በጋምቤላ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፊት መሆኑ ታወቀ
ዘረኛው አገዛዝ ከሰባት አመታት በፊት በጋምቤላ ፈጽሞታል የሚባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ በአለም አቀፍ ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ፊት እየታየ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ገልጸዋል።
በዚህ ሳምንት የጭፍጨፋው ሰባተኛ አመት ታውሶ ሰንብቷል። መታሰቢያውን በሚመለከት ከዶ/ር አለማየሁ ገብረማሪያም ጋር ውይይት ያደረጉት ኢትዮጵያዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ የጋምቤላው ጉዳይ በአለማቀፉ ወንጀለኛ ፍርድ ቤት ፊት እንደሚገኝ ገልጸዋል። የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ጀኖሳይድ ዋች በተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ፕሬዚደንት ዶ/ር ግሬጎሪ እስታንተን የተላከለትን ጥሪም በመቀበልም ጉዳዩን እያጠና ነው ብለዋል።
አቶ ኦባንግ ሜቶ እነ መለስ ዜናዊን ለፈጸሙት ወንጀል ፍርድ ፊት ለማቆም በቂ ህጋዊ መሰረት እና ማስረጃ መኖሩን ጠቅሰዋል። የጋምቤላው ጭፍጨፋ ጉዳይ ብቻ የትግራዩን ገዢ ጉጅሌ ባለስልጣናት ለፍርድ ለማቅረብ ጠንካራ እና በቂ መሆኑን ገልጸው፤ አገዛዙ በሌሎች አካባቢዎች የፈጸመው ወንጀልም ተጨማሪ ጥንካሬ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።
አቶ ኦባንግ፥ በካምቦዲያ ከሃያ አመታት በፊት የተሰበሰበ ማስረጃ በዚህ አመት በወንጀለኞች ላይ እንዳስፈረደ ጠቅሰው፤ እነ መለስ ዜናዊም አንድ ነጥብ ላይ ቀን እንደምትጨልምባቸው እርግጠኛ እንደሆኑ እና ለዛም ተዘጋጅተው እንደሚጠብቋቸው ገልጸዋል።
በርካታ የዘረኛው አገዛዝ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ውስጥ ለፈጸሟቸው የጅምላ ግድያዎች እና ሌሎችም ወንጀሎች በአለማቀፍ ድርጅቶች እና በኢትዮጵያውያን ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ከዚህ ቀደም ዘግበናል።