በመንግስት ሰራተኞች ቅጥር ላይ እገዳ እየተደረገ ነው

ከግንቦት 15ቱ የምርጫ ተውኔት በፊት ድጋፍ ለማግኘት ሲል ገዢውን ቡድን ለተቀላቀሉ ሁሉ ስራ እሰጣለሁ እያለ አባላትን በጥቅም ሲያግበሰብስ የቆየው የወያኔ አገዛዝ የቅጥር እገዳ መጀመሩን ለማወቅ ተችሎአል።

የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈችው ዘገባ፥ የኦሮምያ ክልል አስቸኳይ የቅጥር እገዳ ትእዛዝ በማስተላለፍ ይህንን በስራ ላይ አውሏል። በቅርቡ አንድ የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት ቢሮ ሹመኛ የአስተዳደር እና የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሃላፊዎችን ሰብስቦ፤ አገዛዙ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ያወጣውን እቅድ በተገቢው መንገድ ለማስኬድ አንዳንድ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ በማስታወቅ፤ እስከዛ ድረስ ሃላፊዎቹ ላልተወሰነ ጊዜ ቅጥር እንዲያቆሙ ትእዛዝ አስተላልፏል። ይህንንም ትእዛዝ የያዘ ሰርኩላር ለየቢሮዎቹ ተላልፏል።

የኦሮምያ ክልል ምንጮች ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት፥ አዲሱ የቅጥር እገዳ የአገዛዙን የውሸት ተስፋ ተቀብለው በየቢሮው ስራ ፍለጋ የሚኳትኑትን አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ክፉኛ ይጎዳል። “አገዛዙ በአገሪቱ ውስጥ የተማረ የሰው ሃይል እጥረት አለ እያለ ዘወትር ያላዝናል” ያሉን ምንጭ፤ “አሁን ስራ አጥቶ የሚንከራተተው ባለ ዲግሪ እና ዲፕሎማው ነው” ብለዋል። “የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዳው እንደዚህ እያደገ እና እየሰፋ ነው ከተባለ፤ ለነዚህ ወጣቶች እየተፈጠረ ያለው ስራ የታለ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ግለሰቡ ጨምረው፥ የቅጥር እገዳው ቋሚ ሰራተኞችንም ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መክተቱን ገልጸዋል። ሰራተኞች በየጊዜው ለገዛ ስራቸው እንደ አዲስ እንዲወዳደሩ እየተደረጉ እና እየተባረሩ ስላሉ ሰው ሁሉ በጭንቅ ውስጥ እንደሚኖር አስረድተዋል።

በኦርምያ ክልል ቢሮዎች ውስጥ ለትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ያለው ጥላቻ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጻለች።