በደቡብ አውስትራሊያ በምትገኘው አደላይድ ከተማ የድህረ ምርጫ 97 ሰማእታት ታስበው ዋሉ
በደቡብ አውስትራሊያ በምትገኘው አደላይድ ከተማ የድህረ ምርጫ 97 ሰማእታት መታሰቢያ በአል መከበሩን ከስፍራው የደረሰን ዘገባ አመልክቷል።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች የግንቦት 7 ድምጽን የዝግጅት ክፍል ጨምሮ ለበርካታ መገናኛ ብዙሃን የላኩት ሪፖርት፤ ቅዳሜ ታህሳስ 3 ቀን በተካሄደው የመታሰቢያ በአል ላይ ምርጫውን ተከትሎ የነበረውን ሁኔታ ለማስረዳት ይሆን ዘንድ የተዘጋጀው የፊልምና የፎቶግራፍ ቅንብር ታዳሚውን እንባ አራጭቷል ይላል።
የበአሉን አስተባባሪዎች በመወከል ዝግጅቱን በንግግር የከፈቱት አቶ መኮነን ምስጋናው፦ “ባለንበት ዘመን የእውነትን ታላቅነት የሚያምኑ በርካቶች ቢኖሩም ለእውነት የሚቆሙት፤ አልፎ ተርፎም መስዋእትነት የሚከፍሉት ጥቂቶች ናቸው። እኛም ዛሬ የተሰባሰብነው ከ80 ሚሊዮን የአገራችን ህዝብ ጋር ሲነጻጸሩ ከቁጥር የማይገቡ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችንን ለማሰብ ነው። እነዚህ ሰዎች ትናንት አፈር ቢለብሱም፣ ስማቸው እና ታሪካቸው ግን ምንጊዜም ህያው ነው” ብለዋል።
በዝግጅቱ ላይ በስልክ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የህወሃት የፋይናንስ ክፍል ሃላፊ አቶ ገብረመድህን አራያ፥ ባደረጉት ንግግር ወያኔ የህዝብ ውክልና የሌለው ዘረኛና አገር የማፍረስ አጀንዳውን እየተገበረ ያለ ጸረ አገር ቡድን ነው ካሉ ቦኋላ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ግንባር ስር ተሰባስቦ ወያኔን መዋጋት አለበት” ብለዋል።