በርካታ ነጋዴዎች አገር ጥለው በሽሽት ላይ እንደሚገኙ ተዘገበ

የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ግብር ባለመክፈል እና በመሳሰሉት ክሶች ሽፋን ከትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ተደጋጋሚ ዘገባዎች ሲያሳዩ ቆይተዋል።

ፎርቹን የተባለው እና ለአገዛዙ ቅርበት ያለው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ፥ በርካታ ነጋዴዎች ከዚህ ስጋት የተነሳ አገር ጥለው መውጣታቸውን ገልጿል። እንደ ጋዜጣው ዘገባ፥ በተለይ ከመሬት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል በሚባል ሙስና የከተማዋ ሹመኞች ብዙ ክስ ለመመስረት በዝግጅት ላይ እንዳሉ መታወቁ የስጋቱን ደረጃ ከፍ አድርጎታል።

የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ የአገሪቱን የንግድ ዘርፍ በሙሉ ከአንድ ዘር በተውጣጡ ምርጦች ቁጥጥር ስር ለማዋል ሩጫ ከጀመረ መቆየቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ፥ ብዙ የዋህ ነጋዴዎች ለህዝቡ ሰቆቃ ጀርባቸውን በመስጠት ለገዢው ቡድን ገንዘብ በገፍ ቢለግሱ ንብረቶቻቸውን ማትረፍ የሚችሉ መስሏቸው ሲለፉ ቆይተዋል። በርግጥም አንዳንዶቹ ነጋዴዎች ለጊዜውም ቢሆን ከዚህ ጥቅም ማግኘታቸው ይታወቃል። ቢሆንም ግን፥ ባለፈው የምርጫ ተውኔት ግርግር ዘረኛውን አገዛዝ በመርዳት የኢትዮጵያን ህዝብ የካዱት ነጋዴዎች ሳይቀሩ ከዚህ ጥቃት እንደማይተርፉ የፎርቹን ዘገባ አመልክቷል።

ነጋዴዎቹ በመተባበር ለዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ የላኩት ተማጽኖም ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም የተነሳ በርካታ ታዋቂ ነጋዴዎች ባለፉት ሳምንታት አገር ጥለው መውጣታቸው የአጋጣሚ ጉዳይ እንዳልሆነ ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።