የወያኔ የመሬት ፖሊሲና የገበሬው ሰቆቃ
መሬት ለኢትዮጵያውን ገበሬወች የህልውናቸው እስትንፋስ ነው:: ለኢትዮጵያውን መሬት ከምጣኔ ሀብታዊ መተዳደሪያነቱ ባሻገር የአርነታቸው ነጸብራቅም ነው:: በተለያዩ ስርዓቶች ገበሬው ላይ ሲደርሱ የነበሩና እየደረሱ ያሉት ግፍና ሰቆቃ የገበሬውን እና የመሬቱን ጥብቅ ቁርኝት መነሻ በማድረግ ነው:: ቀደም ባሉት ጊዜያት ገበሬው ጭሰኛ : ገባር ነበር አሁንም በወያኔ ጭፍን የመሬት ፖሊሲ ምክንያት ገበሬው የባለቤትነት መብቱ ተነጥቆ ተከራይ ሆነል:: ለዘመናት ጥሪቱንና ላቡን ያፈሰሰበትን መሬት በአንድ ጀምበር ተንጥቆ በእኛ እናውቅልሀለን የአምባገነኖች የመሬት ፖሊሲ ወደ ባሰ ድህነት ተሸጋግሩአል:: የወያኔው አገዛዝ በአንድ ወገን ነጻ ገበያ አራምዳለው እያለ በሌላ በኩል የመሬት የግል ባለቤትነት መብት መንፈጉ- መሬት እንድ አንድ ካፒታል ገበያው ውስጥ በመግባት የራሱን አስተዋጽኦ እንዳያበረክት እንቅፋት ሆኖበታል::
ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ኑሮ ምክንያት ገበሬው ሌላ ቋሚ ንብረት ማፍራት ባለመቻሉ መሬቱ ላይ የሚመነጩትን ድርብ መብቶች (bundle of rights ) እንዲጠቀምበት የሚያበረታቱና የሚያስቺሉ የመሬት ፖሊሲወችን መንደፍ የአንድ ሀላፊነት የሚሰማው መንግስት የቤት ስራ ነው:: የዜጎች የሀገሪቱን ሀብት በእኩል የመጠቀም መብት ቅድሚያ ሊሰጠውና ትኩረትም ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው:: መንግስት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሀገሪቱን ሀብት እኩል ከዜጎች ጋር ሊጠቀምና ሊያስተዳድር መብትና ስልጣን ከህዝብ ተሰጠው እንጅ ከዚያ አልፎ አሁን እንደምንመለከተው የወያኔው አገዛዝ የዜጎችን መብት መገደቡ የዚህ ስርኣት አምባገነንነት አይነተኛ መገለጫ ነው::
በተጨማሪም የወያኔው አገዛዝ እየተከተለ ያለው አሰራር የመሬት ፖሊሲውን ኢ-ፍትሀዊነት ይገልጽ እንድሆን እንጂ ለገበሬው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ ሲያመጣ አልተስተዋለም:: የከተማው ነዋሪ በገበሬው ላይ ጥገኛ ከመሆኑም በላይ በአንጻሩ በከተሞች ለገበሬው የሚሆን ምቹ የስራ እድል ባለመኖሩ የገበሬው የዛሬውም የወደፊቱም ተስፋ በመሬቱ ላይ እንዲወሰን አስገድዶታል:: በየአምልኮ ቤቱ ደጃፍ ላይ ተቀምጦ ምጽዋት የሚለምነውና : መሬቱን በወያኔው አምባገነን አገዛዝ ጫና (ደላላነት) ለውጭ ኢንቨስተር አሳልፎ ሰጥቶ ወደውጭ ሀገር የሚሰደደው ገበሬ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ የመሬት ፖሊሲ ውጤት ነው::
በመስኩ የተሰራ ጥናትን ዋቢ በማድረግ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ልሳን የሆነው “አዲስ ምእራፍ” መጽሔት እንዳሰፈረው በሀገሪቱ ከ200,000 የማያንሱ ወገኖች በልመና ላይ ተሰማርተው በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ:: ከእነዚህም መካከል አብዛኛወቹ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በግብርና ስራ ይተዳደሩ የነበሩ መሆናቸው በግልጽ ይታያል:: ገበሬው አቅራቢ እንጂ ተጠቃሚ ሊሆን ባለመቻሉ ኑሮው ከእለት እለት እያሽቆለቆለ ሄዱአል:; ይሁን እንጂ ባንጻሩ የወያኔው አገዛዝ የሚዲያ ጀግኖች “ሞዼል አርሶ-አደሮች” የስርኣቱ አሸርጋጆች ምልምል የገበሬ ካድሬወች እንጅ ምስኪኑን የኢትዮጵያ ገበሬ እንደማይወክሉ የኢትዮጵያ ህዝብ አሳምሮ ያውቀዋል:: የሚዲያ ጀግኖቹ ማስታወቂያ ወያኔ በህዝብ ዘንድ ያለውን መጥፎ ስም ለመቀየር የሚጠቀምበት ስትራቴጂ እንጅ ከሌላው ገበሬ የበለጠ ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጡ ይታወቃል::
