የአባ ዱላ ገመዳ የቀኝ እጅ የምትባል መሃንዲስ ቤት ክምር ብር መገኘቱን መረጃ አመልክቷል
“ሚሚ” በሚል ቅጽል ስም የምትታወቀው መሃንዲስ በሰበታ ከተማ የመሬት አስተዳደር ጉዳይ ላይ “ፈላጭ ቆራጭ” እንደነበረች ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ግለሰቧ ለአዜብ መስፍን ከፍተኛ መጠን ያለው መሬት የሰጠው የመሬት አስተዳደር ቢሮ ባልደረባ ከመሆኗም ባሻገር፣ የአባ ዱላ ገመዳ የቅርብ ሰው እና ስራ አስፈጻሚ መሆኗን ለከተማው ባለስልጣናት ቅርበት ያላቸው ግለሰብ ለሪፖርተራችን ነግረዋል። ይሁን እንጂ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ሙስናን በመዋጋት ስም አንዳንድ አገልጋዮቹን ማሰር ሲጀምር ከተያዙት ውስጥ አንዷ ሆናለች።
ምንጮቻችን እንደሚሉት፥ በግለሰቧ መኖሪያ ቤት ላይ በተደረገው ፍተሻ ሮቶ በተባለው የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ጥሬ ብር ተከምሮ ተገኝቷል። ጉዳዩ፥ ይህች የአንዲት ትንሽ ከተማ ዝቅተኛ ባለስልጣን ይህን ያህል ገንዘብ ከሰበሰበች፣ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ደግሞ ምን ያህል ደብቀዋል የሚል ጥያቄ ጭሯል።
ቤታቸው ከተፈተሸው ሌሎች የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ባለስልጣናት ውስጥ አንዳንዶቹም በግቢያቸው ውስጥ ትላልቅ የመንግስት ወይም የንግድ ተቋማት እንደሚያደርጉት የጥበቃ ካሜራዎች አስተክለው እንደተገኙ ለማወቅ ተችሏል።