በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው የሚፈጸመውን ሰቆቃ እያወገዙ ነው

በአለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያውን ማህበራት እና ግለሰቦች የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በእናት አገራቸው በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ሰቆቃ እያወገዙ ነው።

የኢትዮጵያውያን ሴቶች የሰብአዊ መብት ጥምረት የተባለው ድርጅት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የሶስት ልጆች እናት የሆኑ ሴት ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ስለመሆኑ ማስረጃ እንደደረሰው ገልጿል። ድርጅቱ በመግለጫው፥ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ የተባሉት እና በ2001 መንግስት በመገልበጥ ሙከራ ተከሰው ከታሰሩት ውስጥ ብቸኛዋ ሴት የሆኑት እናት ስለደረሰው ሰቆቃ ዘርዝሯል።

ወ/ሮ እማዋይሽ እይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ እና እጃቸው በሰንሰለት ታስሮ ወደ ስቃይ መነዳታቸውን፤ እጃቸው ታስሮ መሰቀላቸውን፤ እግራቸው መገረፉን፤ እንዲሁም የውስጥ ታፋቸው፣ መቀመጫቸው እና እጆቻቸው መገረፋቸውን የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክት ገልጿል። መግለጫው ጨምሮም፥ እናቲቱ ልብሳቸውን አውልቀው ጡቶቻቸው እስኪደሙ በኤሌክትሪክ ገመድ መገረፋቸው ከሁሉ የከፋው መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያው አገዛዝ በወ/ሮ እማዋይሽ ላይ የሚፈጽመውን ሰቆቃ በአስቸኳይ እንዲያቆም እና አለማቀፍ የሰብአዊ ስምምነቶችን እንዲያከብርም ጥምረቱ ጥሪ አድርጓል። አንድ የጥምረቱ ተወካይ፥ ድርጅታቸው በተከሰተው ጉዳይ እጅጉን ቢቆጣም፣ አገዛዙ በአገሪቱ ውስጥ ከሚሰራው ስራ አኳያ አስገራሚ ግን እንዳልነበረ መናገራቸውን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

አለማቀፍ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ድርጅትም ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሰቆቃ እጅጉን እንደሚያወግዝ ገልጾ፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሲቪል ድርጅቶችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ አቅርቧል።

ከድርጅቶች በተጨማሪ፥ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መድረኮች ቁጣና ሃዘናቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። በሆላንድ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ለተለያዩ ድረ-ገጾች በላኩት መልክት፤ የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በእናት ሃገር የሚፈጽመውን ሰቆቃ አስመልክቶ በቅርቡ የወጣውን ሪፖርት ካነበቡ በኋላ የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ቃላት እንደማይገልጹት እና እንቅልፍ መተኛት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።

በዘረኛው አገዛዝ ቁጥጥር ስር በሚገኙ የደህንነት እና የህግ አስከባሪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን “ከውርደት ህይወት ሞት ይሻለናል” በሚል ድፍረት፤ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ በንጹሃን ላይ የሚፈጸመውን ሰቆቃ የሚያጋልጥ ሰፊ ሪፖርት አዘጋጅተው ማውጣታቸው ይታወቃል።