ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መጠለያ አልባ መሆናቸው ታወቀ
በርካታ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ ያለ በቂ ካሳ በመሰናበታቸው መጠለያ አልባ ሆነው በመንከራተት ላይ እንደሚገኙ የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው መረጃ አመልክቷል።
ሪፖርተራችን ሰሞኑን አጠናቅሮ በላከው ዘገባ እንደገለጸው፥ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ ገበሬዎች በልማት ስም ከይዞታቸው ላይ እንዲፈናቀሉ መደረግ ከተጀመረ መቆየቱን አስታውሷል። ከከተማ ባለስልጣናት ጋር በመመሳጠር እና ለገበሬዎቹ ከ30 እስከ 50 ሺህ ብር በመክፈል ባለቤትነትን የሚረከቡት ግለሰቦች፤ ያንኑ መሬት መልሰው በአራት እና በአምስት እጥፍ እንደሚሸጡት በአየር በአየር የመሬት ንግድ የሚሳተፉ ግለሰብ ለዝግጅት ክፍላችን ነግረዋል።
የኑሮ ውድነት የከፋ ደረጃ ላይ በሚገኝበት ዘመን ይህ ክፍያ ብዙ የቤተሰብ አባላት ላሉት ገበሬ እዚህ ግባ የሚባል ካለመሆኑ በተጨማሪ፤ አብዛኛው አርሶ አደር ቀጥሎ ምን እንደሚሰራ ስለማያውቅ ለእንግልት እየተዳረገ እንደሆነ ታውቋል።
ዘጋቢያችን ያናገራቸው አንዳንድ አርሶ አደሮች፥ መድረሻ አጥተው በመንከራተት ላይ መሆናቸውን በለቅሶ ጭምር አስረድተዋል። የተወሰኑት ወደ አዲስ አበባ ተሰደው የወዛደርነት ስራ ለማሳደድ መገደዳቸውንም መረጃው አመልክቷል።