ወደዋናው ነገር ስንመጣ የወያኔን የመሬት ፖሊሲ በተመለከተ ትልቁ ተግዳሮት ከዚህ እንደሚከተለው ሊገለጽ ይችላል:በመጀመሪያ የይዞታ ዋስትና አለመኖር (Tenure insecurity ) ትልቁ ችግር ነው:: የመሬት ባለቤትነት በኦፊሲል ከወያኔው አምባገነን አገዛዝ እጅ ስር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ገበሬው በይዞታው ላይ የእነነት ስሜት እንዲያጣ:: የይዞታ ዋስትና አለመኖር የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ አለው : ገበሬው መሬቱን እንደራሱ ሀብት አድርጎ ይዞ ዘላቂ ልማት እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበታል:: የመሬቱን ለምነትና ስነ-ምህዳራዊ ደህንነት ጠብቆ ከማምረት ይልቅ ጊዜያዊና ገበያ ላይ ብቻ አትራፊ ይሆናሉ ያላቸውን ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ተግዶአል:: በዚህም ምክንያት ሸማቹ የሚፈልገውና ገበሬው የሚያመርተው ባይነትም ሆነ በመጠን ሊጣጣም አልቻለም:: ከዚሁ ቁልፍ ችግር በተጨማሪም የይዞታ ዋስትና አለመኖር ዘለቄታዊ ኢንቨስትመንትን በእጅጉ ያዳክማል :: ከሁሉም በላይ ገበሬው በማሳው ላይ ዛፍን እንዳይተክል ትልቅ እንቅፋት በመፍጠሩ ገበሬው የማሳውን አፈር መከላት መቆጣጠር ካለመቻሉም በላይ የማሳውን ለምነት መራቆትና ምርት አልባ መሆን መከላከል አለመቻሉን መጥቀሰ ይቻላል:: የመሬት መራቆት ችግር ድምር ውጤት ደግሞ ከገበሬው ክልል አልፎ በዓለማችን እየታየ ላለው የአየር ንብረት መዛባት የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለት ነው::
በኢንቨስትመንት ለውጥ ለማምጣት ከተፈለገም የማሳውን ባለቤት ራሱ ገበሬውን በኢኮኖሚና በተክኖሎጂ አቅሙን በማሳደግ (በማጠናከር) የለውጥ ሀይል ማድረግ ሲቻል-ገበሬው በአምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ መሬቱን ተነጥቆና በገዛ ሀገሩ አይኑ እያየ መሬቱ ለባእዳን ተሰጥቶበት የፍትህ ያለህ እያለ ይገኛል::
በሁለተኛ ደረጃ የአምባገነኑን ወያኔ የመሬት ፖሊሲ በተመለከተ የገበሬው ተግዳሮት መሬት የማግኘት መብት (access to land )ችግር ነው:: ምንም እንኩ ህገ-መንግስቱ ማንኛውም እድሜው ከ18 አመት በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ በግብርና ስራ ለመተዳደር ፍላጎት ያለው ያለምንም ክፍያ መሬት ማግኝት ይችላል ቢልም በተግባር ሲታይ ግን እየሆነ ያለው ተቃራኒ ነው:: ለምሳሌ ብዙ ወጣቶች መሬት ይሰጠን ብለው ሲጠይቁ በማህበር ካልተደራጃችው አንሰጥም እንደሚባሉና በማህበር ሲደራጁ ደግሞ ለእናንተ የሚሆን ከሌሎች ባለይዞታወች ላይ ተቆርሶ ስለሚሰጣችው የመሬት ክፍፍል እስኪደረግ ጠብቁ እንደሚባሉ በምሬት ይገልጻሉ:: እነዲህ አይነቶቹ ወጣቶች ሌላ ምንም አይነት አማራጭ ሰለሌላቸው ወይ ለልመና ይዳረጋሉ አለያም ሀገር ጥለው ይሰደዳሉ::
እንደ አብነት ለመጥቀስ የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ በስራ አጋጣሚ ያነጋገራቸው የምእራብ ጎጃም ዞን የጎንባት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ገበሬወች እንደገለጹት “ምንም እንኩ ሰፋፊ መሬት ባካባቢያችን ቢገኝም በአጥር ተከልሎ ለውጭ ባለሀብቶች ለአበባ እርሻ ተቀምጡአል ” በማለት ተናግረዋል:: እነኝሁ ገበሬዎች ከመሬት እጦት የተነሳ በአካባቢው ወጣት ጥፋተኞች እንደተበራከቱ አክለው ገልጸዋል::
ባጠቃላይ የወያኔው አምባገነን አገዛዝ ገና በጠዋቱ በስልጣን ወምበር ላይ ሲኮፈስ ለመሬት ፖሊሲው ልዩ ትኩረት በመስጠት አሁን እየተከተለ ያለውን አሰራር እንዲተገብር የወሰነበት ቁልፍ ምክንያት መሬትን ለፖለቲካ ጥቅም በማዋል የሃገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 80 በመቶ የሚሸፍውን ገበሬ በቁጥጥሩ ስር በማዋል እንደፈለገው ለመድረግ የወጠነው ረቂቅ ሴራ እንደሆነ በርካታ ምሁራን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል ::