በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚደረገው ማሳደድ ተጡዋጡፎ መቀጠሉ ተገለጸ
ጎጠኛው የወያኔ ቡድን የፈጠራቸውን ሰው ሰራሽ ችግሮች ሽሽት በየጎረቤት ሀገራቱ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከየሚኖሩባቸው ሀገራት መንግስታት ጋር በመደራደር በግዴታ ወደ አገርቤት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፥ ፣ ሰሞኑን ደግሞ በደቡብ ሱዳን የሚታየውን የፖለቲካ ትኩሳት ምክንያት በማድረግ በሱዳን ሃገር በስደት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዴት እየተለቀሙ ለወያኔው አገዛዝ ተላልፈው እየተሰጡ እንደሆነ ዘገባዎች ያሳያሉ፣ ፣ በዚህም መሰረት ብሉ ናይል የሚባለው የሱዳን ክልል አስተዳዳሪ ማሊክ አጋር እና የቤንሻንጉል ክልል ፕሬዝዳንት አህመድ ናሲር አልኩርሙክ በተባለችው የሱዳን ከተማ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሱና የተባለው የሱዳን የዜና አገልግሎት ይፋ አድርጎአል። እንደዘገባው ከሆነ ይህ ዘመቻ በከተማዋና በዙሪያው በስደት በሚኖሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረ መሆኑን አያይዞ ገልጹዋል።
የግንቦት ሰባት ዘጋቢ በጉዳዩ ላይ ያናገራቸውና በአካባቢው ይኖሩ የነበር እና በቅርቡ ወደ ለንደን መግባት የቻሉ አንድ ኢትዮጵያዊ እንደገለጹት በስፍራው በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ግፊት የሱዳን ባለስልጣናት በኢትዮጵያውያኑ ሰደተኞች ላይ እየደረሱት ያለው ግፍ እጅግ ፈታኝ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ ጊዚያቶችም የወያኔ ወታደሮች ወደ ከተማዎቹ ዘልቀው በመግባትና የፈለጉትን ገለው የሚሄዱባቸው አጋጣሚዎች ብዙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የሱዳን ባለስልጣናቱም ሆን ብለው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞችን ሁኔታ እንዳያውቁ እንደሚያደርጉ፡ ይህም የወያኔው አገዛዝ ወታደሮች በስደተኞች ላይ የፈለጉትን እርምጃ መውሰድ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን የተለያዩ የፖለቲካ ተቁዋሚዎች ናችሁ በሚል ስም የወያኔው አገዛዝ ወታደሮች በፈለጉበት ጊዜ ወደ ኬንያ በመግባትና የፈለጉትን ገለው የፈለጉትን አፍነው እንደሚወስዱ ባካባቢው ከሚገኙ ባለስልጣናትም ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያኑ በጅምላ እንዲባረሩ እንደሚደረግ ቀደም ብለን መዘገባችን ይታወሳል።