ ካሸነፈ በኋላ መደገፉ ቀላል ነው። ኦባማ ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ሁለት አመታት፣ እሳቸውም ሆኑ የአስተዳደራቸው ባለስልጣናት፣ የቱኒዚያን ህዝብ መሰረታዊ መብት ደግፈው ቆመው አላየንም። ለኦባማ አስተዳደር፣ እውነተኛው ፈተና ያለው አሁን ነው፤ ህዝቡ እርዳታቸውን በሚፈልገበት ወቅት።”
የኛም መልክት ይኸው ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው በራሱ ጉልበት ካሸነፈ በኋላ “እንኳን ደስ ያለህ” እያሉ የሚመጡትን አይደለም። በመከራው ጊዜ ከጎኑ የሚቆሙትን ነው።
ይሁን እንጂ፤ እነሱ ረዱም አልረዱም፤ ነፍሰ ገዳዩን አገዛዝ መደገፋቸውን አቆሙም አላቆሙም፤ መለስን የቤን አሊ እና ከሱ ቀድመው በህዝብ አመጽ ከስልጣን የተባረሩ ብዙ አምባገነኖች እጣ እንደሚገጥመው ጥርጥር የለውም!
የኢትዮጵያ ህዝብ ድል ያደርጋል!