የቃሊቲ እስር ቤት የውጭ አገር ዜጋ የሆኑ እስረኞች ተቃውሞ ማሰማታቸው ታወቀ
የመዲናይቱን የእስር ቤት አስተዳደር ዘረኛ አወቃቀር፣ ወንጀሎች እና ሙስና በሚመለከት ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ ሰፊ መረጃ እንደጠቆመው፤ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ የእስረኞች ቁጥር ከብዙ እጥፍ በላይ ጨምሯል።
“ከ10 አመት በፊት በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ውስጥ በዛ ከተባለ 2 ሺህ እስረኛ ነበር” ያሉት ምንጮች፤ “…አሁን በቃሊቲ ብቻ 10 ሺህ እስረኞች ይገኛሉ” ብለዋል። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ሲሆኑ፤ ሰባት መቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል። ይህ ቁጥር ከቦታ መጣበብ የተነሳ ወደ ዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት የሚላኩትን ከግምት እንዳላስገባም ምንጮቻችን አስምረውበታል።
በቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ “የሰው ልጅ እንደ ጆንያ እየተነባበረ እየተኛ ነው፤ ብርድ ልብስ እና ምንጣፍ የለም፤ የውሃ ችግር አለ” ያለው መረጃ፤ ኢትዮጵያ “ሰው እንደ እቃ የሚታይባታት አገር ሆናለች” ይላል። በዚህ ምክንያትም ጥቅምት 16፣ 2003 አመተ ምህረት የውጭ ዜጋ የሆኑ እስረኞች ከፍተኛ ተቃውሞ እንዳስነሱ የታወቀ ሲሆን፤ ጩኸታቸው ግን ሰሚ እንዳላገኘ ለመረዳት ተችሏል።
በማረሚያ ቤቶቹ ውስጥ ባለው ሁኔታ እንኳን እስረኞች ፖሊሶችም እያማረሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ምንጮች፤ የቃሊቲን እስር ቤት “ሲኦል” ብለውታል። ይህንን ሁኔታ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲያዩት እንደማይፈቀድም ታውቋል። እነ ፓስተር ዳንኤል በቴሌቪዥን ላይ የሚያሳዩት የእስር ቤቱ ክፍል፥ ከፊሉ የራሳቸው ቢሮ ሲሆን የተቀረው የአጠቃላይ እስር ቤቱን ሁኔታ የማይወክል እና ለፕሮፓጋንዳ ጥቅም ሲባል ብቻ የታየ እንደሆነም ምንጮቹ ገልጸዋል።